በሀገራችን ህዝባዊ አመጽን ተከትሎ በሰኔ 2010 ዓ.ም ብትረ መንግሥቱን የሚዘውረው የብልጽግና ፓርቲ ለአመጹ ምክንያት የሆኑትን የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ለመመለስ የተቋም ግንባታ እና የህግ ለውጦችን እያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ከኦሮሚያ እና አማራ ብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በቅርቡ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሕገ-መንግሥቱን በጋራ እንዲሻሻል ለማድረግ የሚሰሩ ስለመሆኑ ተፈራርመዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲሚሻሻሉ በጋራ የተስማሙባቸው የሕገ-መንግሥት የአንቀጾች ዝርዝር ላይ ስምምነት ላይ አልደረሱም(ወይም ለህዝብ ሊገልጹት አልፈለጉም)፡፡
ነገር ግን በመግባቢያው ሰነድ ላይ ከፈረሙት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከጥቂት የሕገ-መንግሥት ምሁራን እንዲሻሻል ጥያቄ የሚቀርብበት አንዱ ድንጋጌ የሕገ-መንግሥት አንቀጽ 62(1) የሆነውና “ሕገ-መንግሥትን የመተርጓም” እና በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን ከምክር ቤቱ ተወስዶ የሕገ-መንግሥት ጉዳይን የሚያይና የሚወስን የሕገ-መንግሥት ፍ/ቤት እንዲቋቋም በማለት ባህር አቋርጠው የምዕራቡንና የምስራቁም ልምድ በማስረጃነት በመጥቀስ በሀገራችንም ይህ ተግባራዊ እንዲሆን እየሞገቱ ይገኛሉ፡፡
ለመሆኑ ይህ ማነጻጸሪያ ሆኖ የቀረቡት ልምዶችነ ለሀገራችን ቁመና የማይሆኑ ጥብቆ ስለመሆናቸው እና ውጤታቸውም ብሔርና ብሔረሰቦችን በብርቅዬ ልጆቻቸውን መስዋዕት በማድረግ ከዘመናት ትግል በኃላ ያገኙትን የልዑላዊነት(Sovereignty) መብት መቃብር የሚከት ስለመሆኑ በዚህ አጭር ጽሁፍ አስዳስሳለሁ፡፡ ተከተሉኝማ….
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ታሪካዊ ዳራ
የዘመናዊዉ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት በባለ 3000 ዓመቱ የአቢሲኒያ ዘውዳዊ አገዛዝ እና በ238ኛው ንጉሰ-ነገስቱ አጼ(ጤ) ሚኒሊክ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ስዩመ-እግዚአብሔር በሆነው አኃዳዊ አገዛዝ(የቀ.ኃ.ስላሴ መንግሥት) ላይ የብሔር እና የመደብ ተቃውሞ በእነ ጀነራል ዋቆ ጉቱ፣ታደሰ ብሩ፣ መንግሰቱ ነዋይ፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ብርሀኑ ደንቄ ፣ወርቅነህ ገበየሁ፣ በባሌ፣በወላይታ፣በኤርትራ እና በትግራይ ህዝብና ገዢዎች አማካኝነት ሲለኮስ ቆይቷል፡፡ ዋለልኝ መኮንን ደግሞ “The Question of Nation & Nationalities in Ethiopia” በሚለው አጭር ጽሁፍ ላይ ‘ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት’ ናት ሲል በሰጠው መደምደሚያ ይህን የብሔር ጥያቄ ወደ የዩኒቨርስቲ የተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደ አንድ የትግል አጀንዳ አድርጎ እንዲገባ በማድረግ ቀድሞ የተለኮሰውን እሳት በሶሻሊስት ማርገብገብያ አቀጣጠለው፡፡ ዋለልኝ መኮንንን የብሔር ጭቆና ጥያቄ ወለደው እንጂ ዋለልኝ መኮንን የብሔር እኩልነት ጥያቄን አልወለደውም፡፡
ግና በተማሪዎች ፖለቲካ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ያደጉትን የግራ ዘመም ፖለቲካ ፓርቲዎች(መኢሶን/ኢህአፓ) በርዕዮተ-ዓለም አንድ ሆነው ለአንድ ዓለማና ህዝብ ተሰልፈው በጋራ ለመስራት መግባባት አቅቷቸው ግልግልና ድርድር ላይ ሳሉ በህዝቡ ውስጥ ያቀጣጠሉት እሳተ-ጎመራ ፈንድቶ ትግሉን በአስራ አንደኛው ሰዓት በጠለፈው የበታች መኮንኖች ስብስብ ‘ደርግ’ የ3000ዘመን ዘውዳዊ አገዛዝን 'ግብዓተ መሬት ተፈጸመ፡፡ የእነዚህ የብሔር ጭቆናን ከህዝባችን ላይ አራግፈን እኩልነት እንተክላለን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የሆኑት ኃይሌ ፊዳና ብርሀነ መስቀል ረዳም በህይወት ሳሉ ሳይግባቡ በመቃብራቸው አንድ እርምጃ እርቀት ላይ ከረፈደ ተስማምተው በአንድ ጉድጓድ ተቀብረው ግዑዝ አካላቸው አንድ ዐፈር ሆነ፡፡ ህያው አካልና እስትንፋሳቸው አንድ ሆኖ ቢሆን ኖሮ የሚለው ዛሬም ’ያ ትውልድ’ን ሰንቆ የያዘ የእግር እሳት የሆነ ቁጭት ነው፡፡
የወታደር ስብስብ የሆነው ደርግም የሽግግር መንግሥት አቋቁሞ ወደ ካምፕ ይመለሳል ቢባልም የግራ ዘመሙን ርዕዮተ ዓለም ግራ በገባው መንገድ ተረድቶት በኢትዮጵያ ያለው የመደብ ጭቆና ነው፤ ለመደብ ጭቆና የምንሰጠው ምላሽ የብሔር ጭቆናን ይመልሳል ብሎ መሬት ላራሹ ፣ዕድገት በህብረት እና የቀይ ኮከብ ዘመቻ እያለ ቢዘምትም፤ የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲቲዩት በማቋቋም በሀገሪቷ ያሉትን የብሔርና ብሔረሰቦች ብዛት ቆጥሮና መዝግቦ ከመያዝ ባለፈና በቋንቋቸው ለማስተማር ዳዴ ብሎ ለጊዜው የብሔር ጥያቄን ተንፈስ ያደረገ ቢመስልም የስልጣን ወንበሩን ያደላደለ በመሰለ ጊዜው ወደ ኃላ በማፈግፈግ የሀገሪቷን አንድነት ህዝቡን አንድ( Unity with Uniformity) በማድረግ አረጋግጣለሁ ብሎ ቀድሞ የተጨቆነውን የብሔሮች የእኩልነት መብት ገድሎ ሊቀብረው ፈለገ፡፡
ይህን የተቃወሙትና ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የተመሰረተችው በብሔር ጭቆና/ የቀኝ ግዛት ነው ብለው ነፍጥ አንግበው “ነገ እልፍ እንሆናለን “ በማለት የትግራይ እና የኦሮሞ ወጣቶችም ህወኃት(ህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ) እና ኦነግ(ኦሮሞ ነጻነት ግንባር) የተሰኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ግንባር ቀደም ቢሆኑም በኃላ ላይ እልፍ የብሔርና ብሔረሰብ ተወካዮችና ፓርቲዎችን በማስተባበር ከ17 ዓመታት የጦር ውጊያ በኃላ ወታደራዊ ጁንታውን ወደ ዚምባብዌ ልከው መንግሥተ ስልጣኑን ተቆጣጠሩት፡፡
በሀገራችን የነበረውን የብሔሮች ጭቆናን ዕውቅና በመስጠት እና በዘመናዊው የሀገር ምስረታው ውስጥ ሁሉም ብሔሮች ሚና ያልነበራቸው በመሆኑ(ጥቂት ሰዎች እንደ ግለሰብ ተሳትፈዋል) በአዲስ መልክ በፍቃዳቸው ተባብረው እና ተጋግዘው የብሔሮችና ኃይማኖት እኩልነት የሰፈነበት፣ዲሞክራሲ የተረጋገጠበት፣ሰላም የበዛበት እና የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት የፖለቲካና የህግ የቃል-ኪዳን ሰነድ የሆነውን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥትን በ1987ዓ.ም አጸደቁ፡፡ ይህ ሰነድ ለብሔር፣ብሔረሰብና ህዝቦች የሉዓላዊነት ስልጣን የሰጠ በመሆኑ እና እራስን በመራስ የማስተዳደር መብታቸው እስከ መገንጠል ድረስ ያከበረ በመሆኑ፤ ማንም ብሔር ማንንም እንዳይጨቁን ዋስትና በመስጠት ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ታላቅ የመተማመኛ ሰነድ ነው፡፡(የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሰት አ.ቁ 8 እና 39)
የኢፌዲሪ የፌዴሬሺን ምክር ቤት
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት በዘረጋው ፓርላመንታሪ የመንግሥት ስርዓት ውስጥ ፓርላማው ሁለት ምክር ቤቶች ሲኖሩት አንደኛው ህግ አውጪ የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሕገ-መንግሥትን የመተርጓም ስልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡
ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሀገሪቱ የበላይ ህግ እና የፖለቲካ የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነውን ሕገ-መንግሥት እንዲተረጉም ስልጣን ሊሰጠው የቻለባትን ጥቂት ምክንያቶችን አጠር አድርጌ አቀርባለሁ፡-
1ኛ/ ተቋማዊ መዋቅር( Institutional structure)
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ሁሉም ብሔር በሔረሰቦች እና ህዝቦች ውስጥ ተመርጠው የተላኩ እንደራሴዎችን የያዘ ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም ከላይ የሕገ-መንግሥቱን ታሪካዊ ዳራ በጥቂቱ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት ይህን ሕገ-መንግሥት ተፈራርመው ያጸደቁት ደግሞ እኚሁ ብሔር እና ብሔረሰቦች በመሆናቸው በሕገ-መንግሰቱ ላይ ለሚነሱ ማንኛውም ቅራኔና አለመግባባቶች ሕገ-መንግሥቱን ከጻፍት እና ተወያይተው ካጸደቁት በላይ የሚያውቅም ሆነ ሊያውቅ የሚችል ሊኖር ስለማይችል ሕገ-መንግሥቱን የመተርጓም ስራ በብቸኝነት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መሰጠቱ ተገቢ ነው፡፡
2ኛ/ የሕገ-መንግሥት ባህሪ( Feature of Constitution)-
ሕገ-መንግሥትን ከሌሎች ህጎች የሚለዩት ባህሪያት መካከል ዋናውና አንደኛው የሕገ-መንግሥት ሰነዱ የህግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መተማመኛ ሰነድ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ህግን ብቻ እንዲተረጉሙ ስልጣን የተሰጣቸው እና በህግ ሙያ ላይ ብቻ የሰለጠኑ ዳኞች የፖለቲካ ሰነድን ሊተረጉሙ አይገባም፡፡ ነገር ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የህግ ባለሙያዎች ስብስብ የሆነው የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ህግን በተመለከተ ለሚነሳ ሀሳብ የሙያ ማብራሪያ እንዲያቀርብለት በሕገ-መንግሥቱ ስለተቋቋመ ሕገ-መንግሥትን ለመተርጓም ከማንም በላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት ተመራጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
3ኛ/ ዲሞክራሲያዊ(Democracy)-
በየትም ሀገር ዘላቂ ሰላም፣የኢኮኖሚና ማህበራዊ ብልጽግናን ለመትከል ለሚደረገው ርብርብ ዋናውና መሰረቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መዘርጋት ነው፡፡ የዲሞክራሲ ግልጽና አጭሩ ትርጓሜ ደግሞ በብዙሀን ህዝብ ድምጽ መተዳደር( “the rule of majority”) ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያየው የተደረገው ከየብሔሩ በየአንድ ሚሊዮኑ ህዝብ ቁጥር አንድ ተወካይ ወይም-----ሰለሚኖር የአንድ አባል ድምጽ የአንድ ሚሊዮን የብሔሩን ተወካይ ድምጽ ስለሚይዝ በብዙሀን ድምጽ የመተዳደር የዲሞክራሲ ግንባታን እውን ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ይህን ስልጣን ለፍ/ቤት ከተሰጠው ጉዳዩን የሚያዩት ጥቂት ዳኞች ብቻ ከመሆናቸው ባሻገር ዳኞቹ በህዝብ ያልተመረጡና እራሳቻውን ብቻ የሚወክሉ በመሆኑ የዲሞክራሲ ግንባታውን ፈራሽ ያደርገዋል፡፡
4ኛ/ ታሪካዊ (Historically)
የ3000ዓመት ዕድሜ አላት በምትባለው አቢሲኒያ/ኢትዮጵያ፤ ታሪክ ተብሎ በመዛግብት ተከትቦ አንድም በቤተ-መጽሀፍት አልያም በቤተ-ትምህርት/በፊደል ቤት አገልግሎት ላይ እየዋሉ የሚገኙት ድርሳናት እንደ ሚያስረዱት ኢትዮጵያውያን የሀገር ድንበርን ለመጠበቅና ልዑላዊነትን ለማስከበር ከውጪ ኃይሎች ጋር ያደረጉት ጦርነቶች እርስ በእርስ ካደረጉት ጦርነት ጋር ሲነጻጸር በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነርሱም፡- በአክሱማዊ ዘመነ-መንግሥት ቀይ-ባህርን አቋርጠን ከአሁኖቹ የመን ጋር፤በንጉሰ ነገሰት ፀርጸ-ድንግል ዘመነ መንግሥት የቀድሞ የኦቶማን ንጉስ የአሁኑ ቱርክ ምጽዎ ወደብን በመውረራቸው የተደረገው ጦርነት፣በአጼ ቴዎድርስ ዘመነ-መንግሰት ከእንግሊዞች ፤በአጼ ዩሀንስ ዘመነ-መንግሥት የጉንደት ጦርነትን ጨምሮ ከግብጽ ጋር ሁለት ጊዜ እና ከአሁኑ ሱዳን ከቀድሞ ደርቡሾች ጋር፤ በአጼ ሚኒሊክ እና አጼ ኃይለስላሴ ዘመነ-መንግሥት የአድዎን ጦርነት ጨምሮ ከኢጣሊያን ጋር ሁለት ጊዜ፤ በዘመነ-መንግሥቱ ኃይለማርያም ከዚያድባሬው ሶማሊያ ጋር የተደረገው እና በዘመነ-መለስ ዜናዊ የባድመ ጦርነት የሚባለው ከኤርትራ ጋር የተደረገው በመጨረሻም “No War No Peace” ተብሎ ፋይሉ የተዘጋው ጦርነት ነው፡፡ በእርግጥ ይህን የተዘጋ ፋይልን ከፍተው ሰላምን አስፍነው ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት በመላካቸው ቀዳማዊ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነው እንደ ሀገር ኮራ እንደ ዜጋ ቀና ያደረገን ታሪክ መጻፋቸው የቅርብ ቀን ትዝታችን ሁሌም ይዘን የምንዞረው የደስታ ጥላችን ነው፡፡
ከእነዚህ ጥቂት ጦርነቶች በስተቀር አጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የተመዘገበው የእርስ በእርስ ጦርነቶች ሲሆኑ ዓላማቸውም ለዘውድ፤ ለተፈጥሮ ሀብት ቅርምት፣ ማንነትን በማጥፋት የብሔርና የሀይማኖት የበላይነትን በመትከል እና ግዛት በማስፋፋት ‘አንድ ሀገር፣ አንድ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ እና አንድ ዓይነት ሀይማኖት ተከታይ’ ለማድረግ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “ኢትዮጵያውያን ሁል ጊዜም የውስጥ ብሔራዊ መግባባት የሌለንና ከእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት የጸዳን አይደለንም” ማለታቸው፡፡
ይህም በመሆኑ በሀገራችን ዛሬም የብሔር ግንባታ ገና ዳዴ በሚልበት ወቅት ሲሆን ከላይ እንደተመለከተው ደግሞ የቀድሞ ታሪካች አንዱ የአንዱ ጠላት የነበረና ዛሬም በብሔርተኛውና በቀድሞ ስርዓት ናፋቂው( radicals and reactionaries) መካከል ባለ የእርስ በእርስ መፈራራትና መጠባበቅ በሰፈነበት ሀገራችን ውስጥ ብሔርና ብሔረሰቦች ልዑልነታዊያቸውን አረጋግጠው የበላይ ህግ ያደረጉትን የፖለቲካ የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነውን ሕገ-መንግሥት የመተርጓም እና በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣንን ከራሳቸው ከብሔረሰቦቻቸው ተወካይ ውጪ በማድረግ በታሪክ አጋጣሚ የመማር ዕድል ላገኘው የህግ ምሁር አሳልፈው የሚሰጡበት መተማመኛ ሊኖር አይችልም፡፡ የህግ ምሁሩም እንደማንኛውም ሰው ብሔር ያለው ከማህረሰቡ የተገኘ በመሆኑ ነገሩን ከብሔሩ በጸዳ መልኩ አይቶ በገለልተኛነት ውሳኔ ሊሰጥበት የሚችልበት አግባብ አነስተኛ ሲሆን ብሔርና ብሔረሰቦችም ይህን ዋስትናቸው የሆነን ሕገ-መንግሥት የመተርጓም ስልጣን ለጥቂት የህግ ባለሙያዎች መስጠት ሀገራችን ያለችበትን ያለመግባባትና ውጥረት በማክረር ወደ ግጭትና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያመራት የሚያደርግ ነው የሚሆነው፡፡
5ኛ/ ፖለቲካዊ (Political)
ማንም ግለሰብ እንደ ሰው ሰብአዊ፤ ዲሞክራሲያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦችም ዲሞክራሲያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች አሏቸው፡፡ ሀገርም እንደ ሀገር ልትቆም የምትችለው ግሰለቡን እንደ ሰው ብሔርና ብሔረሰቦችን ደግሞ ያላቸውን መብቶች ያከበሩ እንደሆኑ ብቻ ነው፡፡ በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን እንደሚታወቀው ሌሎች መብቶች ሁሉ ሊከበሩ የሚችሉት በቅድሚያ ፖለቲካዊ መብት የተከበረ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ስልጣኑን የያዘው አካል በሌሎቹ ሰብአዊ፤ዲሞክራሲያዊ እና ማህበራዊ መብቶች ላይ የመወሰን ስልጣን ያለው ነው፡፡
በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የብሔር እኩልነት ባልተከበረበትና የብሔር እና የኃይማኖት የበላይነት ውጊያ ታሪኳ ለሆነ ሀገር፤ የሁሉ ነገር መነሻ የብሔር እና ብሔረሰቦችን ፖለቲካዊ መብትን ማስከበር ነው፡፡ ሌላው የግለሰብ መብትም ሆነ ሌሎቹ መብቶች ይህን መበት ተከትሎው የሚመጡ እንጂ ሊቀድሙ የሚችሉበት ሁናቴ የለም፡፡ በሀገራችን የብሔረሰቦችን መብት መርገጡን ህልውናቸውን ሊያጠፋ ከጫፍ ማድረሱ ጸሀይ የሞቀ ዓለም ያወቀውታሪካችን ነው፡፡ በመሆኑም ብሔርና ብሔረሰቦች በዘመናት ትግል ያገኙትን የፖለቲካ መብት የሆነውን ሕገ-መንግሥት የመተረጓም መብት በህግ ባለሙያዎች ብቻ ለሚዘወር ፍ/ቤቶች አሳልፎ መስጠቱ እራስን በራስ ማጥፈት(political suicide) ነው፡፡
ማጠቃለያ
ከሀገራችን ቁመና ጋር ተለክተው ያልተሰፍ የምዕራብና የምስራቅ የርዕዮተ-ዓለም ጥብቆን ተውሰው የፓለቲካ ነጻነትን እና የዲሞክራሲ ግንባታን በኢትዮጵያ የብሔር ግንባታ ላይ እንተክላለን በማለት የአንድ እናት ልጆች ፣ በአንድ ወንበር ተቀምጠው ትምህርት የቀሰሙ እና ከአንድ ማዕድ ተጎራርሰው የበሉ ወንድማማቾች ፤ቡድን መስርተው ጠርዝ ይዘው ፣ነፍጥ አንግበው በከተማና የጫካ ወጊያ ተፋጅተው፤ ኢትዮጵያን የአኬልዳማው የደም ምድር፣ ወላጆችን በሀዘን አጉብጦ በእንባ ብዛት ዓይናቸው ጠፍቶ ተስፋቸው ተሰርቆ ሀኪም በሌለው የብቸኝነት በሽታ ተይዘው ወደ መቃብር ማውረዳቸው ዛሬም ያልጠገገ ቁስላችን፤ ያልደረቀ ጠባሳችን፤ ያላገገምንበት ስብራታችን ፤ ወገሻ ያጣንለት የልብ ወለምታችን እና አልቅሰን ያልጨረሰነው ሀዘናችን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ምድሪቷ የወጣት ደምን ጠጥታ፤ በእናቶች እንባ ታጥባ እና በአባቶች ጸሎት ከፈጣሪ ምህረት ብትቀበልም ዛሬም በሀገሬ ብሔር-ግንባታው ገና ፋቅ አለ እንጂ ዳዴ ለማለት የሚያስችል እግር አላወጣም፡፡
ዛሬም ዕውቀት ዘለቀኝ ያለው የሕገ-መንግሥት ምሁራን የሕገ-መንግሥት ጥያቄዎችና አለመግባባቶችን የሚፈታ የሕገ-መንግሥት ፍርድ ቤት ሊቋቋም ያስፈልጋል ሲል እየሞገተ ከሀገራችን ንባራዊ ሁናቴ፣ ታሪክ ፣ የብሔር ጭቆና እና ፖለቲካ ጋር የማይገጥመውን ልማድ ባህር ተሻግሮ ተውሶ ሕገ-መንግሥቱ እንዲሻሻል ሀሳብ ማቅረቡ ጦርነት መጋበዝ፣ ሀገር ማፈራረስን ማዋለድ እና የኢትዮጵያ እናቶችን ድጋሚ ለለቅሶ መጋበዝ መሆኑን የህግ መንግሥት ምሁር የሆነው ZIYAD MOTALA በ ‘CONSTITUTIONAL OPTIONS FOR A DEMOCRATIC SOUTH AFRICA’ በሚለው ጽሁፍ እንደሚከተለው ያስረዳል፡-
“History has shown that institutional transfer of a constitution from one country to another, without considering the objective conditions in the society where one attempts to transplant the constitution, presents a recipe for disaster."“ሕገ-መንግሥቱ ግልጽ ሊያደርገው የፈለገውን እና በሀገሪቷ ውስጥ ድንጋጌው የወጣበትን ዓላማ እና ሁናቴዎች ከግንዛቤ ሳያስገቡ ከአንድ ሀገር ተወስዶ በሌላ ሀገር ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚደረጉ ሕገ-መንግሥታዊ የተቋም ለውጦች የጥፋት ቅመም መሆናቸውን ታሪክ አሳይቶናል”
ስለዚህ የሀገሬ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብዙ ትግል በእልፍ መስዋትነት ያስከበራችሁትን ሕገ-መንግሥትን የመተርጓም ሎዐላዊ ፖለቲካዊ መብት በሕገ-መንግሥቱ የመሻሻል ሂደት ውስጥ በጦር ትግል ያስመሰከራችሁትን ድል በፖለቲካዊ መድረክ በመድገም በድጋሚ እንዲያስከብሩት አደራ እላለሁ፡፡ ይህን የብሔሮች ልዑላዊነት ስልጣን መሻር ወይም መቀነስ እና መግረዝ የሚያስከፍለው ዋጋ መተኪያ የሌለው ስለሆነ በዚህ የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ላይ ከሀገሬ ሁናቴ ጋር የማይጋባ የባህር ማዶ ልምድን ተውሳችሁ ሀሳብ የምታቀርቡ ባለሙያዎች ሀሳባችሁ ወደ ሀገር ውስጥ ሳይገባ የሀገሬን አፈር ከእግሩ አራግፋችሁ ከድንበሬ አስወግዱት፡፡ እናንተም ሀገሬን ላራቆታት ችግር የሀገሬን ኩታ ደርባችሁ ችግሩን ፍቱ፤ መፍትሔ ለመፈለግ ባህር ማዶ የሚያማትረው ዓይናችሁም ይሰብሰብ፡፡
አመሰግናለሁ!