ይህ ጽሑፍ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከውርስ ሕጉ አጠቃላይ አወቃቀር እና አደረጃጀት ወጥተው በአንደኛው የውርስ ሕግ ክፍል የተደነገገን ድንጋጌ አግባብነት ለሌለው ሌላ የውርስ ሕግ ክፍል ተግባራዊ በማድረግ አንዳንዴም በጉዳዩ ላይ ተፈጻሚነት ያላቸዉን የውርስ ሕግ ድንጋጌዎች በመተዉ አጠቃላይ የዉል ሕግ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ ገዥ ትርጉም መስጠታቸውን እና ይህም ሕጉን የተከተለ አለመሆኑን ይከራከራል፡፡ እንዲሁም በዚህ ምክንየት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በራሱ ተቃራኒ እና ምክንየታዊ ያልሆኑ ውሳኔዎች እየተሰጡ መሆኑን በማሳየት የውርስ ሕጉ ሊተረጎም እና ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ ይጠቁማል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአዋጅ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የመስጠት ስልጣን ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ በሃገራችን ወጥ፤ ተመሳሳይ እና ተገማች የሕግ ትርጉም እንዲኖር ያደረገው አስቷጽኦ እጅግ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ ነገር ግን እጅግ አልፎ አልፎ በችሎቱ በራሱ እርስ በእርስ የሚቃረኑ ውሳኔዎች እና ሕጉን ተከትለው የተሰጡ የማይመስሉ የሕግ ትርጉሞች ይታያሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ በውርስ ሕጉ የተሰጡ የሕግ ትርጉሞች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የውርስ ሕግ ያለው አተገባበር ከሕጉ ድንጋጌዎች እሳቤ እና አላማ ወጥቶ እና በእጅጉ እርቆ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች መሠረት ሲመራ ይታያል፡፡ እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የውርስ ሕግን አስመልከቶ የሰጣቸው የታተሙም ሆነ ያልታተሙ የሕግ ትርጉሞች ችሎቱ ራሱ የተቋቋመበትን ሕግን ተመሳሳይ በሆነ መልኩ እንዲተገበር የማድረግ አላማ በሚጻረር መልኩ እርስ በእርሳቸው ሲቃረኑ ይታያሉ፡፡
በውርስ ሕጉ የሚሰጡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ትርጉሞች እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ እና ወጥነት የሌላቸው የመሆናቸው ዋነኛው ምክንየት ተመሳሳይ የሆኑ ነገር ግን እንደአግባብነታቸው የተለያየ ትርጉም የሚሰጡ ቃላቶችን በተለያዩ የውርስ ሕጉ ክፍል የተገለጹ መሆናቸው ሲሆን ሌላኛው ምክንየት ደግሞ በውርስ ሕጉ ክፍል በራሳቸው ተፈጻሚነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች አግባብነት ከሌላው ከሌላኛው የውርስ ሕጉ የሕግ ክፍል ጋር ማቀላቀል ነው፡፡
የውርስ ሕጉ በራሱ ልክ እንደቤተሰብ ሕግ ሁሉ የራሱ የስነ-ስርዓት እና የአካሄድ መንገድ ያበጀ ሕግ ነው፡፡ የውርስ ሕጉ በአጠቃላይ በአምስት ምዕራፍ የተከፋፈለ ነው፡፡የመጀመሪያው ምዕራፍ የውርስ አስተላለፍን፤ ሁለተኛው ምዕራፍ ውርስን ስለማጣራት፤ ሶስተኛው ምዕራፍ የውርስ ክፍፍል፤ እና አራተኛው ምዕራፍ ውርስን ስለሚመለከቱ ስምምነቶችን የሚገዙ ናቸው፡፡ በእነዚህ የተለያዩ ምእራፎች ስር የሚገኙ ድንጋጌዎች በውርስ ሕግ ስር የሚገኙ እርስ በእራሳቸው ሊገናኙ የሚችሉባቸው ጉዳዮች ቢኖርም በዋናነት እንደ ባህሪያቸው እና ጸባያቸው በየራሳቸው ምእራፍ ስር ያሉትን ጉዳዮች እንዲገዙ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ሕጉ ሲተረጎም ይህን አንድነት እና ልዩነት ባገናዘበ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡
የአንዱ የሕግ ክፍል ድንጋጌ በሌላኛው የሕጉ ክፍል ድንጋጌ ለመተግበር የድንጋጌዎችን አላማ እና ይዘት እንዲሁም አንድነት እና ልዩነትን በአግባቡ መረዳት ይሻል፡፡ በውርስ ሕጉ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጣቸው የሕግ ትርጉሞች የውርስ ሕግ የተከፋፈለበትን፤ የተዋቀረበትን እና የሕጉን አቀራረጽ ከግምት ሳያስገባ ዝምድና እና ግንኙነት የሌላቸውን ምዕራፍ ድንጋጌዎች በሌላኛው ዝምድና እና ግንኙነት እንዲሁም አግባብነት በሌላቸው ምእራፎች ድንጋጌዎች ተግባራዊ በማድረግ እርስ በእርስ የሚቃረኑ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡
በሃገራችን በልምድ ያለው የውርስ መብት አተገባበር ተጨምሮበት በህብረተሰቡ ዘንድ በሕጉ አግባብ እየተተገበረ አይደለም፡፡ይህም ተጨመማሪ ምክንየትነት በፍርድ ቤቶች ጭምር የሕጉን አተረጓጎም አዛብቷል፡፡ በርግጥ የሰበር የሕግ ትርጉሞችን የጥራት ችግር የፍርድ ቤቶች ችግር ብቻ አድርጎ መስጠት ምክንየታዊ አይሆንም፡፡ ኃላፊነቱን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ አይወስድም፡፡ ህጎች ወጥ ተመሳሳይ እና ተገማች ሆነው በፍርድ ቤት እንዲተረጎሙ ሕግ አውጪው ህጎችን ግልጽ በማድረግ ሊያወጣ ይገባል ፡፡እንዲሁም ዳኞች ካለባቸው የጊዜ እጥረት እና የስራ ጫና አንጻር የህጎችን አተገባበር ማብራሪያ ጽሑፍ ከሙህራን ሊያገኙ ይገባል፡፡ ሙህራንም ተደራሽ እና ችግር ፈች የሆኑ ስራዎችን በመስራት እና የሰበር ውሳኔዎች በመተቸት ለውሳኔዎቹ ግብዓት ሊያበረክቱ ይገባል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አላማም በሰበር ችሎት የውርስ ሕግ አተረጓጎም ላይ ያለውን ችግር እና የመፍትሄ ሃሳቦች በማሳየት ወደ ፊት የሰበር የሕግ ትርጉሞች ተለውጠው ችግሮቹ ተፈትው የውርስ ክርክሮች ሕጉን መሠረት አድርገው ወጥ፣ ተገማች እና ተመሳሳይ መፍተሄ እንዲያገኙ አስተዋጽዖ ለማድረግ ነው፡፡
በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞችን እያነሳሁ ከሕጉ እና አንዱን የሰበር ችሎት የሕግ ትርጉም ከሌሎች የሰበር ውሳኔዎች እና ከሕጉ ጋር እያነጻጸርሁ ትችቱን እና የመፍትሄ ሃሳቡን አቀርባለሁ፡፡ በቅድሚያ በመግቢያዉ እንደተመለከተዉ አንዱ የችግሩ መንስዔ ምክንየት የሕጉ ቃላት አጠቃቀም በመሆኑ የዉርስ ሕጉ ቁልፍ ቃላቶችን እንመርምር፡፡
1) ስጦታ (donation) እና የኑዛዜ ስጦታዎች (legacy)
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግንቦት 21/2000 ዓ.ም በሰጠዉ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም፡-
"የቁም ስጦታ /donation intervivous/ እና የኑዛዜ ስጦታ(donation mortis causa/ የተለያዩ ናቸው። ሟች ከሞተ በኋላ የሚፈጸም የኑዛዜ የቁም ስጦታን የኢትዮጵያ ሕግ ስጦታ ነው ብሎ እውቅናና ጥበቃ አይሰጠውም። የኑዛዜ የቁም ስጦታዎች የሚገዙት ስለ ኑዛዜ በተደነገገው የሕግ ክፍል ነው። የኢትዮጵያ ሕግ ስጦታ ነው በማለት እውቅና እና ጥበቃ የሚያደርግለት የቁም ስጦታን ነው። አንድ ሰው ቤቱን በቁም ኑዛዜ ስጦታ ለወራሹ ቢሰጥ በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 መሠረት ቤቱ የቁም ኑዛዜ ስጦታ ላደረገላቸው በክፍፍል ወቅት እንዲደርሳቸው ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ እንጂ የተለየ ስጦታ መስጠቱን አያመለክትም።"
በሚል ትርጉም ሰጥቷል፡፡
ከውርስ ሕጉ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 912 እንደምንገነዘበው በውርስ ሕግ ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ (universal title legacy) እና ልዩ የኑዛዜ ስጦታዎች (singular title legacy) መኖራቸው ተገልጧል፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን በእግሊዘኛው (legacy) በሚል የተጠቀሰው ቃል በአማርኛ ስጦታ ተብሎ ስለተተረጎመ በእንግሊዘኛ (legacy) በሚል ተገልጾ በአማርኛ የኑዛዜ ስጦታ በሚል የተተረጎመው ቃል ከመደበኛው ስጦታ (donation) የተለየ ሃሳብ መሆኑን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሌጋሲ በአማርኛ ስጦታ በሚል ትርጉም የተሰጠው ቢሆንም legacy (የኑዛዜ ስጦታ) እና donation (ስጦታ) የተለያዩ ሃሳቦች ናቸው፡፡
Legacy (የኑዛዜ ስጦታ) በኑዛዜ ንብረት መስጠትን የሚያመላክት ሲሆን ኑዛዜ በመሆኑም ሟች ከሞተ በኋላ የሚፈጸም መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ donation (ስጦታ) ግን በጠቅላለው የሚፈጸምበት ሟች ከመሞቱ በኋላ ይሁን በፊት አንድን ንብረት በችሮታ ለሌላ መልቀቅን የሚመለከት ሰፊ ሃሳብ የያዘ ነው ፡፡ Legacy (የኑዛዜ ስጦታ) በ donation (ስጦታ) ስር የሚገኝ ንዑስ ሃሳብ ነው፡፡
ስለሆነም Legacy (የኑዛዜ ስጦታ) እና donation (ስጦታ) የሚሉ ቃሎችን ስጦታ ከሚል እኩል መልክት እንዳላቸዉ አድርጎ ማየት የለብንም፡፡
ታዋቂዉ የሕግ መዝገበ ቃላት ብላክስ ሎዉ legacy is a gift by will በሚል ተርጉሞ donate to give property without receiving consedration for the transfere በሚል ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ ብላክስ ሎዉ እንደተረጎመዉ ሌጋሲ ማለት በኑዛዜ የሚሰጥ የስጦታ አይነት ሲሆን ስጦታ ደግሞ በምላሹ ዋጋ ሳይቀበሉ ንብረትን ማስተላለፍ የሚመለከት ሰፊ ጥቅል ሃሳብ ነዉ፡፡
በተጨማሪም Legacy እና donation ስጦታ የሚል እኩል መልክት የማያስተላልፉ እና የሕጉም እሳቤ ይህ አለመሆኑን ከውርስ ሕጉ ከራሱ ድንጋጌዎች ጋር ማየት ተገቢነት አለው፡፡
በፍ/ብ/ህ/ቁ 1117 ወላጆች በህይወት እያሉ ንብረታቸውን ለተወላጆቻቸው ማካፈል እንደሚችሉ እና ይህም ስጦታ በቁም ስለሚደረጉ ስጦታዎች አፈጻጸም እንደሚገዛ ተመላክቷል ፡፡ ይህን የመሰለው ስጦታ በውርስ ሕጉ የተገለጸው legacy በሚል ሳይሆን donation በሚል ቃል ነው፡፡ ሰጪው ከሞተ በኋላ የሚፈጸም ስጦታ legacy ሲሆን ሰጪው በህይወት እያለ የሚፈጸም ሲሆን ደግሞ (donation) ይሆናል፡፡ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1067 (2) እና (3) የሁለቱን ስጦታዎች አይነት ልዩነት ይበልጥ እንገነዘባለን፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች legacy የሚለው ቃል ምንም እንኳ የኑዛዜ ስጦታ በሚል ቢገለጽም donation ከሚለው የጠበበ መሆኑን የሚያስመዘግበን ነው፡፡ ስለሆነም በውርስ ሕጉ (legacy) በሚል የተገጹ ቃሎችን ስጦታ donation ከሚለው ጋር አንድ እና ተመሳሳይ አድርጎ ማየት ስህተት ነው፡፡
2) የቁም ስጦታ/ስጦታ ሰጪዉ በህይወት እያለ የሚፈጸም ስጦታ /donation intervivous/ እና የኑዛዜ ስጦታ/ስጦታ ሰጪዉ ከሞተ በኋላ የሚፈጸም/ (donation mortis causa/
በዉርስ እና በስጦታ ክርክሮች ላይ አብዛኛዉን ጊዜ ሰነዱ የቁም ስጦታ ነዉ ወይስ የኑዛዜ ስጦታ ነዉ? አንድ ሰነድ የኑዛዜ ስጦታ መሆኑ እና የቁም ስጦታ መሆኑ የሚለየዉ እንዴት ነዉ? የሚለዉን መመርመር የዉርስ ሕጉን የበለጠ ለመረዳት እና በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ጠቃሚ በመሆኑ ልንመረምረዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፌ/ጠ/ፍ/ቤ/ሰ/ሰ/ች ሁለት የተለያዩ ዉሳኔዎችን የሰጠ መሆኑ ነገሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ሁለቱንም የሰበር የሕግ ትርጉሞች አንስተን ተገቢነታቸዉን እንዳስሳለን፡፡
የሰ/መ/ቁ.189118፡- ሟች መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገ የስጦታ ውል ለክርክር መነሻ የሆነውን ቤት ለአንደኛው ወራሽ ሰጥተው እሳቸው ከ28 ቀን በኋላ ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የስጦታ ውሉ እንዲፈጸም እየተጠየቀ ያለው ከሟቹ ሞት በኋላ ከሆነ ሟች አድርገዋል የተባለው የስጦታ ውል የሚፈጸመው ከሟች ሞት በኋላ ስለሆነ በሞት ምክንያት የተደረገ ስጦታ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በሞት ምክንያት የተደረገ ስጦታ ደግሞ ስለኑዛዜ የተነገሩት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች እንደሚሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2428 ድንጋጌ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም የግራ ቀኛቸውን ክርክር መነሻ በማድረግ አግባብነት ያላቸውን ስለኑዛዜ የተነገሩትን ድንጋጌዎች ማየቱ ተገቢ ነው፡፡
ሟች ካላቸው የውርስ ሀብት ውስጥ የመኖሪያ ቤታቸውን በስጦታ ውል ሰጥተው የቀራቸው የውርስ ንብረት እጅግ አነስተኛ ሆኖ ለሌሎች ወራሾች ከቀረው የውርስ ሀብት አንጻር ሲታይ የሚደርሳቸው የውርስ ሀብት ድርሻ እጅግ አነስተኛ ከሆነ ጉዳዩ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ.1123 ድንጋጌ አንጻር የሚታይ ይሆናል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ተፈጻሚነት ሲታይ አባት እና እናት ያላቸውን ሀብቶች ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ለልጆቻቸው እና ወደ ታች ለሚቆጠሩ ተወላጆቻቸው ለመስጠት እና ለማከፋፈል መብት ያላቸው ቢሆንም ይህ የስጦታ አከፋፈል ወደ ታች ከሚቆጠሩ ተወላጆች አንዱ ከሚደርሰው ከሩብ የበለጠ ጉዳት ደርሶበት እንደሆነ የስጦታ ክፍፍሉ ቀሪ ሊደረግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
ሌሎች ወራሾች ከሟች የውርስ ሀብት ምንም ያልደረሳቸው ሳይሆን የደረሳቸው ድርሻ ግን አነስተኛ ከሆነ እነዚህ የሟች ወራሾች ከሚደርሳቸው የውርስ ሀብት ድርሻ አነስተኛ ደርሷቸዋል ከሚባል በስተቀር ከሟች የውርስ ሀብት ምንም ድርሻ እንዳላገኙ ተነቅለዋል የሚያስብል አይደለም በሚል የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል። ነገር ግን በሚቀጥለው የሰበር መዝገብ ከዚሁ ጋር የማይስማማ ትርጉም እንደሚከተለው ተሰጥቷል፡፡
ሰ/መ/ቁ/196783፡- የስጦታ ውል አደራረግ በባህሪው ሁለት ዓይነት ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2428 ድንጋጌ ያሣያል። አንደኛው ስጦታ ሰጪው ከሞተ በኋላ የሚፈጸም ወይም የሚተላለፍ መብት/donation mortis causa/ የሚመለከት ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ የሥጦታ ውል የኑዛዜ ዓይነት ሆኖ ስለኑዛዜ የተደነገው ደንብ ተፈጻሚነት የሚኖረው ሲሆን ሌላኛው የሥጦታ ዓይነት የቁም ስጦታ ወይም ሰጪው በህይወት እያለ የሚፈጸም/donation inter vivos/ የሚባለው ዓይነት ነው። በሁለቱ መካከል የሚኖረው መሠረታዊ ልዩነት የመጀመሪያው ተፈጻሚነቱ ስጦታ ሰጪው ከሞተ በኋላ እንደመሆኑ ውሉ የሚታየው በኑዛዜ ዓይነት ሆኖ ጉዳዩም ስለኑዛዜ በተደነገገው ሕግ መሠረት የሚታይ ሲሆን ሁለተኛው ግን ስጦታ ሰጪው በሕይወት እያለ የሚፈጸም በመሆኑ በስጦታ ሰጪው እና በስጦታ ተቀባዩ መካከል የሚኖረው መብትና ግዴታ ስለሥጦታ ውል በተደነገገው ደንብ የሚገዛ መሆኑ ነው። አንድ የሥጦታ ውል ከሁለቱ በየትኛው ዓይነት ይፈረጃል የሚለውን ለመለየት የሚቻለው እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠን የፍ/ብ/ሕግ ቁጥር 2428 ነው። ከዚህ ድንጋጌ ይዘት መገንዘብ እንደሚቻለው ስጦታ ውሉ ላይ ስጦታው ተፈጻሚ የሚሆነው ስጦታ ሰጪው ከሞተ በኋላ መሆኑን የሚያመላከት ቃል መኖሩ ከተረጋገጠ የስጦታው ዓይነት ሰጪው ከሞተ በኋላ የሚፈጸም ወይም የሚተላለፍ በመሆኑ ልክ እንደኑዛዜ የሚታይ ይሆናል ማለት ነው።
የቤቱ ስመ-ሀብት ወደ ስጦታ ተቀባይ አለመተላላፉ ብቻውን የስጦታውን ዓይነት ስጪው ከሞተ በኋላ የሚፈጸም የሥጦታ ዓይነት ነው ሊያሠኝ የሚችል አይደለም። የስጦታ ውሉ የኑዛዜ ዓይነት ነው ለማለት የሚያሥችል ምክንያት ከሌለ ከውርስ መነቀል አለመነቀል ጉዳይ የሚመረመርበት አግባብ አይኖርም። ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም
ከእነዚህ ሁለት የሕግ ትርጉሞች መገንዘብ የሚቻለው በመጀመሪያው ውሳኔ ላይ ስጦታው የሚፈጸመው ሟች ከሞተ በኋላ ስለመሆኑ የሚያመላክት ቃል ከስጦታ ውሉ ላይ የለም፡፡ችሎቱ የገለጸው ስጦታው እንዲፈጸም የተጠየቀው ሟች ከሞተ በኃላ ከሆነ ስጦታው ሟች ከሞተ በኋላ እንደሚፈጸም (donation mortis causa / እንደሆነ ተደርጎ እንደሚወሰድ ሲሆን በሁለተኛው የችሎቱ ውሳኔ ላይ ግን የስጦታ ውሉ የእንዲፈጸም የተጠየቀበት ጊዜ ሳይሆን ስጦታ ሰጪው በህይወት እያለ የሚፈጸም /donation intervivous/ እና ሰጪው ከሞተ በኋላ የሚፈጸም (donation mortis causa/ የሚለውን ለመወሰን መታየት ያለበት ስጦታው እንዲፈጸም በተጠየቀበት ቀን ሰጪው ሞቶ ነበር ወይስ በህይዎት ነበር የሚለው ሳይሆን በስጦታ ውሉ ላይ ስጦታው ተፈጻሚ የሚሆነው መቸ እንደሆነ የሚያመላክት ቃል እና ይዘቱን በመመርመር ነው፡፡ የስጦታ ውሉ ስጦታ ሰጪው ከሞተ በኋላ ሚፈጸም መሆኑን የሚያመላከት ቃል መኖሩ ከተረጋገጠ የስጦታው ዓይነት ሰጪው ከሞተ በኋላ የሚፈጸም ወይም የሚተላለፍ በመሆኑ ልክ እንደኑዛዜ የሚታይ ይሆናል፡፡ የስጦታ ውሉ ተፈጻሚነቱ እንደተደረገ ወይም ሟች በህይዎት እያለ መሆኑን ካላሳየ የስጦታ ውሉ ሟች ከሞተ በኋላ የሚፈጸም (donation mortis causa / ይሆናል የሚል ነው።
ስለሆነም የመጀመሪያው የሕግ ትርጉም ሟች ከሞተ በኋላ እንዲፈጸም የተጠየቀ ስጦታ ሟች ከሞተ በኋላ የሚፈጸም (donation mortis causa / የስጦታ አይነት አድርጎ የተረጎመ ሲሆን ሁለተኛው የሕግ ትርጉም ግን የስጦታውን አይነት የሚወሰነው መቼ እንዲፈጸም ተጠየቀ በሚለው ሳይሆን የስጦታ ውሉ መቸ እንደሚፈጸም እንደሚያዝዝ የስጦታ ውሉ ይዘት ታይቶ ነው የሚሉ ስለሆኑ ሁለቱም የሚቃረኑ ወይም አብረው የሚሄዱ የሕግ ትርጉሞች አይደሉም፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 2428 ሰጪው ሲሞት ይፈጸማሉ ተብለው በተወሰኑት ስጦታዎች ላይ ስለ ኑዛዜ የተነገሩት ድንጋጌዎች ተፈጻሚዎች ይሆናሉ በማለት ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ድንጋጊ በግልጽ መገንዘብ እንደሚቻለው አንድ ስጦታ ሟች ከሞተ በኋላ የሚፈጸም (donation mortis causa) መሆኑ የሚለየው ስጦታው ሰጪው ሲሞት ይፈጸማል የሚል ከሆነ እንጂ ሰጪው ከሞተ በኋላ ስጦታው እንዲፈጸም ስለተጠየቀ ወይም ክስ የቀረበዉ ስጦታ ሰጪዉ ከሞተ በኋላ ስለሆነ አይደለም፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 2428 በሞት ምክንያት የተደረገ ስጦታ የሚል እርስ የተሰጠው ቢሆንም በእንደሊዘኛው donation mortis causa በሚል ስለተገለጸ ሰጪው ሊሞት ሲል ወይም ስጦታው ከተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰጪዉ ስለሞተ ብቻ ከሞት በኋላ የሚፈጸም ነው አያስብልም ፡፡በሞት ምክንያት የተደረገ ስጦታም ሌላ አይነት የስጦታ አይነት አለመሆኑን ከእንግሊዘኛው ትርጉም እንረዳለን፡፡
ስለሆነም አንድ ስጦታ ከሁለቱ የስጦታ አይነቶች የትኛው አይነት ስጦታ ነው ብሎ ለመለየት እንዲፈጸም የተጠየቀበት ጊዜ ሳይሆን መቸ እንደሚፈጸም የውሉ ይዘት ታይቶ የሚለይ በመሆኑ እና ሟች በህይወት እያለ ሊፈጸም የሚችል ስጦታ ሆኖ ነገር ግን ሟች ከሞተ በኋላ እንዲፈጸም መጠየቁ የስጦታውን አይነት ሟች ከሞተ በኋላ የሚፈጸም ስጦታ (donation mortis causa) ስለማያደርገው የመጀመሪያው የሰበር ትርጉም ቀሪ ሊሆን የሚገባው ነው፡፡
በአጠቃላይ የስጦታ ውል አደራረግ በባህሪው ሰጪው በህይወት እያለ የሚፈጸም /donation intervivous/ እና ሰጪው ከሞተ በኋላ የሚፈጸም (donation mortis causa / በሚል በሁለት ተከፍሎ የሚታይ መሆኑን ከፍ/ብ/ህ/ቁ 2428 የምንገነዘበው ነው፡፡ሁለቱ አይነት ስጦታዎች ህጋዊ ተቀባይነትን ለማግኘት የሚገዙባቸው ስርዓቶች የተለያየ ነው፡፡የመጀመሪያው የስጦታ አይነት ስጦታው የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን በግልጽ ኑዛዜ ፎርም መሠረት የሚገዛ ሲሆን ሁለተኛው አይነት ስጦታ የስጦታው ንብረት የሚንቀሳቀስም ይሁን የማይንቀሳቀስ ከኑዛዜ ሕግ አንጻር የሚታይ ነው ፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባው ሰጪው ሲሞት ይፈጸማሉ ተብለው የሚደረጉ ስጦታዎች በፍታብሄር ሕጉ ስለ ስጦታ በተደነገገው ምዕራፍ ስር ጉዳዩ የሚገዛበት የሕግ ክፍል ከመመላከቱ ውጪ እንደ ስጦታ የሚታይ ነው ወይ የሚለው ሊታይ ይገባዋል፡፡ ይህንን ሃሳብ በሚቀጥለው ክፍል እንመረምራለን፡፡
3) በውርስ ሊደርሰው ከሚገባው ከሩብ በላይ ማጣት ከውርስ መነቀል ስላለመሆኑ
ከፍ ብሎ በተራ ቁጥር 1 ባለው እርዕስ ስለ legacy (የኑዛዜ ስጦታ) እና donation (ስጦታ) ልዩነት እና አንድነት ያነሳሁት ከፍ ብሎ በመጀመሪያ በተጠቀሰው የሰበር ችሎቱ የሕግ ትርጉም ላይ ስጦታዉ የኑዛዜ ስጦታ መሆኑን ተቀብሎ እያለ፡-
"ስለሆነም ሟች ካላቸው የውርስ ሀብት ውስጥ የመኖሪያ ቤታቸውን በስጦታ ውል ሰጥተው ( በሞት ምክንየት በተደረገ ስጦታ) የቀራቸው የውርስ ንብረት እጅግ አነስተኛ ሆኖ ለሌሎች ወራሾች ከቀረው የውርስ ሀብት አንጻር ሲታይ የሚደርሳቸው የውርስ ሀብት ድርሻ እጅግ አነስተኛ ከሆነ ጉዳዩ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ.1123 ድንጋጌ አንጻር የሚታይ ይሆናል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ተፈጻሚነት ሲታይ አባት እና እናት ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ለልጆቻቸው እና ወደ ታች ለሚቆጠሩ ተወላጆቻቸው ያላቸውን ሀብቶች ለመስጠት እና ለማከፋፈል መብት ያላቸው ቢሆንም ይህ የስጦታ አከፋፈል ወደ ታች ከሚቆጠሩ ተወላጆች አንዱ ከሚደርሰው ከሩብ የበለጠ ጉዳት ደርሶበት እንደሆነ የስጦታ ክፍፍሉ ቀሪ ሊደረግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡---"
በሚል የሰጠው የሕግ ትንታኔ የኑዛዜ ስጦታን legacy እና ስጦታን (donation) ሃሳብን በመቀላቀል የተሰጠ ስለሆነ ነው፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 የሚገኘው የተከፋፈሉ ስጦታዎች (partition made by donations) በሚለው ክፍል ስር ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የሚያወራው ስለ ኑዛዜ ስጦታ (legacy) ሳይሆን ስለ ስጦታ (donation) ነው፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 መጎዳት ተግባራዊ የሚሆነው እና ተፈጻሚነቱ በኑዛዜ ስጦታ (legacy) ሳይሆን በስጦታ (donation) ላይ ነው፡፡ ስለሆነም በኑዛዜ ስጦታ (legacy) ላይ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (1) መሠረት ከሩብ በላይ ጉዳት ደርሶብኛል የስጦታ አከፋፈሉ ይቅር ብሎ ሊጠይቅ አይችልም፡፡ በኑዛዜ ስጦታ (legacy) ላይ ከሩብ በላይ ድርሻ አጥቻለሁ፤ ኑዛዜው ይሻርልኝ ወይም ክፍያው ቀሪ ይሁንልኝ የሚሉ ክርክሮች በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 መሠረት ተቀባይነት አግኝተው በርካታ የሰበር ውሳኔዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከሕጉ አቀራረጽ በኑዛዜ ስጦታ (legacy) ከሩብ በላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ ለተወላጅ ኑዛዜ ማድረግ ከፍታብሄር ሕግ ቁጥር 1123 እንደማይገናኝ የምንገነዘበዉ ሲሆን ተናዛዡም ተወላጁን እስካልነቀለው ድረስ ከሩብ በላይ ያለምክንየት ማሳጣት ሕጉ አይከለክለውም፡፡
በዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ እምነት በፍታሃብሄር ሕጉ መንቀል (disherison) ከኑዛዜ ስጦታ ጋር እንጂ ከድርሻ ማነስ (lesion) ጋር በምንም አይገናኝም፡፡ እንዲሁም ድርሻ ማነስ (lession) ከ(donation) ጋር እንጂ ከኑዛዜ ስጦታ (legacy) ጋር አይገናኝም፡፡ አንደኛው የሌላኛውን ውጤትም አይወስድም፡፡
ስለመነቀል የሚያደነግጉት የፍ/ብ/ህ/ቁ 937፤938፤939 እና ሌሎችም የመነቀል ሃሳቦች ተናዛዥ ንብረቱን ከሞተ በኋላ በኑዛዜ ስጦታ (legacy) የሚያስተላለፍበትን አግባብ የሚመለከቱ እንጂ ሟች በህይወት እያለ ስለሚፈጸም ስጦታ (donation) ወይም የስጦታ ክፍፍል (partition made by donation) የሚመለከቱ አይደሉም፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 መነሻ እና መሠረቱ ከዚሁ ድንጋጌ ከፍ ብሎ የተቀመጠዉ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1117 የተከፋፈሉ ስጦታዎች (partition made by donations) የሚለው የሕጉ ክፍል ነው፡፡ ይህ የሕግ ክፍልም ወላጆች በህይወት እያሉ ከመሞታቸው በፊት ንብረታቸውን ለተወላጆቻቸው በስጦታ (donation) ባከፋፈሉ ጊዜ በሚነሳ ክርክር ተፈጻሚ የሚሆን የሕግ ክፍል ነው፡፡ በዚህ የሕግ ክፍል የሚገዛው ስለ የስጦታ ውል (donation) ብቻ ነው፡፡ በዚህ የሕግ ክፍል እና በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 የተጠቀመው ቃል (legacy) በሚል ሳይሆን (donation) በሚል ነው፡፡
ወላጆች በህይወት እያሉ የሚፈጸም የስጦታ አከፋፈል በቁም ስለሚደረጉ ስጦታዎች (በመደበኛዉ የስጦታ የሕግ ክፍል ) በተደነገጉት ደንቦች መሠረት መፈጸም አለበት በሚል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1119 የተደነገገዉም የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 የስጦታ ዉልን እንጅ የኑዛዜ ስጦታን የማያሳይ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነዉ፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 ወላጆች በህይወት እያሉ ንብረታቸውን በስጦታ ባከፋፈሉ ጊዜ ተወላጆች ይህ የስጦታ ክፍፍል ባይደረግ ኖሮ ሊደረሰው ከሚገባው የውርስ ድርሻው ከ1/4ኛ በላይ እንዳያሳጡት ገደብ የሚጥል እንጅ ወላጅ የኑዛዜ ስጦታ (legacy) ሲያደርግ ተወላጁን ሊደርሰው ከሚገባው ከ1/4ኛ በላይ እንዳያሳጣው የሚከለክል ድንጋጌ አይደለም፡፡ ድንጋጌው የስጦታ ክፍፍል ባይኖር ኖሮ ይላል እንጂ ኑዛዜ ባይኖር ኖሮ አይልም፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ድንጋጌ አንድ አይነት ሃሳብ በሌለው በኑዛዜ ስጦታ (legacy) ላይ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይችልም፡፡ የዚህ የሕግ ክፍል ተፈጻሚነት በስጦታ ውል (partition by donation) ላይ ብቻ ነው፡፡ስለሆነም በኑዛዜ ስጦታ ጊዜ ሟች በኑዛዜዉ ተወላጅን ከሩብ በላይ እንዳያሳጣ የሕግ ገደብ የለበትም፡፡
ለትችት በተያዘው ከላይ በተገለጸው የሰ/መ/ቁ.189118 የሰበር ችሎቱ በአንድ በኩል ሟች ያደረጉት ኑዛዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2428 መሠረት ሟች ከሞተ በኋላ የሚፈጸም ስጦታ ነው ብሎ ወረድ ብሎ ግን የድርሻ መጠንን በሚመለከት ሲያትት
"-----በስጦታ ውል ሰጥተው የቀራቸው የውርስ ንብረት እጅግ አነስተኛ ሆኖ ለሌሎች ወራሾች ከቀረው የውርስ ሀብት አንጻር ሲታይ የሚደርሳቸው የውርስ ሀብት ድርሻ እጅግ አነስተኛ ከሆነ ጉዳዩ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ.1123 ድንጋጌ አንጻር የሚታይ ይሆናል፡፡"
በሚል የደረሰበት መደምደሚያ የፍ/ብ/ህ/ቁ.1117-1123 ተፈጻሚነት ሟች ከሞተ በኋላ በውርስ ማጣራት ታልፎ ለሚደረግ የኑዛዜ ስጦታ ( legacy ) ሳይሆን ሟች በህይወት እያለ ለተወላጆቹ አስቀድሞ በሚያደርገው ስጦታ ለሚያደረግ ክፍፍል መሆኑን ያላገናዘበ ነው፡፡
በእርግጥ በዚሁ መዝገብ ችሎቱ
"----የዚህ ድንጋጌ ተፈጻሚነት (የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ማለት ነው) ሲታይ አባት እና እናት ያላቸውን ሀብቶች ወደ ላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ለልጆቻቸው እና ወደ ታች ለሚቆጠሩ ተወላጆቻቸው ለመስጠት እና ለማከፋፈል መብት ያላቸው ቢሆንም ይህ የስጦታ አከፋፈል ወደ ታች ከሚቆጠሩ ተወላጆች አንዱ ከሚደርሰው ከሩብ የበለጠ ጉዳት ደርሶበት እንደሆነ የስጦታ ክፍፍሉ ቀሪ ሊደረግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡"
በሚል ጠቅሷል ፡፡
የዚህ የሕግ ትርጉም የችግሩ መንስዔ የሚመነጨው ወላጆች ለተወላጆች በፍ/ብ/ህ/ቁ 1117 መሠረት ክፍፍል የሚያደርጉት በኑዛዜ ስጦታ ነው ወይስ በስጦታ ማለትም ከመሞታቸው በፊት በሚፈጸም ስጦታ ነዉ ወይስ ከሞቱ በኋላ በሚፈጸመው የሚለውን አለመለየቱ ነው፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) የስጦታ ክፍያ እንዲቀር የሚደረገው ወደ ላይ የሚቆጠረው ስጦታ አድራጊው ወላጅ በሞተ በሁለት አመት ውስጥ እና የስጦታው መከፋፈል ከተደረገበት ቀን አንስቶ በአስር አመት ውስጥ ክስ ካልቀረበ በቀር ዋጋ የሌለው ይሆናል በሚል የይርጋ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ በግልጽ የምንገነዘበው የድንጋጌው ተፈጻሚነት ሟች በህይወት እያለ በስጦታ ባከፋፈለን መሠረት ሊደርሰኝ ከሚገባው 1/4ኛ ድርሻ በላይ ስላጣሁ በሚል የሚቀርብ ክስ ሟች ከሞተ በሁለት አመት ውስጥ ወይም በአማራጭ የስጦታ ክፍፍሉ ከተደረገ በአስር አመት ውስጥ መቅረብ እንዳለበት ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የስጦታ ክፍፍሉ ከተደረገ በኋላ የስጦታ ክፍፍል ያደረገው ሰው ክፍፍሉን ከፈጸመ በኋላ አስር አመት በህይወት ከቆየ ሊደረሰኝ ከሚገባው ከሩብ በላይ አጥቻለሁ ወይም ድርሻ አንሶኛል በማለት ክስ ለማቅረብ የጊዜ ገደብ የሚያልፍባቸው መሆኑን ነው፡፡
ይህን ክፍፍል እንደ ኑዛዜ ስጦታ ማለትም ሟች ከሞተ በኋላ እንደሚደረግ ድልድል ካየነው ሟች በኑዛዜ ለተወላጆቹ የኑዛዜ ስጦታ አድረጎ ኑዛዜውን ካደረገ በኃላ አስራ ሁለት አመት ቆይቶ ቢሞት ውርሱ ሲከፈት ልጆቹን በኑዛዜው ክፍፍል የተደረገው ሟች ከመሞቱ ከአስር አመት በፊት ስለተደረገ በይርጋ ታግዳችኋል ልንል ነውን? ኑዛዜ ግላዊ እና ሚስጥራዊ ከሆነበት ተፈጥሮው አውጥተን አስቀድሞ ለተወላጆች ያልተገለጸን እና የማያውቁትን ኑዛዜ ሟች ከሞተ በኋላ የሚከፈትን ኑዛዜ እና ከሟች መሞት በኋላ የሚያውቁትን ኑዛዜ ወላጃችሁ ድልድሉን ወይም ክፍፍሉን ካደረገ አስር አመት ሆኖታል ስለዚህ የመነቀል ጥያቄያችሁ ሟች በሞተ በወር ውስጥ ብታቀርቡም በይርጋ ታግዳችኋል ማለት ፍትሃዊ ነው? ይርጋው መቆጠር የሚጀምረው በመብታቸው መስራት ከጀመሩበት ሟች ከሞተበት ቀን ጀምሮ ነው እንዳንል ሟች ከሞተ በሁለት አመት ውስጥ ተብሎ ሌላ አማራጭ መሆኑ ተገልጧል፡፡ስለሆነም በኑዛዜ ስጦታ ከውርስ መነቀልን እና በስጦታ ክፍፍል አነስተኛ ድርሻ ማግኘትን አንድ አድርጎ በመውስድ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123`ን ተግባራዊ ማድረግ ከሕጉ ውጪ ነው፡፡
በአጭሩ በቁም ስጦታ ዉል በተደረገ ክፍፍል ተጎድቻለሁ ወይም ሊደረሰኝ ከሚገባዉ 1/4ኛ በላይ አጥቻለሁ የቁም ስጦታ ክፍፍሉ ይሻርልኝ በሚል አንድ ተወላጅ ክስ ለማቅረብ የግድ የስጦታ ሰጪዉን መሞት መጠበቅ የማይኖርበት መሆኑ በስጦታ ያከፋፈለዉን ተወላጅን ቸምሮ ሊከስ የሚችል መሆኑ በሌላ በኩል በኑዛዜ ተነቅያለሁ ኑዛዜዉ ይሻርልኝ የሚል ሰዉ የግድ ጥያቄዉን የሚያቀርበዉ ተናዛዡ ከሞተ በኋላ ወራሾችን ተከሳሽ በማድረግ መሆኑን መገንዘብ የሁለቱን ልዩነት ለመለየት ይረዳል፡፡
4 ) በኑዛዜ አነስተኛ ድርሻ ስለደረሰኝ (ከ1/4ኛ በላይ ስላጣሁ) ወይም በዝምታ በኑዛዜ ተነቅያለሁ ስለሆነም ኑዛዜው ይሻርልኝ የሚል ክስ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 (3) የተመለከተው አስር አመት ሊሆን የማይገባ ስለመሆኑ፡-
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በበርካታ መዝገቦች በኑዛዜ አነስተኛ ድርሻ ስለደረሰኝ በኑዛዜ ተነቅያለሁ ስለሆነም ኑዛዜው ይሻርልኝ የሚል ክስ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 (3) የተመለከተው አስር አመት ነው እንጂ የፍ/ብ/ህ/ቁ 994 አይደለም በሚል በተደጋጋሚ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን ከፍ ሲል እንደገለጽሁት የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ከመነቀል ጋር የሚያያዝ ሳይሆን ሟቾች በህይወት እያሉ ንብረታቸውን ለተወላጆቻቸው ባከፋፈሉ ጊዜ የሚፈጸምበትን ሁኔታ ስለሚመለከት ከውርስ በዝምታ ተነቅያለሁ የሚል ወይም ድርሻ ስላነሰኝ በተዘዋዋሪ መንገድ ተነቅያለሁ የሚል ክስ ወደ ፊት በምገልጸው ምክንየት እንደየሁኔታው በፍ/ብ/ህ/ቁ 993 እና 994 ወይም በፍ/ብ/ህ/ቁ 1677 እና 1845 መሠረት አስር ዓመት ይሆናል እንጂ በፍብ/ህ/ቁ 1123(3) መሠረት አይገዛም፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) ያስቀመጠው አማራጭ ሁለት የይርጋ ጊዜዎችን ነው፡፡ የመጀመሪያው ሟች ከሞተ ጀምሮ እስከ ሁለት አመት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ክፍፍሉ ከተፈጸመ በአስር አመት ውስጥ ነው፡፡ይህ ድንጋጌ ስለ ስጦታ (donation) እንጂ ስለኑዛዜ ስጦታ (legacy) የማያወራ በመሆኑ የኑዛዜ ስጦታ (legacy)`ን መነሻ ለሚያደርግ ጽንሰ ሃሳብ ከውርስ መነቀልንም ይመለከታል ሊባል አይቻልም፡፡ እንዲሁም አንድ ተወላጅ የስጦታ ክፍፍሉ እንዲሰረዝ ክስ ለማቅረብ የስጦታ አድራጊዉን ሞት መጠበቅ አይጠበቅበትም፡፡ ይልቁንም በስጦታ ንብረቱን ያከፋፈለዉን ወላጁን ጭምር ሊከሰዉ ይችላል፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) የኑዛዜ ስጦታን ይመለከታል ካልን ከውርስ የመነቀሉ ጉዳይ የይርጋ ጊዜዉ ሟች ከሞተ በኋላ በሁለት አመት ይርጋ ነው ብለን እንደገና ደግሞ በአማራጭ ሟች ከሞተ ጀምሮ በአስር አመት የሚታገደው ክፍፍል ከተደረገ ጀምሮ ነው ሊባል ነው፡፡ ምክንየቱም ስለ ኑዛዜ መሻር የምናወራዉ ሟች ከሞተ በኋላ ብቻ ነዉ፡፡
የኑዛዜ ስጦታ ክፍፍሉ ተደርጎ እስከ አስር አመት ሟች በህይወት ቢቆይ የመነቀል ጉዳይ ለማንሳት ያለው ጊዜ ሟች ከሞተ ጀምሮ እስከ ሁለት አመት ነው የሚል አንድምታም ይኖረዋል፡፡
እንደሚታወቀው ኑዛዜ የሚከፈተው እና ይፋ የሚሆነው ሟች ከሞተ በኋላ ውርሱ ተከፍቶ ማጣራት ሲጀመር ነው፡፡ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 965 እንደምነገነዘበው ኑዛዜ የሚከፈተው ሟች ከሞተ በኃላ በ40ኛው ቀን ሲሆን ኑዛዜው ከዚህ ቀን በኃላ ከተገኘ ከዚህ ቀን ዘግይቶ ምናልባትም ሟች ከሞተ ከሁለት አመት በኋላ ሊከፈት ይችላል፡፡ ስለሆነም ተከፍቶ ባልታወቀ ኑዛዜ ላይ ሟች ከሞተ በኋላ ከ2 ዓመት በኋላ ክስ ለማቅረብ በይርጋ ታግደሃል ሊባል አይገባም፡፡ ሁለተኛ ከውርስ የመነቀል ጉዳይ ሟች ከሞተ በኋላ በሁለት አመት ካልቀረበ በቁጥር 1123 (3) መሠረት በሁለት አመት ይታገዳል ካልን ትልቅ እና ሰፊ ለሆነው በፍ/ብ/ህ/ቁ 974 (2) እንደተመለከተው በውርስ ማጣራት ጊዜ ኑዛዜን ወይም ድልድልን ለመቃወም ሟች ከሞተ እስከ አምስት አመት የይርጋ ጊዜው እንደሆነ ካስቀመጠው ዘመን ያነሰ ጊዜ ሕግ አውጭው ያስቀምጣ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሶስተኛ የውርስ መነቀል ጉዳይ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) የተቀመጠው የሁለት አመት እና የአስር አመት ጊዜ ውስጥ የቱ እንደሚመረጥ እና ተግባራዊነቱ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ከሞተ በሁለት አመት እና ክፍፍል ከተደረገ በ10 ዓመት ውስጥ የተባለው ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ አራተኛ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) ላይ በመጎዳት ሊደርሰው ከሚገባው ከሩብ በላይ አጥቻለሁ በሚል የሚቀርበው ክስ አይነት እና የጊዜ ገደቡ የተቀመጠለት ጥያቄ በእንግሊዘኛው rescission የሚል ሲሆን በአማርኛው አከፋፈሉ እንዲቀር በሚል የተገለጸ ስለሆነ ቃሉ አስቀድሞ የተደረገ ክፍፍል መኖሩን ታሳቢ ያደረገ እንጂ ሰጪው ከሞተ በኋላ የሚደረግን የኑዛዜ ስጦታ ወይም የኑዛዜ ስጦታ ክፍፍልን የሚመለከት አለመሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡
5) በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 የተመለከተው የክፍያ ደንብ ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1117-እስከ-1123 ከተመለከቱ ድንጋጌዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለው ስለመሆኑ፡-
አንድ ተወላጅ አንድን ንብረት ለተወላጁ መስጠቱ እንደ ክፍያ ደንብ እንጂ እንደ ኑዛዜ ስጦታ እንደማይታይ በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 የተገለጸው መርህ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1117 እና 1123 እንደተገለጸው ወላጆች በህይወት እያሉ ንብረታቸዉን በስጦታ ባከፍፈሉበት ጊዜ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ በመግቢያዉ እንተገለጸዉ ለችግሩ ሌላው መንስዔ ተመሳሳይ መልክት የሌላቸውን አንድ አይነት ቃላቶት ለተለያዩ ሃሳቦች ሕጉ መጠቀሙ ነው፡፡
በፍ/ብ/ህ/ቁ.1117 በአማርኛው የተከፋፈሉ ስጦታዎች (partition made by donation) በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 ደግሞ የኑዛዜ ስጦታና የክፍያ ደንብ (legacies and rule of partition) በሚል ተቀምጧል፡፡ እንግሊዘኛው ሌሎች ገላጭ ቃላቶች እንደተጠበቁ ሆነው ለሁለቱም የተለያዩ ሃሳቦች partition በሚል አንድ ቃል ገልጧል፡፡ አማርኛው ግን የተከፋፈሉ ስጦታዎች እና የክፍያ ደንብ በሚል በተለያዩ ቃላቶች ነው የገለጻቸው፡፡ከአማርኛው ከስሙ እንደምንረዳው የተከፈፈሉ ስጦታዎች የሚለው በተለይ የተከፋፈሉ የሚለው ቃል ያለፈ ነገርን አስቀድሞ ተደረገውን የሚያመላከት በመሆኑ ሟች በህይወት እያለ ውርሱ ከመከፈቱ በፊት የተደረጉ ስጦታዎችን እንደሚመለከት የሚያሳይ ነው፡፡የክፍያ ደንብ ማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ በጥንቃቄ ከሕጉ ላይ እንፈትሽ፡፡
በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 ሟች ተቃራኒ ሃሳብ በኑዛዜው ቃል ከሌለ በቀር ለተወላጁ አንድን ንብረት ወይም ከውርስ ሃብቱ አንድን ድርሻ መስጠቱ ተራ የሆነ የክፍያ ደንብ እንጂ እንደ ኑዛዜ ስጦታ አይቆጠርም ይላል፡፡ የሰበር ችሎቱን ጉዳዩን ወደ ፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 የመሰደው የዚህ ድንጋጌ አገላለጽ ስለሆነ በዚህ አንቀጽ የክፍያ ደንብ (rule of partition) ምንድን ነው? በየትኛው የሕጉ ክፍል የሚገኝ ሀሳብ ነው? ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ጋር ተመሳሳይ ነው ወይ? የሚለውን እንመርምር፡፡
የክፍያ ደንብ (rule of partition) የሚባለው ሃሳብ የሚመጣው ውርስ ተከፍቶ፤ ውርስ ተጣርቶ፤ የውርስ እዳው እና የልዩ ኑዛዜ ተጠቃሚዎች ክፍያ ተከፍሎ፤ የውርስ ሃብቱ ተሰብስቦ እና ወራሾች ተለይተው ከተጠናቀቀ በኃላ ለወራሾች የሚተርፈው ገንዘብ ተለይቶ ተጠናቆ ይህን የተጣራ ተራፊ የውርስ ሃብት ወራሾች እንዴት እንደሚከፋፈሉት የሚያሳይ የውርስ ንብረት ክፍፍል ስርዓቶችን የሚመለከት ነው ፡፡ እነዚህ የክፍያ ደንቦች (rule of partition) በፍትሃብሄር ሕጉ ቁጥር 1060 እስከ 1096 ያሉት ያሉት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች የውርስ ሃብቱ ተጣርቶ ተጠናቆ ውርሱ ከተዘጋ በኋላ በማጣራቱ ሂደት ለወራሾች የሚተርፉት ንብረቶች በወራሾች መካከል በስምምነት፤ በኑዛዜው መሠረት፤ ንብረቱን አስገምተው በማካካስ፤ በእጣ ድልድል፤ በአይነት፤ በስምምነት በመሸጥ፤ በሃራጅ በመሸጥ ለወራሾች ሊካፈፈሉ እና ሊደለደሉ የሚችሉ መሆኑን በማመላከት የውርስ ሃብት ክፍፍል መፈጸሚያ መንገዶችን ወይም ስርዓቶችን የሚደነግጉ የክፍያ ደንቦች (rule of partition) ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በተለይ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1083 ክፍያው የሚፈጸመው ሟች ባደረገው ኑዛዜ መሠረት ሲሆን ኑዛዜ ከሌለ በሕጉ በተመላከቱ የክፍያ ደንቦች ይፈጸማል በማለት ይደነግጋል፡፡ እንዲሁም የፍ/ብ/ህ/ቁ 980 የክፍያ ደንብ ስለማቋቋም በሚል እርስ ስር ውርሱ እንዴት እንደሚከፋፈል የትኛው የውርስ ሃብት ለማን እንደሚሆን ድልድል እንደሆነ አስቀምጧል፡፡
እነዚህን ድንጋጌዎች ከቁጥር 913 ጋር ስናያቸዉ ተቃራኒ አገላለጽ ከሌለ በስተቀር አንድ ወላጅ ለተወላጁ አንድን ንብረት ወይም ከውርስ ሃብቱ አንድን ድርሻ መስጠቱ ተራ የሆነ የክፍያ ደንብ እንጂ እንደ ኑዛዜ ስጦታ አይቆጠርም የሚለው ወላጅ ለተወላጁ በኑዛዜ አንድን ንብረት ወይም ድርሻ መስጠቱ ውርሱ ተጣርቶ ከተዘጋ በኋላ ተራፊ የውርስ ሃብቶች ለወራሾች ሲከፋፈሉ ወይም ለጊዜውም ድልድል ሲደረግ የክፍያ ደንቦች (rule of partition) ሲተገበር እነዚህ ንብረቶች ለተባሉት ተወላጆች እንዲደርሳቸው በኑዛዜ ማዘዛቸውን ያሳያል እንጂ የኑዛዜ ተጠቃሚ የሆኑ ልጆች እነዚህ በኑዛዜ የተደለደሉላቸው ንብረቶች ከግምት ሳይገቡ ቀሪውን የውርስ ሃብት ከሌሎች ወራሾች ጋር እኩል ልካፈል ማለት አይችሉም ማለት ነው፡፡
በፍ/ብ/ህ/ቁ 1086 ላይ የድርሻዎቹ አመዳደብ የሚለው rule of partition in kind በሚል በእንግሊዘኛ ተተርጉሞ በግልጽ መገኘቱም የክፍያ ደንብ (rule of partition) በሚል በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 የተገለጸው ይህን የሕግ ክፍል እንጂ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1117-1123 ያለውን እንደማይመለከት የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ሌላው የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123`ን ከፍ/ብ/ህ/ቁ 913 የምናገኛኝበት ምክንየት የውርስ ጉዳይ መነሳት የሚችለው እና የውርስ ሕጉ ተግባራዊነት ተናዛዙ ከሞተ በኋላ ብቻ ነው ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ ሁል ጊዜ ትክክል አይደለም፡፡ የእኛ ሃገር የፍታብሄር ሕግ የተቀዳበት የፈረንሳይ የፍታብሄር ሕግ የቁም ስጦታን እና የኑዛዜ ስጦታን በውርስ ሕጉ ክፍል በመጽሃፍ 3 የንብረት ማግኛ መንገዶች በሚለው ስር በእርእስ 3 ደንግጓል፡፡ በዚህም የፈረንሳይ ፍታብሄር ሕግ በእኛ የፍሃብሄር ሕግ ቁጥር 1117 የተከፋፈሉ ስጦታዎች (partition made by donation) የሚለውን (Distributions made by Father, Mother, or other ancestors, among descendants ) በሚል ነው የሚያስቀምጠው፡፡
በዚህ የፈረንሳይ የፍታብሄር ሕግ (Distributions made bay Father,Mother,or other ancestors, among descendants ) ተብሎ የተቀመጠው ሃሳብ በእኛ የፍትሃብሄር ሕግ የተከፋፈሉ ስጦታዎች (partition made by donation ) የሚለው ሃሳብ ስለመሆኑ በግልጽ ድንጋጌዎቹ የሚናገሩት ነው፡፡ ለማሳያ ያህል የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123(3) በስጦታው ሊደርሰው ከሚገባው ከ1/4ኛ በላይ ሊያጣ አይገባም የሚለው ከላይ በተገለጸው የፈረንሳይ የፍታብሄር ሕግ የተወሰደ መሆኑን የፈረንሳይ የፍትሃብር ሕግ አንቀጽ ይህን አስመልክቶ
"The distribution made by ancestor may be impeached for cause of wast more than a fourth"
በሚል ከደነገገዉ የምንረዳዉ ነዉ፡፡
የእኛ የፍትሃብሄር ሕግ ከአንቀጽ 1117-1123 ያሉ ድንጋጌዎችን ከፈረንሳይ የፍትሃብሄር ሕግ ሃሳቡን ሲወስድ Distributions የሚለውን partition በሚል ቀይሮታል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም የፍትሃብሄር ህጎች “--made by---" ስለሚሉ ያለፈ መሆኑን ስለሚያሳዩ ክፍፍሉ በስጦታ ውል አስቀድሞ የተደረገ እንጂ ገና በሚከፋፈል የውርስ ንብረት ላይ እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ፡፡ የእኛ የፍትሃብሄር ሕግ 1085 ጀምሮ ሟች በህይወት እያለ ወራሾች በስጦታ ያገኘዉ ንብረት በሕጉ በተቀመጡት በስተቀሮች ዉጪ ሊመልሱ እንደሚገባ መደንገጉ በዉርስ ሕጉ ክፍል ስለ ስጦታ ጭምር የተካተተ ሃሳብ መኖሩን የሚያሳይ ነዉ፡፡
ሌላዉ መጎዳት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ መሠረታዊ ምንጩ የውርስ ሳይሆን የውል ሕግ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ በውርስ ሕጉ ቁጥር 1117 የተካተተበት ዋነኛ ምክንየት ከቁጥር1117-1123 ያሉ ጽንሰ ሃሳቦች ሟች በህይወት እያለ በስጦታ ውል መሠረት የሚያደርገውን የስጦታ ክፍፍል የሚመለከት እና ስጦታ አድራጊውም በህይወት እያለ እስከ አስር አመት በውል የተደረገውን የስጦታ ክፍፍሉን መቃወም የተፈቀደዉ ኑዛዜ ባለመሆኑ ግላዊ ባህሪ የሌለው እና ተቀባዮች ሊቃወሙት የሚችሉት፤ እንዲሻሻል ሊጠይቁበት የሚችሉት ውል ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ይህም የሕጉ አስተሳሰብ ነገሩን ትኩረት ሰጥተን እንዳንረዳው አድርጎናል፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 913 ላይ የተጠቀሰው የክፍፍል ደንብ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 የተመለከተው መከፋፈል ጋር አንድ አይነት እንዳልሆነ የማያወላዳ ተጨማሪ ምክንየት አቀርባለሁ ፡-
- በፍ/ብ/ህ/ቁ 904 እና 905 የኑዛዜዎች መሻር እና ውድቅ መሆን በሚለው ክፍል ኑዛዜ ከተደረገ በኋላ ልጅ ከተወለደ ኑዛዜዎች ፈራሽ ይሆናሉ፡፡ ዳኞች በልዩ ሁኔታ ኑዛዜውን ካላፈረሱት ለተወለደዉ ልጅ ቢያንስ እጅግ ቢያንስ ሶስት እሩብ ማግኜት አለበት ይላል፡፡ በሌላ በኩል የፍ/ብ/ህ/ቁ 1121 እና 1123 ስጦታው ከተደረገ በኋላ የተወለደ እንደሆነ ሰጪው በሞተ ጊዜ የተተወው ልጅ የስጦታ አከፋፈሉ እንዲፈርስ መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ከክፍፍሉ የተወለደው ወይም የተተወው ልጅም ከ1/4ኛ በላይ ሊያጣ እንደማይገባ ይደነግጋል፡፡ ሕጉ በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 የተመላከተው ክፍፍል ደንብ በፍ/ብ/ህ/ቁ ከ1117 እስከ 1123 የተመለከተው ነው ብሎ ካሰበ የስጦታውን እጣ ፈንታ አስመልክቶ ልጅ በሚወለድበት ጊዜ ለምን ሁለት ጊዜ ይደነግጋል?
- የፍ/ብ/ህ/ቁ 1105 እና 1106 በክፍፍል ስርዓቱ ንብረቱ በተሳሳተ መንገድ ተገምቶ ከሶስት እሩብ በታች የሆነ አነስተኛ ድርሻ የደረሰው ወራሽ ውርሱ በተከፋፈለ በ3 ዓመት ውስጥ ክፍፍሉ እንዲቃና ለመጠየቅ እንደሚችል ይደነግጋል ፡፡ በሌላ በኩል የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ጉዳቱ ሊደርሰው ከሚገባው ከሩብ በላይ ጉዳት ከሆነ የስጦታ ክፍፍሉ እንዲቀር ሟች በሞተ በሁለት አመት ውስጥ እና የስጦታ ክፍፍሉ በተደረገ አስር አመት ውስጥ ጉዳቱን ለማስተካከል መተየቅ እንደሚችል ደንግጓል፡፡ በፍ/ብ/ህ/ቁ 913 የተመላከተው የክፍያ ደንብ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ከተመላከተው ጋር ተመሳሳይ ነው ከተባለ ሕጉ ለምን በክፍፍል ጉዳት የደረሰበት ሰው እንዲያቃና ሁለት ቦታ ላይ መግለጽ ለምን ያስፈልገዋል? ለምንስ ለአንድ አይነት ጉዳይ የተለያየ የይርጋ ጊዜ ገደብ ያስቀምጣል?
እነዚህ ድንጋጌዎች የክፍያ ደንብ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ከተመላከተው የስጦታ ክፍፍል የተለዩ እና በተለያየ ሕግ የሚገዙ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የፍ/ብ/ህ/ቁ 913`ን በዝርዝር ያየሁት ሰበር ችሎቱ ይህን ድንጋጌ በኑዛዜ ስጦታ ወይም በክፍያ ደንብ ክርክር ጊዜ ወደ ቁጥር 1123 ለመሸጋገር ስለሚጠቀምበት እና የችግሩ ዋና ምንጭ በመሆኑ ነው፡፡
6) በተዘዋዋሪ መንገድ ከውርስ መነቀል ምንድን ነው?መነቀል ከውርስ ሃብቱ ምንም አለማግኘት ነው ወይስ ድርሻ ማነስ ነው?
ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ ሰበር ችሎቱ በሰ/መ/ቁ.189118
"---ሌሎች ወራሾች ከሟች የውርስ ሀብት ምንም ያልደረሳቸው ሳይሆን የደረሳቸው ድርሻ ግን አነስተኛ ከሆነ እነዚህ የሟች ወራሾች ከሚደርሳቸው የውርስ ሀብት ድርሻ አነስተኛ ደርሷቸዋል ከሚባል በስተቀር ከሟች የውርስ ሀብት ምንም ድርሻ እንዳላገኙ ተነቅሏል የሚያስብል አይደለም፡፡"
በሚል ያሰፈረው አገላለጽ ነው፡፡
ከላይ እንደገለጽሁት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 በስጦታ ክፍፍል ሊደርስ ከሚገባው ከሩብ በላይ ማጣት ወይም መጎዳት ከውርስ መነቀል ጽንሰ ሃሳብ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ የሰበር ችሎቱ አንድ ጊዜ መነቀል ማለት ምንም ድርሻ አለማግኘት እንጂ ድርሻ ማነስ አይደለም፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ምንም አለማግኘት ብቻ ሳይሆን ድርሻ ማነስም በተዘዋዋሪ መንገድ መንቀል ነው በሚል እርስ በእርሱ የሚቃረኑ የሰበር ውሳኔዎች ስላሉ እነሱን ማየት ተገቢ ነው፡፡
ቀጥሎ በማነሳቸዉ የሰበር የሕግ ትርጉሞች ላይ በአንዳንዶቹ ላይ ኑዛዜው መነቀል አስከትሏል የሚባለው ከቀሪው የውርስ ሃብት ጋር ተነጻጽሮ አነስተኛ ድርሻ ሲደርሰው ነው፤ በኑዛዜ ሊደርሰው ከሚገባው 1/4ኛ ማጣት እና መነቀል እኩል ነዉ፤ መጎዳት ወይም ከ1/4ኛ በላይ ማጣት ከመነቀል የተለየ ነዉ፤ በኑዛዜ እጅግ አነስተኛ ገንዘብ ማግኘት የድርሻ ማነስ ሳይሆን መነቀል ነው፤ ከውርስ መነቀል ማለት ከውርስ ሃብት ምንም አይነት ድርሻ አለማግኘት እንጂ አነስተኛ ድርሻ ማግኘት ስላልሆነ ከሌሎች ወራሾች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ድርሻ ተሰጥቶኛል የሚል ወገን ከውርስ ተነቅያለሁ ሊል አይችልም የሚሉ ናቸዉ፡፡ እነዚህን የሰበር የሕግ ትርጉሞች በዝርዝር እንመልከታቸዉ፡፡
ሰ/መ/ቁ 57836፡- በኑዛዜ የሚከናወኑ ተግባሮች የኑዛዜ ስጦታ (legacy) ወይም የክፍያ ደንብ (rule of partiton) ሊሆኑ ይችላሉ። በመርህ ደረጃ አንድ ሰው ከውርስ ሀብቱ መካከል አንድን ንብረት ለወራሾቹ መስጠቱ የኑዛዜ ስጦታ አያሰኘውም። ይህን አይነት ስጦታ ሕጉ የሚቀበለው እንደ አንድ የክፍያ ደንብ ነው። በመሆኑም አንድ አውራሽ ለወራሹ አንድ ንብረት ቢናዘዝለት የኑዛዜው አፈጻጸም የስጦታ (legacy) አፈጻጸም በመከተል ሳይሆን የክፍያ ደንብ (partition) በመከተል የሚከናወን ነው። ሆኖም በኑዛዜው ላይ የሚሰጠውን ክፍያ መጠን በመገለጹ ብቻ ሁልጊዜ የክፍያ ደንብ ነው ሊባል የሚቻል አይሆንም። የተሰጠው የንብረት መጠን ከሟቹ የውርሰ ሀብት ግምት ጋር ታይቶ ውጤቱም በዚህ እረገድ መለየት አለበት። በሌላ አነጋገር ሟቹ በኑዛዜው ላይ የሚያሰፍረው የንብረት መጠን ከሟቹ የውርሰ ንብረት መጠን ጋር እየታየ የመነቀል ጉዳይ ነው ወይስ የክፍያ ማነስ? የሚለው ነጥብ የሚለይ ይሆናል። የባልና ሚስት የጋራ በሆነ ንብረት ላይ አንደኛው ወገን በኑዛዜው ንብረቱን በሰጠ ጊዜ በኑዛዜው ፍርስ መሆን አለመሆን ላይ ተናዛዡ በንብረቱ ላይ መብት ያለው መሆን አለመሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ንብርቱ የጋራ መሆን አለመሆኑ ላይ የነበረው ግንዛቤ ውጤት ይኖርዋል። ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1047 (1) እና (2) መገንዘብ የሚቻለው ኑዛዜ ፍርስ ሊሆን የሚችለው ተናዛዡ ስጦታ ባደረገበት ንብረት ላይ መብት እንደሌለውና ይህንም ያውቅ እንዳልነበር ሲታወቅ ብቻ ነው። በኑዛዜ የተሰጠን ስጦታ የክፍያ ደንብን በመከተል ለመፈጸምና እና የክፍያ ማነስ ነው በማለት በክፍያ ደንብ ድንጋጌዎች ለማስተካከል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1117 እና 1123 ጥምር ንባብ መሠረት ኑዛዜ የተደረገለት ሰው የሟቹ ተወላጅ ወይም ወደ ላይ የሚቆጠር ዘመድ መሆን አለበት። “ ልጅ ትዳር ከመሠረተች በኋላ አልተንከባከበችኝም ስታመም አልጠየቀችኝም” የሚል ምክንያት ከውርስ ለመንቀል የሚያስችል በቂና ህጋዊ ምክንያት አይደለም። ቅጽ/11
ሰ/መ/ቁ.235837፡- አንድ ኑዛዜ ወደታች የሚቆጠር ተወላጅን ከውርስ የነቀለ ነው ሊባል የሚችለው በዝምታ ወይም በሕግ ተቀባይነት የሌለውን ምክንያት በመጥቀስ ምንም ድርሻ ሳይሰጥ ወይም በውጤት ምንም ድርሻ እንዳልተሰጠ የሚያስቆጥር የድርሻ መጠን በኑዛዜው ሲጠቀስ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁጥር 938 ድንጋጌ ይዘት መገንዘብ ይቻላል። እንደዚሁም አባት ወይም እናት ወይም ሌሎች ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ለልጆቻቸው ወይም ወደታች ለሚቆጠሩ ተወላጆች ሀብታቸውን ለመስጠት ወይም ለማከፋፈል እንደሚችሉ እና በስጦታው አከፋፈል ውስጥ ተቃራኒ ቃል ከሌለ በስተቀር ወደታች ከሚወለዱ ወራሾች አንዱ ሊደርሰው ከሚገባው ድርሻ ከ1/4ኛ በላይ ጉዳት ደርሶበት ከሆነ የስጦታ አከፋፈሉ እንዲቀር መጠየቅ እንደሚችል በፍ/ሕ/ቁጥር 1117 እና 1123/1 ተመልክቷል። ኑዛዜው ተወላጅን ያለምክንያት ከውርስ ሐብት የነቀለ ነው ወይም ከ1/4ኛ በላይ ጉዳት ያደረሰ ነው የሚባል ከሆነ ውጤቱ የኑዛዜ ክፍፍሉ ቀሪ ሆኖ ኑዛዜ ሳይኖር ሊያገኝ የሚችለውን ድርሻ እንዲያገኝ ማድረግ መሆኑንም ከእነዚሁ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች ይዘት መረዳት ይቻላል። በኑዛዜ ከውርስ ሐብት መነቀል ወይም ከ1/4ኛ በላይ ጉዳት መድረሱ ሊታወቅ የሚችለው በኑዛዜው የድርሻ መጠን ተጠቅሶ ውጤቱ ግን መንቀል መሆኑን ወይም ከ1/4ኛ በላይ ጉዳት መድረሱ ሊረጋገጥ የሚችለው ኑዛዜውን በማየት ብቻ ሳይሆን የውርስ ሐብቱ ተጣርቶ ሲቀርብ ከአጠቃላይ የውርስ ሐብቱ አንጻር ተነቅያለው ወይም ጉዳት ደርሶብኛል ለሚለው ተወላጅ በኑዛዜ የተሰጠውን የድርሻ መጠን በማገናዘብ ነው።የውርስ ሐብቱ ተጣርቶ ተጎዳሁ ወይም ተነቀልሁ ለሚለው የደረሰው ለሌሎች ከተሰጠው ጋር ተነጻጽሮ ሳይታይ በኑዛዜው ላይ ሟች ድርሻ መስጠታቸውን ብቻ በመመልከት ከኑዛዜ አልተነቀሉም ወይም በኑዛዜው ከ1/4ኛ በላይ ጉዳት አልደረሰባቸውም ሊባል አይችልም። ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ/ም
ሰ/መ/ቁ 55648፡- ሟች በኑዛዜው ተወላጁን ስለአረዳኝ እና ስላልጠየቀኝ በሚል ምክንያት ከውርስ ሀብቱ ሊደርሰው ከሚችለው 1/4ኛ ድርሻ በላይ ሊያሳጡት አይገባም። የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (1) እና 938(2)”ን በጣምራ በመተርጎም መረዳት የሚቻለው ሟች የተወሰኑት ተወላጆቻቸውን ስላረዷቸውና ስላልጠየቋቸው በውርስ ከሚደርሳቸው ድርሻ ሩብ በላይ እንዲያጡ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት አይደለም። በመሆኑም ተናዛዡ በቂ ባልሆነ ምክንያት ተወላጁን ሊደርሰው ከሚገባው ከ1/4ኛ በላይ የውርስ ድርሻ የከለከለው ከሆነ እና ለሌላኛው ተወላጅ ከሩብ በላይ የሆነውን ንብረቱን እንዲተላለፍለት ኑዛዜ አድርጎ ከተገኘ ኑዛዜው ተጎዳሁ የሚለውን ተወላጅ እስከ 1/4ኛ ድረስ ብቻ የውርስ ንብረት የሚያሳጣቸው በመሆኑ በዚሁ መንገድ ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው ተደርጎ ሊተገበር ይገባዋል። ቅጽ/11
ሰ/መ/ቁ 58338፡- አንድ አውራሽ ለወራሹ አንድን ንብረት ቢናዘዝለት የኑዛዜው አፈፃጸም የስጦታ አፈፃጸምን በመከተል ሳይሆን የክፍያ ደንብ በመከተል የሚከናውን ይሆናል። ነገር ግን በኑዛዜው ላይ የሚሰጠው የክፍያ መጠን በመገለጹ ብቻ ሁል ጊዜ የክፍያ ደንብ ነው ሊባል የሚቻል አይደለም። በኑዛዜ የተሰጠው የንብረት መጠን ከሟቹ የውርስ ንብረት ጋር መታየት ያለበት ነው። በሌላ አገላለጽ ሟች በኑዛዜው ላይ የሚያሰፍረው የንብረት መጠን ከሟቹ የውርስ ንብረት መጠን ጋር እየታየ የመነቀል ጉዳይ ነው ወይስ የክፍያ ማነስ የሚለው ነጥብ የሚለይ ይሆናል። ጠቅላላ ንብረቱ ስድሰት መቶ ሺህ ብር የሚቆጠር ሟች ሁለት ልጆቸ በህይወቴ ከፍተኛ ችግር ስለፈጠረብኝ እያንዳንዳቸው አምስት ብር እንዲወስዱ የወንድሜ ልጅ ቀሪውን ንብረቴን በሙሉ እንዲወስድ በሚል ቢናዘዝ ጉዳዩ የክፍያ ማነስ ሳይሆን የመነቀል ውጤት ያለው ነው። ለወንድሙ ልጅ ያደረገለት ጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ በመሆኑ እንዲሁም ዝርዝሩን ሳይገልፅ በህይወቴ ከፍተኛ ችግሮች ስለፈጠሩብኝ የሚለው የተለያየ ደረጃ እና እርከን ያለው በመሆኑ ለመንቀል በቂና ህጋዊ ምክንያት ስላልሆነ በፍ/ብ/ህ/ቁ/ 938 እና 915 መሠረት ሁሉም ልጅና የወንድም ልጅ የውርሱን ንብረት እኩል ሊካፈሉ ይገባል እንጂ ውጤቱ የክፍያ ማነስ ስለሆነ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 መሠረት በክፍያ ደንብ የሚታይ ነው ሊባል አይገባም። ቅጽ/11
ሰ/መ/ቁ 47622፡- የፍ/ብ/ህ/ቁ 913 በኑዛዜ ስጦታ (legacy) እንዲሁም የክፍያ ደንብ (rule of partition) ማድረግ እንደሚቻል የሚናገር ነው። በመርህ ደረጃ አንድ ሰው ከውርስ ሃብቱ መካከል አንድን ንብረት ከወራሾቹ መካከል ለአንዱ በኑዛዜ መስጠት የክፍያ ደንብ እንጂ የኑዛዜ ስጦታ አያስብልም። በመሆኑም አንድ አውራሽ ለወራሹ አንድን ሃብት ሲናዘዝ የኑዛዜው አፈጻጸም የስጦታ (legacy) አፈጻጸምን በመከተል ሳይሆን የክፍያ ደንብን (rule of partition) በመከተል የሚከናወን ነው። አንድ አውራሽ በኑዛዜ ወራሽ ለሆነው ልጅ አምስት ሺ ብር ተናዘዘለት እና ለሌሎች ወራሾች ደግሞ ሌላ ንብረት ከተናዘዘላቸው የክፍያ ደንብ እንጂ የኑዛዜ ስጦታ ባለመሆኑ በክፍያው አንድ ተወላጅ ከሚደርሰው ከሩብ የበለጠ ጉዳት ከደረሰበት የኑዛዜ ክፍፍሉ እንዲቀር ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። የጉዳቱን መጠን ለማወቅ ውርሱ መጣራት አለበት። እንዲሁም ከውርስ መነቀል ማለት ከውርስ ሃብት ምንም አይነት ድርሻ አለማግኘት እንጂ አነስተኛ ድርሻ ማግኘት ስላልሆነ ከሌሎች ወራሾች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ድርሻ ተሰጥቶኛል የሚል ወገን ከውርስ ተነቅያለሁ ሊል አይችልም። ቅጽ/10
የሰ/መ/ቁ.189118፡-------- ሌሎች ወራሾች ከሟች የውርስ ሀብት ምንም ያልደረሳቸው ሳይሆን የደረሳቸው ድርሻ ግን አነስተኛ ከሆነ እነዚህ የሟች ወራሾች ከሚደርሳቸው የውርስ ሀብት ድርሻ አነስተኛ ደርሶአቸዋል ከሚበል በስተቀር ከሟች የውርስ ሀብት ምንም ድርሻ እንዳላገኙ ተነቅሏል የሚያስብል አይደለም፡፡ የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም
ሰ/መ/ቁ.135686፡- ኑዛዜው የሕጉን ፎርማሊቲ ያሟላ ነው ከተባለና በኑዛዜው አንድ ወራሽ አለአግባብ ተነቀለ የሚባል ቢሆን በውርሱ አከፋፈል ላይ የሚታይ እንጂ በአግባቡ የተሰጠን ኑዛዜ ፈራሽነት የሚያስከትል የሕግ ምክንያት አይኖርም። ከፍትሃብሔር ሕጉ አንቀጽ 913 ድንጋጌ የኑዛዜው ቃል የተናዛዥን ተቃራኒ ሐሣብ የሚገልጽ ካልሆነ በቀር ከውርስ ሃብት አንድ ድርሻን ወይም አንድ ንብረትን ሟቹ ለወራሾች መስጠቱ ተራ የሆነ የክፍያ ደንብ እንጂ እንደ ኑዛዜ ስጦታ ነው ተብሎ አይቆጠርም በማለት ያስቀምጣል።
ከዚህ ድንጋጌ ለመገንዘብ የሚቻለው በኑዛዜው የሚከናወኑ ተግባሮች የኑዛዜ ስጦታ (legacy) ወይም የክፍያ ደንብ (Rule of Partition) ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው። በመርህ ደረጃ አንድ ሰው ከውርስ ሀብቱ መካከል አንድን ንብረት ለወራሾቹ መስጠቱ የኑዛዜ ስጦታ አያሰኘውም። ይልቁንም ይህ አይነት ኑዛዜ ሕጉ የሚቀበለው እንደ አንድ የክፍያ ደንብ ነው። በመሆኑም አንድ አውራሽ ለወራሹ አንድን ንብረት ቢናዘዝለት የኑዛዜው አፈፃፀም የስጦታ (legacy) አፈፃፀምን በመከተል ሳይሆን የክፍያ ደንብ (Partition) በመከተል የሚከናወን ይሆናል።
ኑዛዜው ስጦታን (legacy) የሚመለከት ከሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 942 ጀምሮ ባሉ አንቀፆች መሠረት በማጣራት (liquidation) ሥርዓት የሚከናወን ሲሆን ክፍያ ግን ክፍፍልን (partition) በሚመለከቱና ከአንቀጽ 1060 ጀምሮ ባሉ ድንጋጌዎች መሠረት የሚስተናገድ ነው። የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1123 ደግሞ በዚሁ የሕጉ ክፍል ማለትም የውርስ ክፍፍልን በሚመለከተው ስር ያለ ነው። በመሆኑም የቁም ስጦታ የሚለውን ቃል ብቻ በመያዝ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1123 ድንጋጌ ለጉዳዩ አግባብነት የለውም ሊባል አይገባም። ኑዛዜው የስጦታ ነው የሚባል ቢሆን ኖሮ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥሮች 1037-1051 መሠረት እንዲሁም 1047/3/ መሠረት የተጠቀሰው ንብረት ወይም ግምቱ ለስጦታ ተጠቃሚው በቅድሚያ ይሰጣል።
የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1123/1/ ድንጋጌ በስጦታ አከፋፈል ውስጥ ተቃራኒ ቃል ከሌለ በቀር ወደታች ከሚቆጠሩ ተወላጆች አንዱ ከሚደርሰው ከሩብ የበለጠ ጉዳት ደርሶበት እንደሆነ የስጦታ አከፋፈሉ እንዲቀር ለመጠየቅ ይችላል በማለት በግልፅ ያስቀምጣል። የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1123 በስጦታ አከፋፈሉ ተቃራኒ ቃል ከሌለ በቀር የሚለው ይዘት ሟች ተወላጆቹን ከሩብ የበለጠ ጉዳት እንዲደርስባቸው ለማድረግ የሚችለው ሕጋዊና በቂ ምክንያት ሲኖረው ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 938 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ጋር በማገናዘብ ተረድተናል። በመሆኑም በውርስ ክፍፍል ጊዜ ተወላጅን ከሩብ በላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ የሚቻለው ሕጋዊና በቂ ምክንያት ሲኖር ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1123/1/ ድንጋጌ ስር በስጦታ ክፍፍሉ ተቃራኒ ቃል ከሌለ በቀር የሚለው ሐረግ አቀራረፅና ይዘት የሚያስገነዝበን ነው። "ሲቸገረኝ ልትረዳኝ፣ ልታስታምመኝ በችግሬ ልትደርስልኝ ቀርቶ በየጊዜው የምትሰድበኝና የምታዋርደኝ የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲሁም ከባንክ የተቀመጠውን ገንዘብ እንዳይወርሰኝ ከውርስ ነቅያታለሁ" የሚል ከጠቅላላ ንብረቱ 2000 ብር ብቻ ቢናዘዝለት ምክንያቱ ተወላጅን ከሩብ በላይ እንዲያጣ ለማድረግ በቂ ነው። ምክንያቱም ተወላጅ ወላጁን የሚስድብና የሚያዋርድበት አግባብ በማህረሰቡ ዘንድም ሆነ በወንጀል ሕጉም ተቀባይነት የሌለው ነውና፡ የስድቡ አይነትና የማዋረዱ ሁኔታ በኑዛዜው በግልጽ ባይጠቀስም ይህ አለመደረጉ ኑዛዜውን ፈራሽ ለማድረግ የማያስችል ሲሆን መታየት ያለበት ወላጅ በተወላጅ መሰደቡና መዋረዱ በነባራዊው አለም በማህበረሰቡም ተቀባይነት የሌለው አስነዋሪ ተግባር የመሆኑ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የሟች ልጅ ሁነው እያለ ለሟች ተገቢውን ክብር መስጠት እያለባቸው ሲሰድቧቸውና ሲያዋርዷቸው የነበረ መሆኑ ከተረጋገጠ ክፍፍሉ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1123 መሠረት መስተካከል ይኖርበታል። የተናዛዡ ፍላጐትም በሕግ መጠበቅ አለበት። ህዳር 19 ቀን 2010 ዓ.ም
ከፍ ሲል ከተጠቀሱት ጥቂት የሕግ ትርጉሞችሰበር ችሎቱ ከሕጉ እሳቤ በመውጣቱ ሲቸገር እና እርስ በእርስ የሚጋጩ ውሳኔዎችን መስጠቱን እናያለን፡፡
በመጀመሪያዎቹ ውሳኔወች ላይ በአንዳንዶቹ ላይ ኑዛዜው መነቀል አስከትሏል የሚባለው ከቀሪው የውርስ ሃብት ጋር ተነጻጽሮ አነስተኛ ድርሻ ሲደርሰው ነው ተባለ፡፡ በሁለተኛው ውሳኔ በኑዛዜ ሊደርሰው ከሚገባው 1/4ኛ በላይ ማጣት እና መነቀል እኩል ደረጃ ተሰጠው ፡፡ በሶስተኛው ውሳኔ መጎዳት ወይም ከ1/4ኛ በላይ ማጣት ከመነቀል የተለየ እንደሆነ ትርጉም ተሰጠ ፡፡ በአራተኛው ውሳኔ እጅግ አነስተኛ ገንዘብ ማግኘት የድርሻ ማነስ ሳይሆን መነቀል ነው በሚል ተወሰነ፡፡ በአምተኛው እና ስድስተኛው ውሳኔ ከውርስ መነቀል ማለት ከውርስ ሃብት ምንም አይነት ድርሻ አለማግኘት እንጂ አነስተኛ ድርሻ ማግኘት ስላልሆነ ከሌሎች ወራሾች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ድርሻ ተሰጥቶኛል የሚል ወገን ከውርስ ተነቅያለሁ ሊል አይችልም በሚል ተወሰነ፡፡ በሰባተኛው ውሳኔ ላይ ደግሞ ከ1/4ኛ ድርሻ በላይ ማጣት ከውርስ መንቀል ጋር እኩል ሆኖ ተወሰነ፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ጥቂት የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች ከውርስ መነቀል እና የመነቀል ውጤት እንዲሁም ከውርስ መነቀል እና የድርሻ ማነስን በተመለከተ በሰበር የተሰጡት ውሳኔዎች ግራ የሚያጋቡ መሆኑን እንገነዘባል፡፡
አንድ ተወላጅ በኑዛዜ ድርሻ አንሶታል ካልን ውጤቱ ይህ ተወላጅ ኑዛዜው ባይኖር ኖሮ ሊደርሰው የሚገባውን ሩቡን ማለትም ¼ ወይም 25% አጥቶ 75% እንዲያገኝ ሆኖ ይፈጸማል፡፡ አንድ ተወላጅ በኑዛዜ ያለ በቂ ምክየት ወይም በዝምታ ተነቀለ ካልን ግን ውጤቱ ከሌሎች ጋር እኩል መካፈል ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ተወላጅ በኑዛዜ የተሰጠው ድርሻ አነስተኛ መሆን ድርሻ ማነስ ነው፤ መጎዳት ነዉ ወይስ መነቀል ነው የሚለውን ድምዳሜ መለየት ተወላጁን ሊያገኘው ከሚገባው 25% ላይ መወስን ስለሆነ ግልጽ ትርጉም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ፡-የውርስ ሃብቱ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን ብር ሆኖ አራት ወራሾች ሆነው አንደኛው ተወላጅ በኑዛዜ ድርሻ አንሶታል ካልን ኑዛዜው ባይኖር 250,000 ብር ይደርሰው ነበር፡፡ በኑዛዜው ምክንየት ሊያጣ የሚችለው የ250,000 ን 25% ብር 62,500 ብቻ ነው፡፡ያበቂ ምክንየት ወይም በዝምታ መነቀል ነው ካልን ግን ተወላጁ ከሌሎች ተወላጆች እኩል 250,000 ብር ያገኛል፡፡ስለዚህ መነቀል ማለት አነስተኛ ድርሻ ሲሆን ነው? ምንም ሳይሰጠው ሲቀር ነው? ሊደርስው ከሚገባው ከ1/4ኛ በላይ ሲያጣ ነው? የሚለው ከፍ ሲል የተመላከቱት እና ሌሎች ውሳኔዎች ታይተው እንደገና በሰባት ዳኞች ሌላ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሚያስፈልገው ነው፡፡
በአንድ አንድ ባለሙያዎች መወዛገብ ስላለ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) ሊደርሰው ከሚገባው ከ25% በታች ስለማግኘት ሳይሆን ሊደርሰው ከሚገባው 25% ማጣት ወይም 75% ስለማግኘት የሚያወራ ነው፡፡ በተጨማሪም የሕግ ባለሙያወች እና ጸሃፊዎች መነቀል እና መጎዳት ግንኙነት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
እንደ እኔ አረዳደድ እና አመለካከት ግን የሰበር ትርጉሞች እስካልተለወጡ ድረስ አስገዳጅነታቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ ከውርስ መነቀል ከመጎዳት ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም፡፡ምክንየቱም በጽሁፌ መጀመሪያ አካባቢ እና ከፍ ሲል እንደገለጽሁት የመጎዳት ጽንሰ ሃሳብ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) ወላጆች በህይዎት እያሉ ለተወላጆቻቸው በስጦታ ውል (ሰረዝ የተጨመረበት) ንብረታቸውን ለተወላጆቻቸው በቁማቸው በሚያከፋፍሉበት ጊዜ ተፈጻሚነት ያለው እና ውል በመሆኑም ተወላጆች ወላጆቻቸው በህይዎት እያሉም ድርሻ አንሶኛል ከ1/4ኛ በላይ አጥቻለሁ ይስተካከልልኝ ብለው የሚጠይቁበትን የሕግ አግባብ የያዘ እና የሚገዛ እንጂ መሠረቱ ውል ሳይሆን ኑዛዜ ወይም የኑዛዜ ስጦታ ከሆነው የመነቀል ጽንሰ ሃሳብ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ የመጎዳት ድንጋጌዎችም ለመነቀል ተፈጻሚነትም ሆነ ተገቢነት የላቸውም፡፡ በመሆኑም ተወላጅ በኑዛዜ ሊያገኝ ከሚገባው 1/4ኛ በታች ቢሰጠው ተነቀለ ሊባል አይቻልም፡፡ በሕጉ አነጋገር ከሄድን 1/4ኛ ብቻ ማሳጣት አይደለም ወላጅ የተወለደን ተወላጁን ሊደርሰው የሚገባውን 80 % ቢከለክለው የሕግ ገደብ የለበትም፡፡ ማንኛውም ሰው ንብረቱን በውርስ ለማስተላለፍ ህገ መንግስታዊ መብት አለው፡፡ ይህን ህገ-መንግስታዊ መብቱን የማይገናኝ ነገር በማገናኘት ልንገድበው አይገባም፡፡ ኑዛዜ ተናዛዙ ከፈለገ የሚያደርገው፤ ከፈለገ የሚሽረው፤ የሚለውጠው፤ የሚቀይረው የተናዛዡ የግል ስራ ነው፡፡
በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ተወላጆች በድርሻ ሲጎዱ ማስተካከያ እንዲጠይቁ የተፈቀደው ተናዛዞች በሕይዎት እያሉ የሚፈጸም ግላዊነት እና ሚስጥራዊነት የሌለው በተግባር የተካፈሉት የስጦታ ውል በመሆኑ እንደማንኛውም ውል ተዋዋይ ወገኖች እንዲሻሻል ወይም እንዲቀር መጠየቅ ስለሚችሉ ነው፡፡ ስለሆነም ከ1/4ኛ በላይ ማጣት ከመነቀል ጋር የሚያያዝበትም ሆነ መነቀል ነው የሚባልበት የሕግ ምክንየት የለም፡፡ እንዲሁም አነስተኛ ድርሻ ማግኘት መነቀል አይደለም፡፡ ሊደርሰው ከሚገባው ከ1/4ኛ በታቸ ማግኘትም መነቀል አይደለም፡፡ ነገር ግን እጅግ አነስተኛ ድርሻ ማግኘት ለምሳሌ አንድ ሚሊዮን ብር ሊደርሰው እየቻለ አምስት ብር በኑዛዜ ቢሰጥ ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1123 ጋር ታይቶ ሳይሆን በራሱ በመነቀል ጽንሰ ሃሳብ ታይቶ 5 ብር እንደሰጠ ስለማይቆጠር እንደ መነቀል የሚቆጠር ነው፡፡ እንደሰጠ ስለማይቆጠርም ከድርሻ ማነስ ጋር አይገናኝም፡፡ ስለሆነም ከምክንየታዊነት አንጻር ሰበር ችሎቱ መነቀል ምንም አለማግኘት ነው የሚለውን በተሻለ አገላለጽ እጅግ አነስኛ ድርሻ መስጠት ወይም እንደሰጠ በማያስቆጠር ወ..ዘ.ተ በሚል ገላጭ ቃል ቢያሰተካክለው የሕጉን መንፈስ የተከተለ ይሆናል፡፡ ምክንየቱም ምንም አለማግኘቴ ከተባለ ጥሩ የዉርስ ንብረት ያለዉ ሟች አስር ወይም መቶ ብር ወይም ሳንቲም ስለሰጠ የተወላጆችን ያለበቂ ምክንየት ያለመነቀል መብት ይጣብባል፡፡
7) በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የውርስ ሕግ መነቀልን መሠረት ያደረገ የኑዛዜ ይሻርልኝ ይርጋ ላይ የተሰጡ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች እና ሕጉ
ሌላው ከሕጉ የቃላት አጠቃቀም ችግር የተነሳ የሕጉን መንፈስ ሳይከተሉ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠበት የዉርስ ሕግ ጉዳይ የይርጋ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ የሕግ ባለሙያ አሁን ካሉት የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች ተነስቶ ከኑዛዜ ይሻርልኝ ጋር የተያያዙ የዉርስ ሕግ ክርክሮችን በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም፡፡ የመነቀል ጉዳይ ይርጋው ይርጋዉ ከሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች አንጻር ስንት ነዉ የሚለዉን በተመለከተ የሰበር ችሎቱን መደናገር ለማሳየት ውሳኔዎች እናንሳ፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመጀመሪያው ሰ/መ/ቁ.231510፣ ሰ/መ/ቁ.152134 እና ሰ/መ/ቁጥር 182269 በሰጣቸዉ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች ላይ ኑዛዜ ከውርስ ነቅሎኛል በሚል የሚቀርብ ክስ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ 973 የተቀመጠው ሳይሆን በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) የተቀመጠው ነው ብሏል፡፡ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞቹ ይዘታቸዉ በአጭሩ እንደሚከተለዉ ነዉ፡፡
1) ሰ/መ/ቁ.231510፡- በኑዛዜ ከውርስ ተነቅያለሁ የሚል ወራሽ ኑዛዜ እንዲፈርስ በፍ/ሕ/ቁጥር 1123/3 መሠረት በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 152134 (በቅጽ 23 የታተመ) በየትኛውም ደረጃ ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ ነው። በዚህ መሠረት ሟች በኑዛዜ ተጠቃሚወች ከፍተኛ የመንፈስ ጫና ተደርጎባቸው ያደረጉት ኑዛዜ ከውርስ የነቀለ በመሆኑ ህጋዊ ውጤት ሊኖረው አይገባም ለሚል ክስ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ጊዜ በፍ/ሕ/ቁጥር 1123/3 የተመለከተው 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ ነው።ግንቦት 30ቀን 2015 ዓ/ም
2) ሰ/መ/ቁ.152134፡- የፍትሃብሄር ሕግ ቁጥር 973 ስለ ኑዛዜ መነበብ እንዲሁም ኑዛዜው ሲነበብ የነበሩ ሰዎች ኑዛዜው እንዲፈርስ አቤቱታ የሚያቀርቡበትን ሥርዓት እና ጊዜውን በሚመለከት የሚደነግግ ነው። ይህ ድንጋጌ ኑዛዜው ከውርስ ነቅሎኛል /ነቅሎናል/ በማለት ኑዛዜው እንዲፈርስ የሚቀርብን ወይም የቀረበን አቤቱታ የሚመለከት አይደለም። የአመልካቹ መሠረታዊ የአቤቱታ ይዘት ኑዛዜው ከውርስ የመንቀል ውጤት ያለው በመሆኑ እንዲፈርስ የሚል ከሆነ ይህ የዳኝነት ጥያቄ ሊታይ የሚገባው በፍትሃብሄር ሕግ ቁጥር 1123 መሠረት ነው እንጂ በአንቀጽ 973 መሠረት አይደለም። ቅጽ/23
3) ሰ/መ/ቁጥር 182269፡- የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 973 ኑዛዜ ሲነበብ የነበረ ሰው ኑዛዜው እንዲፈርስ የሚጠይቅበትን የይርጋ የሚመለከት ሲሆን ኑዛዜው ከውርስ የመንቀል ውጤት ያለው ሆኖ እንዲፈርስ የሚቀርበውን ክስ የሚመለከተው ይርጋ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1123 ሥር የተደነገገው ነው። መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ/ም
በሌላ በኩል በሚከተለዉ በሰ/መ/ቁ 36604 ላይ ደግሞ ኑዛዜው ከውርስ ነቅሏል በሚል ኑዛዜን በፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 የተመለከተው ጊዜ ካለፈ መሻር አይቻልም በሚል የይርጋ ጊዜው መጨረሻው በ974/2/ የተመለከተው አምስት አመት ነው በሚል አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ የሕግ ትርጉሙ በአጭሩ እንደሚከተለዉ ነዉ፡፡
4) ሰ/መ/ቁ 36604፡- ያለኑዛዜ ወራሽ የሆነ ሰው ኑዛዜ መደረጉን ብቻ ሳይሆን ኑዛዜ የተደረገለት ሰው በኑዛዜው መሠረት ተጠቃሚ ሆኖ መቆየቱን ጭምር አውቆ ለአስራ ስድስት ዓመታት በዝምታ ማለትም ሳይቃወም ከቆየ በኋላ ኑዛዜው አይፀናም በማለት ተቋውሞ ሲያነሳ የኑዛዜው ተጠቃሚ የሆነው ሰው የይርጋ መቃወሚያ ካነሳ ተቃውሞው በፍ/ብ/ህ/ቁ 973 መሠረት ተቀባይነት ማግኘት አለበት። ከአምስት ዓመት በኋላ ተቃውሞ ለማቅረብም የጊዜ ገደቡን በ974/2/ የተመለከተው የጊዜ ገደብ ይከለክለዋል። ፍ/ቤቶችም የይርጋ መቃወሚያውን ወይም የጊዜ ገደቡን አልፈው ያለኑዛዜ ወራሾችን ያለምንም ምክንያት ነቅሏል ወይም በዝምታ ነቅሏል በማለት ኑዛዜው አይፀናም የሚል ውሳኔ መስጠት አይችሉም። (በቅፅ/8 ታትሟል)
በሌላ በኩል በሌሎች መዝገቦች ላይ ደግሞ ከውርስ ተነቅኛለሁ የሚል ክስ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ይርጋ እንደሚገዛ ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ በአጭሩ ይዘታቸዉ የሚከተለዉ ነዉ፡፡
5) ሰ/መ/ቁ.148272፦ ኑዛዜ በተዘዋዋሪ መንገድ ከውርስ የነቀለኝ ስለሆነ ይሻርልኝ የሚል አቤቱታ ተፈጻሚ የሚሆነው ሕግ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000 (1) እና (2) ድንጋጌዎች እንጂ የቁጥር 974 (2) ድንጋጌ አይደለም ።መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም.
6) ሰ/መ/ቁ.147662፡- በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 973 እና 974 ድንጋጌዎች የተመለከተውን የተለያየ የይርጋ ጊዜ የተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ ሰበር ሰሚ ችሎት እነዚህን ድንጋጌዎች አግባብነት ካላቸው ውርስን ከሚመለከቱ የፍትሐብሔር ሕጉ ሌሎች ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ በመተርጎም የፍ.ሕ.ቁ. 973 እና 974 ድንጋጌዎች ተናዛዡ ካደረገው የውርስ ሀብት ድልድል ጋር ተያይዞ የሟች ወራሾች ኑዛዜው አይጸናም የሚሉባቸውን ምክንያቶች መሠረት በማድረግ ተቃውሞ ለማቅረብ የሚችሉበትን የጊዜ ገደብ የሚያመለክቱ እንጂ በቁጥር 938 እና 939 ድንጋጌዎች ጥበቃ የተደረገለትን ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ከውርስ ያለመነቀል መብት፣ኑዛዜው የተደረገበት ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል የተናዛዡ አለመሆኑን እና መሰል መብቶችን መሠረት በማድረግ ኑዛዜው እንዲፈርስ ወይም እንዲቀነስ በሚቀርቡ ክሶች ጉዳይ ተፈጻሚነት የላቸውም። የእነዚህ ዓይነቶቹ ክሶች የሚቀርቡበትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ቀደም ሲል በመ.ቁ.15974 እና በሌሎች መዝገቦችም በተሰጠው የሕግ ትርጉም መሠረት በፍ.ሕ.ቁ. 1000 የተመለከተው የይርጋ ዘመን ስለመሆኑ በመ.ቁ. 70292 እና በመ.ቁ. 93501 ላይ አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም ሰጥቶአል። ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም
7) ሰ/መ/ቁ.148272፡- በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 973 እና 974 ድንጋጌዎች የተመለከተውን የተለያየ የይርጋ ጊዜ የተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት እነዚህን ድንጋጌዎች አግባብነት ካላቸው ውርስን ከሚመለከቱ የፍትሐብሔር ሕጉ ሌሎች ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ በመተርጎም ቁጥር 973 እና 974 ድንጋጌዎች ተናዛዡ ካደረገው የውርስ ሀብት ድልድል ጋር ተያይዞ የሟች ወራሾች ኑዛዜው አይጸናም የሚሉባቸውን ምክንያቶች መሠረት በማድረግ ተቃውሞ ለማቅረብ የሚችሉበትን የጊዜ ገደብ የሚያመለክቱ እንጂ በቁጥር 938 እና 939 ድንጋጌዎች ጥበቃ የተደረገለትን ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ከውርስ ያለመነቀል መብት፣ኑዛዜው የተደረገበት ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል የተናዛዡ አለመሆኑን እና መሰል መብቶችን መሠረት በማድረግ ኑዛዜው እንዲፈርስ ወይም እንዲቀነስ በሚቀርቡ ክሶች ጉዳይ ተፈጻሚነት የሌላቸው ስለመሆኑ እና የእነዚህ ዓይነቶቹ ክሶች የሚቀርቡበትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ቀደም ሲል በመዝገብ ቁጥር 15974 እና በሌሎች መዝገቦችም በተሰጠው የሕግ ትርጉም መሠረት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000 የተመለከተው የይርጋ ዘመን ስለመሆኑ በመዝገብ ቁጥር 70292 በ13/07/2005 ዓ.ም. እና በመዝገብ ቁጥር 93501 በ12/07/2006 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 454/1997 በአንቀጽ 2(1) መሠረት በየትኛውም እርከን በሚገኝ ፍ/ቤት ላይ አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም ሰጥቶአል። በመሆኑም ኑዛዜ በተዘዋዋሪ መንገድ ከውርስ የነቀለኝ ስለሆነ ይሻርልኝ የሚል አቤቱታ ተፈጻሚ የሚሆነው ሕግ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000 (1) እና (2) ድንጋጌዎች እንጂ የቁጥር 974 (2) ድንጋጌ አይደለም ።መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም.
በሌላ በኩል ደግሞ በሰ/መ/ቁ.92788 ላይ ድንጋጌው ተገልጾ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (1) ከተመለከተው መጠን በላይ ስለተጎዳሁ የሚል ክስ የይርጋ ዘመኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ነው ይላል፡፡ ይዘቱ በአጭሩ የሚከተለዉ ነዉ፡፡
8) ሰ/መ/ቁ.92788፡- የፍ.ሕ.ቁ. 973 እና 974 ድንጋጌ ኑዛዜው ሲነበብ የነበሩ ወይም የተወከሉ ሰዎች ኑዛዜው አይጸናም ወይም አንዱ በኑዛዜው የተነገረው ቃል አይጸናም በማለት ክስ ለማቅረብ ያላቸውን ሀሳብ መግለጽ የሚችሉበትን የጊዜ ገደብ ከማስቀመጥ ውጪ ተቃውሞ አቅራቢዎቹ ኑዛዜው አይጸናም የሚል የተቃውሞ ሀሳብ ለማቅረብ የሚችሉባቸው ምክንያቶች ምን እንደሆኑ የሚጠቁመው ነገር የለውም። በፍ.ሕ.ቁ. 973 እና 974 ድንጋጌዎች የተመለከተውን የተለያየ የይርጋ ጊዜ የተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ የፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት እነዚህን ድንጋጌዎች አግባብነት ካላቸው ውርስን ከሚመለከቱ የፍትሐብሔር ሕጉ ሌሎች ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ በመተርጎም የፍ.ሕ.ቁ. 973 እና 974 ድንጋጌዎች ተናዛዡ ካደረገው የውርስ ሀብት ድልድል ጋር ተያይዞ የሟች ወራሾች ኑዛዜው አይጸናም የሚሉባቸውን ምክንያቶች መሠረት በማድረግ ተቃውሞ ለማቅረብ የሚችሉበትን የጊዜ ገደብ የሚያመለክቱ እንጂ በቁጥር 938 እና 939 ድንጋጌዎች ጥበቃ የተደረገለትን ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ከውርስ ያለመነቀል መብት፣ኑዛዜው የተደረገበት ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል የተናዛዡ አለመሆኑን እና መሰል መብቶችን መሠረት በማድረግ ኑዛዜው እንዲፈርስ ወይም እንዲቀነስ በሚቀርቡ ክሶች ጉዳይ ተፈጻሚነት የሌላቸው ስለመሆኑ እና የእነዚህ ዓይነቶቹ ክሶች የሚቀርቡበትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ቀደም ሲል በመ.ቁ.15974 እና በሌሎች መዝገቦችም በተሰጠው የሕግ ትርጉም መሠረት በፍ.ሕ.ቁ. 1000 የተመለከተው የይርጋ ዘመን ስለመሆኑ በመ.ቁ. 70292 በ13/07/2005 ዓ.ም. እና በመ.ቁ. 93501 በ12/07/2006 ዓ.ም. አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም ሰጥቶአል። በመሆኑም የቀረበው ክሱ የሟች ኑዛዜ በሟች ነፍስ አባት አማካይነት የቤተሰቡ አባላት በተገኙበት እንደተነበበላቸው፣ኑዛዜው በእናታቸው ድርሻ ላይ ጭምር የተደረገ፣ወራሾችን የሚነቅል እና በፍ.ሕ.ቁ. 1123(1) ከተመለከተው መጠን በላይ ጉዳት የሚያደርስባቸው መሆኑን ገልጸው ኑዛዜው እንዲፈርስ ውሳኔ ይሰጥ ዘንድ ዳኝነት የጠየቁ ከሆነ ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ዘመን በፍ.ሕ.ቁ. 973 የተመለከተው ሳይሆን በፍ.ሕ.ቁ. 1000 የተመለከተው ነው። መጋቢት 24 ቀን 2006 ዓ.ም.
የሚሉ የሰበር አስገዳጅ ትርጉሞችን ብቻ ማንሳት ምን ያህል የውርስ ሕጉን ባለመከተል ውዝግብ ውስጥ እንደተገባ የሚያሳይ ነው፡፡
በመጀመሪያው፣ በሁለተኛው እና በሶስተኛው የሰበር ውሳኔ ኑዛዜ ከውርስ ነቅሎኛል በሚል የሚቀርብ ክስ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ 973 የተቀመጠው ሳይሆን በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) የተቀመጠው ነው ይላል ፡፡በአራተኛው ውሳኔ ኑዛዜው ከውርስ ነቅሏል በሚል ኑዛዜን በፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 የተመለከተው ጊዜ ካለፈ መሻር አይቻልም በሚል የይርጋ ጊዜውን መጨረሻው በ974/2/ የተመለከተው አምስት አመት ነው ይላል፡፡ በአምስተኛው፤ በስድስተኛው እና በሰባተኛው፤ ውሳኔዎች ላይ ደግሞ ከውርስ ተነቅኛለሁ የሚል ክስ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ይርጋ እንደሚገዛ ትርጉም ተሰጥቷል ፡፡ በስምንተኛው የሕግ ትርጉም ደግሞ ጭራሽ ድንጋጌው ተገልጾ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (1) ከተመለከተው መጠን በላይ ስለተጎዳሁ የሚል ክስ የይርጋ ዘመኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ነው ይላል፡፡
"------በፍ.ሕ.ቁ. 1123 (1) ከተመለከተው መጠን በላይ ጉዳት የሚያደርስባቸው መሆኑን ገልጸው ኑዛዜው እንዲፈርስ ውሳኔ ይሰጥ ዘንድ ዳኝነት የጠየቁ ከሆነ ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ዘመን በፍ.ሕ.ቁ. 973 የተመለከተው ሳይሆን በፍ.ሕ.ቁ. 1000 የተመለከተው ነው።"
ከእነዚህ ትርጉሞች ተነስተን የውርስ መነቀል የይርጋ ዘመኑ ምን ያህን ነው የሚለውን በእርግጠኝነት በሰበር የሕግ ትርጉም መሠረት ይኸ ነው ማለት አንችልም፡፡ የሚያስገድደዉስ የትኛዉ ነዉ የሚለዉን ለመምረጥ ያስቸግራል፡፡
ምክንየቱም፡-
- በመጀመሪያ በተጠቀሰው የሕግ ትርጉም መሠረት ከውርስ የመነቀል ክስ ይርጋ ገደብ በፍ/ሕ/ቁጥር 1123/3 የተመለከተው 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ ነው፡፡ከውርስ የመነቀል ክስ ተግባራዊ የሚሆነው የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123/3/ ነው ከተባለ ለምን አስር ዓመት ይሆናል፡፡ በዚህ ድንጋጌ እኮ ሟች ከሞተ በሁለት አመት ውስጥ በሚል ተገልጧል ፡፡ ስለዚህ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ለኑዛዜ አግባብነት አለው ከተባለ በዚሁ ድንጋጌ የተመላከተውን በአማራጭ የተመላከተ የሁለት አመት ይርጋ ባላየ ልናልፈ አንችልም፡፡ ስለዚህ በዚህ የሕግ ትርጉም መሠረት አስር አመት ነው ወይስ ሁለት አመት የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡
- በሁለተኛነት እና በሶስተኛነት በተጠቀሰው የሕግ ትርጉም በተመሳሳይ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ሲተገበር ሁለት አመቱ ነው ወይስ አስር አመቱ የሚለውን አይለይልንም፡፡
- በአራተኛነት የተጠቀሰው ደግሞ የመነቀል ጉዳይ ይርጋ መጨረሻ በፍ/ብ/ህ/ቁ 974/2/ የተመላከተው አምስት አመት ነው ስለሚል ይህም ትርጉም በግልጽ ስላልተለወጠ አምስት አመት ነው ሊባል ይቻላል፡፡
- አምስተኛ፤ ስድስተኛ እና ሰባተኛ የሕግ ትርጉሞች ደግሞ ከውርስ የመነቀል ጉዳይ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 (1) እና (2) በተመለከቱት ይርጋዎች ይገዛል የሚል በመሆኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 (1) እና (2) ያስቀመጠው ይርጋ 3 እና አስራ አምስት አመት በመሆኑ ከሁለቱ የትኛው ነው የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ የይርጋ ጊዜው አስር ዓመት ነው በሚል ከተሰጡት ጋር ይጋጭብናል፡፡
- በስምንተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ትርጉም ደግሞ ጭራሽ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 በተመላከተው መሠረት ከሩብ በላይ ጉዳት ከደረሰባቸው የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 (3) የተመላከተው ሳይሆን ወደ ኋላ ተመልሶ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ነው ይላል፡፡ በቁጥር 1000 ስር ከተመላከተው አማራጭ የትኛው የሚለውን አያሳይም፡፡
ስለሆነም በሰበር ትርጉሞች መሠረት ከውርስ የመነቀል ይርጋ የቱ ነው የሚለውን መለየት አይቻልም፡፡ የውርስ ሕግ ከልዩ ባህሪያቶቹ አንዱ በመግቢያዉ እንደተገለጸዉ የራሱ የተለየ ስነ-ስርዓት መኖሩ እና በየራሳቸው ተከፋፍለው ለተዘረጉት ስነ-ሥርዓቶች የየራሳቸው ልዩ ባህሪ ያላቸው መሆኑ እንዲሁም የሚገዙበት ድንጋጌ የየራሳቸው እንጂ የአንደኛው ክፍል ድንጋጌ በሌላኛው የውርስ ሕጉ ክፍል ተግባራዊ አለመሆኑ ነው፡፡
ታዲያ በመነቀል ምክንየት ኑዛዜ እንዲፈርስ የሚቀርብ ክስ የይርጋ ጊዜው ምን ያህል ነው? በሰበር ከተሰጡት አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች መካከል የትኛዉ ትክክል ነዉ? ወይስ ሁሉም ሕጉን የተከተሉ ትርጎሞች አይደሉም? የሚለውን እንመርምር፡፡
በቅድሚያ የፍ/ብ/ህ/ቁ 973 ድንጌን አጠቃላይ አላማ እና ግብ እንዲሁም አጠቃላይ መንፈስ ከአጠቃላይ የውርስ ሕግ ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ ማየቱ ተገቢነት አለው፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 973 ስለውርስ ሕግ በተደነገገው የፍታብሄር ሕጉ በአንቀፅ 5 ስር ወራሽነትን ስለማጣራት በሚለው ምዕራፍ ሁለት ውስጥ የወራሾቹን ሁኔታ ለጊዜው ስለመወሰን በሚለው ንዑስ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የድንጋጌው ይዘትም፡-
"ኑዛዜው ሲነበብ የነበሩ ወይም የተወከሉ ሰዎች ኑዛዜው አይፀናም ወይም አንዱ በኑዛዜው የተነገረው ቃል አይፀናም በማለት ክስ ለማቅረብ ያላቸውን ሀሳብ መግለጫ ወይም ስለክፍያው በሂሳብ አጣሪው የቀረበውን የድልድልን አመዳደብ አሳብ ለመቃወም ኑዛዜው ከተነበበት አንስቶ የሚቆጠር አስራ አምስት ቀን አላቸው፡፡ ይህ መግለጫ በጽሑፍ ካልሆነና ለአጣሪው ወይም ለዳኞች ወይም በውርሱ የተነሳውን ነገር ለመጨረስ ለተመረጡ የሽምግልና ዳኞች እንዲደርስ ካልደተረገ በቀር አይጸናም፡፡ ይህ መግለጫ ከተሰጠበት ቀን አንስቶ እስከ ሶስት ወር ጥያቄውን /ክሱን/ ለዳኞች ወይም ለሽምግልና ዳኞች ካላቀረበ በቀር የመጠየቅ መብቱን ያጣል”
የሚል ነው፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 974 ደግሞ ኑዛዜው ሲነበብ ያልነበሩ ሰዎች ኑዛዜው ከፈሰሰበት ጊዜ ጀምሮ ከአምስት አመት በኋላ ወይም ኑዛዜ የሌለ እንደሆነ ከአምስት አመት በኋላ ስለኑዛዜው መጽናት እና ስለክፍያው አመዳደብ አጣሪው ያቀረበው የድልድል ሃሳብ በማናቸውም አስተያየት ቢሆን መቃወሚያ ሊቀርብብት አይችልም፡፡ ይላል
ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ በግልጽ እንደምንረዳው የእነዚህ ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ውርሱ በሚጣራበት ጊዜ ማለትም የውርስ ማጣራት ተግባር በሚከናወንበት ጊዜ እና ስልጣን ያለው ተቃውሞ የሚቀርብላቸው እና የሚሰማ ውርስ አጣሪ ወይም የውርስ ጉዳይ ለመጨረስ የተመረጡ የሽምግልና ዳኞች /arbitrators/ ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 ተግባራዊ እንዲሆኑ ኑዛዜው የተነበበው በውርስ ሕጉ ወራሽነትን ስለማጣራት የሚለው ምዕራፍ ሁለት ሲተገበር በውርስ ማጣራት/liquidation of succession/ ጊዜ በሕጉ እውቅና ባለው ውርስ አጣሪ አማካኝነት ውርሱን ለማጣራት አላማ በሆነ ጊዜ ነው፡፡ ኑዛዜው የተነበበው በሟች 40ኛ ቀን መታሰቢያ እለት ቢሆንም ኑዛዜውን ያነበቡት ሰው በሕጉ እውቅና ያገኘ ውርስ አጣሪ ሆኖ የተነበበውም ለውርስ ማጣራት አላማ መሆን አለበት፡፡ የዚሁ የሕግ ክፍል የሆኑት የፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 መነሻ ድንጋጌዎች የፍ/ብ/ህ/ቁ 965/1/ እና 966/1/ ኑዛዜ መነበብ እና መከፈት ያለበት በውርስ አጣሪ መሆን እንዳለበት ይነገራሉ፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 ድንጋጌዎች በፍ/ብ/ህ/ቁ 965 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሠረት ሟች ከሞተበት ጀምሮ ውርሱ ሲከፈት የውርስ አጣሪ የሚሾም መሆኑን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ ስለሆነም በሕግ፤ በኑዛዜ ወይም በስምምነት የተመረጠ የሽምግልና ዳኛ /Arbitrator/ ከሌለ እና የውርሱ ማጣራት በሕጉ አግባብ ባልተጀመረበት እና ኑዛዜው የተከፈተው እና የተነበበው ውርሱን ለማጣራት ስልጣን በሌለው ሰው (የሃይማኖት አባትን ጨምሮ) ቢሆንም ወራሾች ውርስ የማጣራት ስልጣን ለሌለው ኑዛዜ አንባቢ የተቃውሞ መግለጫ ያቅርቡ የሚባልበት የሕግ ምክንያት ስለሌለ በእነዚህ ድንጋጌዎች የተቀመጡት ይርጋዎች በበሕጉ አግባብ ባልተጠራ የዉርስ ጉዳይ ላይ ተግባራዊነት የላቸውም፡፡
በሌላ በኩል የፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 ድንጋጌዎች በኑዛዜ መጽናት እና ህጋዊነት ላይ የሚነሳን ክርከር የይርጋ ጊዜ የደነገጉ ናቸው፡፡ በድንጋጌዎቹ "--ስለኑዛዜው መጽናት----ኑዛዜው አይጸናም----አንዱ በኑዛዜ የተነገረ ቃል አይጸናም---- action of nullitiy of will ---the validity of will------ " በሚል የተገለጹት ቃላቶች የኑዛዜ ፈራሽነትን የሚመለከት ክስ ይርጋን እንደሚደነግጉ ያመላክታሉ፡፡በውርስ ሕጉ የኑዛዜ መጽናት እና አለመጽናት እንዲሁም ህጋዊነት መስፈርቶች በፍ/ብ/ህ/ቁ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 857 እስከ 941 ተቀምጠዋል፡፡ከፍ/ብ/ህ/ቁ 857 እስከ 941 የተደነገጉትን ምክንየት በማድረግ ኑዛዜ አይጸናም የሚል ክርክር በፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 ይርጋ የሚገዛ ነው፡፡
ስለሆነም ስለመነቀል የሚያወራው የፍ/ብ/ህ/ቁ 938 እና 939 በፍ/ብ/ህ/ቁ 973 እና 974 ስር የሚገኝ በመሆኑ እንደሕጉ እሳቤ ሟች ከሞተበት ቀን ጀምሮ ውርስ አጣሪ ተመድቦ ውርስ አጣሪው አንዱ ስራው የሆነውን ኑዛዜ አግኝቶ ኑዛዜውን ከፍቶ ለውርስ ማጣራት አላማ ካነበበላቸው እና ጊዜያዊ ድልድሉን ካሳወቃቸው በዚህ ኑዛዜ ተነቅያለሁ ኑዛዜው አይጸናም ሊሻር ይገባል የሚል ክስ ይርጋ በፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 በተመለከተው የይርጋ ጊዜ የሚገዛ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከውርስ ተነቅያለሁ ኑዛዜው ይሻርልኝ የሚል ክስ ይርጋ የፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 አይደለም በማለት የሰጠው የሕግ ትርጉም ከፍ ሲል በገለጽሁት ምክንየት ሙሉ በሙሉ ሕጉን የተከተለ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን በጥንቃቄ ማየት ያለብን ሌላ አቅጣጫ ወይም እይታ አለ፡፡
በብዛት በውርስ ችሎቶች እንደሚታየው እና በባህልም በልምድም የዳበረው ሟች እንደሞተ ውርስ አጣሪ አይሾምም፡፡ኑዛዜ ቢኖር እንኳን በሟች መታሰቢያ ቀን ወይም በሌላ ቀን የቅርብ ዘመድ ወይም የሃይማኖት አባት ያነብላቸዋል እንጅ ውርስ አጣሪ ተመርጦ፤ የውርስ ማጣራት ስራ ተጀምሮ ለውርስ ማጣራት አላማ አይነበብም፡፡ወይም ኑዛዜው ይቀመጥና አንድ ወራሽ ከአመታት በኋላ የውርስ ጥያቄ ሲያቀርብ ኑዛዜው አለ ተብሎ ይቀርብና ውርሱ ባይጣራም በሟች መታሰቢያ ቀን ተነቧል በፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 በይርጋ ይታገደል የሚል ክርክር ይቀርባል፡፡ወይም አንደኛው ወራሽ ውርሱ ባይጣራም ኑዛዜው መኖሩን እያወቀ ከአመታት በኋላ ኑዛዜው ከውርስ ስለነቀለኝ ይሻርልኝ የሚል ክስ ያቀርባል፡፡በሌላ ወገን በመቃወሚያነት የፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 ይነሳል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ በኑዛዜው መጽናት እና ህጋዊነት ላይ የፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡ምክንየቱም ከፍ ሲል እንደገለጽሁት የፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 ድንጋጌ ተፈጻሚነት እና ተግባራዊነት በውርስ ማጣራት ጊዜ በሕጉ አግባብ ውርስ አጣሪ ተመርጦ፤ በውርስ አጣሪው ለውርስ ማጣራት አላማ ኑዛዜው ሲከፈት እና ሲነበብ ነው፡፡
ውርሱ በሕጉ እሳቤ አግባብ በተሾመ ውርስ አጣሪ ካልተጣራ፤ በውርስ አጣሪው ለውርስ ማጣራቱ አላማ ካልተነበበ፤ ውርሱ ያልተጣራ ከሆነ አንድ ተነቀልሁ የሚል ወራሽ በምን ያህል ጊዜ ኑዛዜው እንዲሻር መጠየቅ እንዳለበት የውርስ ሕጉ ያስቀመጠው የይርጋ ጊዜ የለም ፡፡
የውርስ ሕጉ ይህን ሁኔታን በሚመለከት በዝምታ ስላለፈው የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ.1677 መሠረት በፍ/ብ/ህ/ቁ 1845 የተመለከተው የ አስር አመት የይርጋ ጊዜ ነው፡፡
ስለሆነም በመነቀል ምክንየት ኑዛዜ እንዲሻር የሚቀርብ ክስ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 የተመለከተው እና በፍ/ብ/ህ/ቁ 1845 የተመለከተው ሲሆን ከሁለቱ የትኛው የሚለው የሚለየው ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው በሕጉ አግባብ የውርሱ መጣራት አለመጣራት ጉዳይ ነው፡፡ውርሱ ከተጣራ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 የተመለከተው የይርጋ ጊዜ አግባብነት የሚኖረው ሲሆን ውርሱ ካልተጣራ ግን የፍ/ብ/ህ/ቁ 1845 ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ የውርስ ክፍፍል ወይም የውርስ ሃብት ለመጠየቅ ቅድሚያ ውርሱ መጣራት የማይጠበቅበት እና የውርስ ማጣራት ተግባር የውርስ ሃብት ለማግኘት ሁል ጊዜ ቅድመ ሁኔታ አለመሆኑ ከፍ ሲል ተነቀልሁ በሚል የሚቀርብ ክስ ይርጋ በሁለት አይነት መንገድ መታየት እንዳለበት የተደረሰበትን መደምደሚያ የሚያጠናክር ነው፡፡
ሌላው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተነቀልሁ በሚል ኑዛዜ እንዲሻር የሚቀርብ ክስ ላይ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ጊዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 የተመለከተው የይርጋ ጊዜ ነው ያለውን አግባብነት እንመልከት፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ጥያቄውን ለማቅረብ የተወሰነ ጊዜ፡-
- ከሳሽ መብቱን እና የውርስ ንብረቶች በተከሳሹ መያዛቸውን ካወቀ ሶስት አመት ካለፈ በኋላ ስለወራሽነት የሚያቀርበው ክስ ተቀባይነት የለውም፡፡
- እንደዚሁም ሟች ከሞተበት ወይም ከሳሹ በመብቱ መስራት ከቻለበት ቀን አንስቶ አስራ አምስት አመት ካለፈው በኋላ ከዘር የወረደ እርስት ካልሆነ በስተቀር የተባለውን የውርስ ጥያቄ ክስ በማናቸውም አስተያየት ቢሆን ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ይላል
ከዚህ ድንጋጌ እና ከዚህ ድንጋጌ ከፍ ብሎ በፍትሃብሄር ሕጉ ከተመለከተቱ ድንጋጌዎች በግልጽ መገንዘብ የሚቻለው ድንጋጌው የውርስ ንብረት የአላግባብ በሌላ ሰው ተይዞብኛል ወይም በውርስ ሕጉ መሠረት ሊጠበቅለት የሚገባው መብቱ በሌሎች ተይዞበት ከሆነ ይህንን መብቱን ወይም ንብረት ለማስጠበቅ የሚቀርብ ክስን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የኑዛዜ መጽናት እና ፈራሽ መሆንን የሚመለከት ስለመሆኑ ምንም የሚያመላከት የቃላትም ሆነ የይዘት አመላካች የለውም፡፡
ይህን ድንጋጌ ከኑዛዜ ይፍረስልኝ ጋር የምናገናኘው ኑዛዜ ስለነቀለኝ ይፍርስልኝ የሚል ክስ የሚቀርበው የውርስ ሃብት ለመጠየቅ ነው ብለን አስቀድመን ስለምናስብ ወይም ስለምንገምት ነው፡፡ ነገር ግን ኑዛዜ ነቅሎኛል ኑዛዜው ይፍረስልኝ ማለት አንድ ራሱን የቻለ የክስ ምክንየት ሲሆን የውርስ ንብረት መብት በሌለው ሰው ስለተያዘ ይለቀቅልኝ ወይም በውርስ የሚገባኝ ንብረት በሌላ ሰው ተይዞብኛል ለቆ ያስረክበኝ ደግሞ በንብረቱ ግምት ልክ ዳኝነት ተከፍሎበት የሚቀርብ ሌላ ራሱን የቻለ የክስ ምክንየት ነው፡፡ ስለሆነም ኑዛዜ ይሻርልኝ ለሚል ክስ ሁል ጊዜ የንብረት ይለቀቅልኝ ጥያቄ ታሳቢ ያደረገ ነው በሚል እሳቤ የኑዛዜ ይሻርልኝን ክስ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ጋር ልናገናኝ አይገባም፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ጉዳይ ኑዛዜው ተሽሮ ንብረቱ ሲጠየቅ የሚታይ ጉዳይ ነው እንጂ በኑዛዜ ይሻርልኝ ጥያቄው የሚስተናገድ አይደለም፡፡
ኑዛዜው ስለነቀለኝ ይሻርልኝ በሚል ክስ የሚቀርበው የይርጋ መቃወሚያ ከላይ እንደገልጽሁት የፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 ወይም 1845 ሲሆን ክሱ በእነዚህ የይርጋ ድንጋጌዎች የማይታገድ ከሆነ እና ኑዛዜው ከተሻረ የንብረት ይለቀቅልኝ ክስ ሲቀርብ ተከሳሹ በንብረቱ መልቀቅ እና ማስረከብ ክርክር ላይ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000`ን በመቃወሚያነት ሊያነሳ ይችላል፡፡
ሌላው ይህ ድንጋጌ የሚገኘው ልክ እንደ ፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 በውርስ ሕጉ ወራሽነትን ስለማጣራት በተደነገገው የሕጉ ክፍል በምዕራፍ 2 ስር ነው፡፡ ይህ የሕጉ ምእራፍ የፍ/ብ/ህ/ቁ. 974 እና 973 የተደነገጉበት ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽሁት ኑዛዜ ነቅሎኛል ይፍረስልኝ ለሚል ክስ የፍ/ብ/ህ/ቁ.974 እና 973 ውርሱ በተጣራ ጊዜ አግባብነት ያለው ነው፡፡ በአንድ ምእራፍ ስር ሕጉ ከውርስ በመነቀል ምክንየት ኑዛዜ እንዲፈርስ ለሚቀርብ ክስ በሁለት የተለያየ ቦታ ላይ የይርጋ ጊዜ የሚያስቀምጥበት ምክንየት የለም፡፡ በተጨማሪም በፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 የተቀመጠው የሶስት አመት እና የ አስራ አምስት ዓመት የይርጋ ጊዜ ነው፡፡ ከዘር የወረደ እርስት በአሁኑ ጊዜ ስለሌለ ሁሉም የውርስ ይገባኛል እና የውርስ ሃብት ይለቀቅልኝ ጥያቄዎች በእነዚህ የይርጋ ድንጋጌዎች የሚታዩ ናቸው፡፡ በዚህ ድንጋጌ ከተጠቀሱት ከሁለቱ የትኛው ነው የሚለውን የሰበር ችሎቱ አላየም፡፡ ስለሆነም በፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ላይ የተቀመጡት የሶስት አመትም ሆነ የአስራ አምስት አመት ይርጋዎች በኑዛዜ ተነቅያለሁ ኑዛዜው ይሻርልኝ ለሚል ክስ ተፈጻሚነት ስለሌላቸው የሰበር ችሎት በኑዛዜ ተነቅያለሁ ኑዛዜው ይሻርልኝ በሚል ለሚቀርብ ክስ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 የተመለከተው ነው በሚል የሰጠውን የሕግ ትርጉም ሊለውጥ ይገባል፡፡
ሌላው በተለያዩ የሰበር ውሳኔዎች የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 በወራሾች መካከል ለሚደረግ ክርክር ነው፡፡ ወራሽ በሆነ እና ባልሆነ መካከል የይርጋ ጊዜው 10 ዓመት ነው በሚል ስለተሰጡት አስገዳጅ ትርጉሞችም ግልጸኝት በጥቂቱ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ ሲታይ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 የሚያወራው ያለ ኑዛዜ ወራሽ ( ዘመዳሞች) ስለሆኑ ሰዎች ብቻ አይደለም ፡፡የፍ/ብ/ህ/ቁ 996 እርሱ ስለወራሾች የሚሰጥ የምስክር ወረቀቶች እና የወራሽነት ጥያቄ የሚል ነው፡፡ የወራሽነት ጥያቄ ማንሳት የሚችሉት እና ወራሾች የሚባሉት ያለ ኑዛዜ ወራሾች እንዲሁም ጠቅላላ የኑዛዜ ወራሾች እና ልዩ የኑዛዜ ወራሾች ናቸው፡፡ በተለይም የፍ/ብ/ህ/ቁ 1002 ከዚህ በላይ (ከፍ/ብ/ህ/ቁ 996-1001 ) የተደነገጉት ድንጋጌዎች ልዩ የኑዛዜ ስጦታ ለተደረገላቸው ሰዎችም ተፈጻሚዎች ናቸው ይላል፡፡ ልዩ የኑዛዜ ስጦታ የተደረገላቸው ሰዎች ደግሞ ሁል ጊዜ የሟች ያለኑዛዜ ወራሽ ናቸው ሊባሉ አይቻልም፡ከሟች ጋር ምንም የስጋ ዝምድና የሌለው የሟች ልዩ ኑዛዜ ስጦታ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡
ስለዚህ በአንዳንድ የሕግ ባለሙያወች እና ዳኞችም ጭምር የፍ/ብ/ህ/ቁ 1000 ተፈጻሚነት በ`ያለኑዛዜ ወራሾች (በሕግ ወራሾች) መካከል ለሚነሳ ክርክር ብቻ ነው የሚል የሚያዙት አቋም ምክንየታዊ አይደለም፡፡ ድንጋጌው በ`ያለኑዛዜ ወራሾች እና በጠቅላላ የኑዛዜ ወራሽ መካከል፤በልዩ ኑዛዜ ተጠቃሚ እና ካለኑዛዜ ወራሽ በሆኑ መካከል እንዲሁም በጠቅላላ የኑዛዜ ወራሾች እና በልዩ ኑዛዜ ተጠቃሚዎች መካከል ተፈጻሚነት ያለው ነው፡፡
ሌላው በኑዛዜ ስለተነቀልሁ ኑዛዜው ይሻርልኝ በሚል የሚቀርብ ክስ ላይ ተፈጻሚነት ያለው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1123 ላይ የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ነው በሚል የተሰጡት የሕግ ትርጉሞች ከፍ ብየ በዝርዝር እንደገለጽሁት የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1123 የሚመለከተው አውራሹ በህይወት እያለ ለተወላጆቹ ሃብቱን በሚያከፋፍልበት የስጦታ ውል ጊዜ እንጂ መነሻ ሃሳቡም ሆነ ጽንሰ ሃሳቡ ከኑዛዜ ስጦታ ጋር ለሚያያዝ የመነቀል ጉዳይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ ስለሆነም የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እነዚህ ትርጉሞች ሕጉን የተከተሉ ስላልሆኑ ሊለውጥ ይገባል፡፡
ማጠቃለያ
በጽሑፉ በተገለጹ ጉዳዮች ላይ የውርስ ሕግ አተረጓጎም እና አተገባበር ከሕጉ ወጥቶ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጣቸው ሕጉን መሠረት ባላደረጉ እና እርስ በእርስ በሚጣረሱ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች እየተመራ የሚገኝ ሲሆን እነዚህ አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች ወጥ ባለመሆናቸውም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተቋቋመበትን ወጥነት፣ ተገማችነት እና ተመሳሳይ የሕግ ትርጉም በሃገሪቷ እንዲኖር የማድረጉን አላማ እያሳኩ ባለመሆኑ እንዲሁም ለውርስ ክርክር ረጅም ጊዜ መውሰድ፤ አድካሚ እና አሰልቺ መሆን የሰበሩ አቋም እና ሕጉን የተከተለ ወጥ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አለመኖሩ አስተዋጽኦ ስላለው በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በተገለጸው የመፍትሄ ሃሳብ አግባብ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕጉ በሚፈቅደዉ አግባብ የሕግ ትርጉሞቹን ሊቀይር ወይም ሊያሻሽል ይገባል፡፡