ዓለማችን ላይ የፈረንጆቹ 2020 የተወሳሰቡ ችግሮችን ይዞባት መጥቷል፡፡ ከቻይና ውሃን በትንሹ ተነስቶ በወራት ውስጥ ዓለምን ካዳረሰው የኮሮና ቫይረስ የሚስተካከል ችግር ግን ይመጣል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ይህ ቫይረስ በቀጥታ በሰው ልጆች ጤና እና ህይዎት ላይ እያሰከተለ ከሚገኘው ኪሳራ እና ውድመት በሚስተካከል ደረጃ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም እያስከተለ ይገኛል፡፡ ከአሜሪካ ስቶክ ማርኬት እስከ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ከአውሮፓዊያኑ የንግድ ልውውጦች እስከ ኢትዮጵያ የአበባ ንግድ፤ ከካናድ የጥራጣሬ ግብይት እስከ አዲስ አበባ የአትክልት ተራ ንግድ ድረስ ብዙ መመስቃቀሎችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ በዚህ መመሰቃቀል ውስጥ ብዙ አካላት ተጎጂ የሚሆኑ ቢሆንም በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ተቀጥረው እንደሚሰሩ ሰራተኞች ግን የችግሩ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሽ አይገኝም፡፡ በተለይ ከአሜሪካ የቅጥር ገባያ እየሰማን እንዳለነው ብዙ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን እየቀነሱ እያጋጠማቸው ያለውን የገንዘብ እጥረት በማቃለል ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ በሀገሪቱ የሚገኘውን የሥራ አጥ ቁጥር ወደ ስላሳ በመቶ እያደረሰው ይገኛል፡፡ ይህ ችግር ወደ ኢትዮጵያ መከሰቱ የማይቀር ነው፡፡ ብዙ የግል ድርጅቶች ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ እያቆሙ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ የሠራተኛን የደሞዝ ወጪ ያለምንም ችግር የመሸፈን አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ይሄን ችግር ከግምት ውሰጥ በማስገባት የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት መጋቢት /2012 ዓ/ም ከአሠሪዎችና ሠራተኛ ማህበራት ጋር በመነጋገር አሠሪዎች በዚህ ወቅት ለሰራተኞቻቸው ወጥ የሆነ ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችል የኮቪድ 19 የሥራ ቦታ ምላሽ (workplace Response) የተመለከተ ፕሮቶኮል (ፕሮቶኮል ወይም ፕሮቶኮሉ) አውጥቷል፡፡ የዚህ ፕሮቶኮል መነሻ የዓለም ስራ ድርጅት (አይ.ኤል.ኦ) በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ ሀገራት እና የስራው ዓለም ሲጠቃ የቀውስ አስተዳደር ምላሽን በተመከተ በተቀመጠው ጋይድ ላይን መሰረት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ይህ አጭር ዳሰሳ ፕሮቶኮሉ በአሠሪዎች እና በሰራተኞች ላይ የሚጥለውን መብትና ግዴታ ከማየት ባለፈ የፕሮቶኮሉን ህጋዊ አንድምታ እና መሰል ጉዳዮችን አይዳስስም፡፡
- የፕሮቶኮሉ ዓላማ
የፕሮቶኮሉ አሠሪዎች ያላቸውን ህልውና ለማስቀጠል የሠራተኛ የደሞዝ ወጭን በመቀነስ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች እና ሰራተኞች ደግሞ በዚህ ወቅት ሊደርስባቸው የሚችለውን ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት የአሠሪውን ህልውና እና የሰራተኞችን ማህበራዊ ዋስትና በማመጣጠን ወጥ ምላሽን ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ በፕሮቶኮሉ ላይ እንደተጠቀሰው የቫይረሱን ወረርሽን ባስተማማኝ መልኩ ለመከላከል እና ወረርሽኙ ቢከሰት ጉዳትን ለመቀነስ እንዲሁም ወረርሽኙ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፤ በድርጅቶች ቀጣይነትና ህልውና እና በሠራተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚፈጠረውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ ነው፡፡
- የአሠሪ ግዴታዎች
የወረርሽኙን የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ
በፕሮቶኮሉ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የአሠሪዎች የመጀመሪያ ግዴታ የሚጀምረው የቫይረሱን መስፋፋት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እርምጃዎች በመውሰድ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ማንኛውም አሠሪ የሚከተሉትን የመከላከያ እርምጃዎች የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡
- የውሃና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን አቅርቦት ማረጋገጥ፤
- የአፍና አፍንጫ መሰፈኛ ማቅረብ ስለ አጠቃቀሙ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ፤
- በድርጅቱ ሃላፊ የሚመራ የሰራተኞች ማህበር አባል የሚሆንበት የኮሮና ቫይረስ ቁጥጥርን የሚመራና የሚከታተል ኮሚቴ ማቋቋም፤
- ሰራተኞች በተጠጋጋ ሁኔታ የሚሰሩባቸውን ቦታዎች በመለየት አሰራሩን ለማስቀረት ወይም ለመቀየር መሞከር፤
- በሰራተኞች የትራንስፖርት ስርቪሶች ላይ መጨናነቅን ማስወገድ አስፈላጊውን የንጽህና ጥንቃቄ ማድረግ እንዲሁም በጉዞ ወቅት መስኮቶችን ክፍት እንዲደረጉ ማድረግ፤
- ስለ ኮሮና ቫይረስ ግንዛቤ ማስጨበጫ የሚያግዙ ሰራተኞች በሚገባቸው ቋንቋ ፖስተሮች፤ የጥንቃቄ ምልክቶች፤ የመከላከያ ዘዴዎችን በፁሁፍ፤ በስዕል፤ በድምጽና በምስል በታገዘ ሁኔታ ማቅረብ፤
- የካፍቴሪያ አገልግሎት ለሰራተኞቻቸው የሚያቀርቡ ድርጅቶች የአገልግሎት ስአቱን በማስረዘም የተጠቃሚ ሰራተኞችን ቅርርብ መቀነስ፤
- ድርጅቶች ስብሰባዎችን በማስቀረት በተቻለ መጠን ግንኙነትን በኢንተርኔት፤ በኢሜል ወይም በስልክ ማድረግ፤
- የድርጅት ሀላፊዎች ከሠራተኛ ማህበራት ጋር በመመካከር የኮሮና ቫይረስ ክትትል፤ ቁጥጥር እና ሪፖርት ስርዓት መዘርጋት፤
- የሠራተኛ ገዴታዎች
ሰራተኞች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚወሰዱ እርምጃዎችን የመከተል እና የመፈፀም ዝርዝር ግደታዎች በፕሮቶኮሉ ውስጥ ተካተዋል፡፡
- ሊወሰዱ የሚገባቸው ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች
ከላይ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከተቀመጡ የመከላከያ እርምጃዎች ባለፈ ፕሮቶኮሉ አሠሪዎች ሊወሰዱ የሚገባቸውን ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም የፕሮቶኮሉ አሠሪዎች ያላቸውን ህልውና ለማስቀጠል የሚወስዷቸውን እርምጃዎች እና ሰራተኞች ደግሞ በዚህ ወቅት ሊደርስባቸው የሚችለውን ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ያጣጥማሉ የሚላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን አሠሪዎችና እና ሰራተኞች በእነዚህ ጉዳዮች የመገዛት ግዴታ ያላቸው ቢሆንም ፕሮቶኮሉ አሠሪዎች እንደተሰማሩበት ሴክተርና ሁኔታ አንፃር የራሳቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲያቀርቡ ያበረታታል፡፡ በዚህ መሰረት የሚከተሉት ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰድ እንደሚኖርባቸው በፕሮቶኮሉ ውስጥ ተካቷል፡፡
- የድርጅቶች ቀውስን የመቋቋም ችሎታ እና ምላሽ የመስጠት አቅም ከድርጅት ድርጅት እንዲሁም ከሴክተር ሴክተር የሚለያይ በመሆኑ መፍትሄዎች ከድርጅቶቹ እንዲመነጭ ከማድረግ ባሻገር በሶስተኛ ወገን የቀረበውን የጋራ ቢደረግ፤
- ያልተቋጩ አዲስ ህብረት ስምምነት ድርድሮች ባሉበት ሁኔታ ለሚቀጥሉት አስራ ሁለት ወራት እንዲቋረጡ፤
- ተግባራዊ ያልተደረጉ የደመወዝ ጭማሪ ለሚቀጥሉት 12 ወራት ተግባራዊ እንዳይደረጉ፤
- ተግባራዊ ሲደረጉ የነበሩ የተለያዩ አበሎች (የበረሀ አበል፤ የትራንስፖርትና የቤት አበል)፤ ጉርሻ፤ የምርት ቅምሻ፤ ኮሚሺን፤ እና ሌሎች እንደ ደመወዝ የማይቆጠሩ ክፍያዎች ችግሩ ሙሉ ለሙሉ እስኪቀረፍ እንዳይፈፀሙ ቢደረግ፤
- በአሠሪዎችና በሠራተኛ ማህበራት ውይይት መነሻነት ድርጅቱን ለማቆየት ሲባል በስራ ላይ የሚገኘውን የደመወዝ እስኬል የመከለስና ውጤቱን ተግባራዊ ማድረግ፤
- ሰራተኞች ያልተጠቀሙበት የዓመት እረፍታቸውን እንዲጠቀሙ ማድረግ እና እረፍታቸውን ተጠቅመው የጨረሱ ካሉ ከቀጣይ ዓመታት የእረፍት ጊዜ ቢያንስ ግማሹን እየተጠቀሙ በክፍያ እንዲቆዩ ማድረግ፤
- እጅግ አስፈላጊ ባልሆኑ የድርጅት ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች ለጊዜው የተወሰነ ብድር በመስጠት ሁኔታዎች ሲሻሻሉ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የጹሁፍ ማረጋገጫ መስጠት፤
- ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች በሀገር ውስጥ ገባያ እንዲሸጡ ፈቃድ መስጠትና ሰራተኞችን በሥራ ላይ ማቆየት
- አቅም በፈቀደ መጠን ማህበራዊ ኃላፊነትን ድርጅቶች እንዲወጡ በተለያየ ደረጃ የተዋቀሩ የአሠሪና ሠራተኛ ማህበራት አባሎቻቸውን የማበረታታትና በቅንጅት መስራት
ማጠቃላያ
ፕሮቶኮሉ አለማችን አሁን ያለችብን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ በማደረግ የሰጠው ወቅታዊ ምላሽ ነው፡፡ ፕሮቶኮሉ እንደመመሪያ ሊታይ ይገባዋል ወይስ ምክረ ሃሳብ ነው? ፕሮቶኮሉ ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ጋር በምን አይነት መልኩ ሊጣጣም ይችላል? የአዋጁ ድንጋጌዎች በእንደዚህ አይነት ሁነታዎች የሚገደቡበት የህግ አግባብ ተቀምጧል ወይ? እነዚህንና መሰል ህጋዊ ጥያቄዎችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም በፕሮቶኮሉ ማጠቃላያ ላይ እንደተጠቀሰው ፕሮቶኮሉ ህጋዊ ውጤት ያለውና ሁሉም አሠሪዎችና ሰራተኞች ሊከተሉት የሚገባ ሰነድ ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ጥያቄዎች ቢኖሩም ሰነዱ ሀገራችን በአሁኑ ሰዓት ያለችበትን ሁለንተናዊ ውጥንቅጥ ከከተታት ጉዳዮች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ችግር ውስጥ ሊጥላት የሚችለውን የአሠሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት በመጠኑም ቢሆን ሊያቃልል የሚችል ተግባር በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡