By Yohannes Eneyew Ayalew on Monday, 15 May 2017
Category: Construction Law Blog

አስገዳጁ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ የሕንጻ መደርመስን ይከላከለው ይሆን?

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነው ጉዳይ ልክ የዛሬ አመት ገደማ በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ልዩ ስሙ ሰሚት በሚባል ስፍራ የተደረመሰውን ህንጻ እና እሱን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው ደብዳቤ (circular) መሰረት አስገዳጅ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ በድጋሜ እንዲኖር መደረጉን በማስመልከት ነው፡፡ ኢንሹራንስ (መድን) የሚለው ቃል ሲነሳ ምንግዜም ቢሆን ሊዘነጋ የማይችለውጉዳይ የአደጋ (risk) መኖር ነው፡፡ የአደጋ መከሰት ለመድን ቅድመ ሁኔታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ስለ መድን ታሪክ በአጭሩ ለመናገር ስነሳ አባይን በጭልፋ ኢንዲሉ! በጥቅቱ ጠቆም ለማድረግ ያህል የሚከተለውን ዐረፍተ ነገር እጽፋለሁ፡፡ በአለማችን ጥንታዊ የሚባለው መድንበ3ሺህ ዓ.ዓ ቻይናዊያን የጀመሩት ሲሆኑ በወቅቱም ነጋዲያን በሸቀጦቻቸው ላይ በአንድ ማጓጓዢያ እቃ መጫን እና መጠቀም የሚደርሰውን አደጋ ብሎም የሚመጡ የጎርፋ እና መሰል አደጋወችን ለመከላከል በርካታ የማጓጓዣ አማራጮች በወሰዱ ማግስት ነበር፡፡ ከዚያም በሜሶፖታሚያ (ሳምራዊያን) ስልጣኔ ወቅት እየተስፋፋ መመጣቱ በድርሳናት ላይ ሰፍሯል፡፡ በተለይም እኤአ በ1750 ዓ.ዓ በሰፈረው የንጉስ ሐሙራቢ ሕግ እንደተመለከተው ነጋድያን በባህር በሚነግዱበት ወቅት እቃውን በጥሩ ሁኔታ እንዲደርስ አስቀድመው በብድር ያስጭናሉ፤ እቃውም በጥሩ ሁኔታ ከደረሰ ለአበዳሪው ተጨማሪ ገንዘብ ጭምር እንደሚከፍል ይናገራል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዕቃው ቢጠፋ ወይም ቢዘረፍ የአበዳሪው ዋስትና ሙሉ ኃላፊነት ነው፡፡ (ቫውግሃን፡1997፡3) ከዚያም በኋላ በሜዲትራንያን ባህር የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴወች ከነጋዲያን አስቀድሞ በተሰበሰበ አረቦን/Premium/ ለሚደርሱ የባህር ላይ ንግድ አደጋወች ማካካሻ ተደርገው ሲሰራባቸው ቆይቷል፡፡

በመካከለኛው ዘመንም በጥናታዊቷ የጣሊያን ዋጀንዋ ከተማ እኤአ በ1347 የመጀመሪያው ዘመናዊ የመድን ውል በሥራ ላይ ዋለ፡፡ ከዚህም የተነሳ መድን ከሌሎች ዓይነት የፍትሃብሄር ድርጊቶች ለመለየት ተሞክሯል፡፡ (ፍራንክሊን፡2001፡274)

ስለ መድን ውል በጠቅላላው ሲታሰብ ከትልቀቱ እና ስፋቱ የተነሳ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚኖሩ የታመነ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መድን ሕግ እና ውሎች ዙሪያ በርካታ አሳሳቢ ችግሮች አሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ እንኳንስ በሁለቱም ማለትም በሕግ እና በውሎች ዙሪያ ቀርቶ ከውሎች ውስጥ ጥቂቶችን በሚገባ ተመርጠው በአግባቡ ቢፈተሹ ብዙ አሳሳቢ ችግሮች እንደሚገኙባቸው የሚያከራክር አይደለም፡፡ (ዘካሪያስ ቀንዓ፡1998፡1)

የመድን ውል ዓይነቶች በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም የህይወት መድን፣የንብረት መድን፣የአደጋ መድን፣የባህር መድን፣የኮንስተራክሽን መድን ወ.ዘ.ተ በፖሊሲው የተመለከተውን ስያሜ በመያዝ ይጠራል፡፡

የኮንስትራክሽን መድን የሚባለውም በግንባታ ወቅት ለሚደርሱ አደጋወች እንዲሁም ጉዳቶች በአሰሪው ወይም በሥራ ተቋራጮች የሚገቡት የኢንሹራንስ ሽፋን ነው፡፡

የዚህ ጹሁፋ ዋና ዓላማ በሃገራችን በቅርብ ጊዜ የሚሰሩ ህንጻወች ለሚያደርሱት ጉዳት የመድን ሽፋን እንዲገቡ ለማሳሰብ እና ያሉትን ህግጋት ለመዳሰስ ነው፡፡

1. ጽንሰ ሃሳቡ

ኢንሹራንስ ልክ እንደሌሎች የንግድ ግብይቶች ሁሉ በፖሊሲ መልኩ ሲቋቋም ተዋዋይ ወገኖችን የሚያስገድድ ውል ነው፡፡ በ1952ዓ.ምበወጣው የኢትዮጵያ የንግድ ህግም ኢንሹራንስን በተመለከት በአንቀጽ 654(1) ላይ የሚከተለውን ትርጉም ሰጥቶት እናገኛለን፡-

“የኢንሹራንስ ፖሊሲ ውል ማለት ኢንሹራስ ሰጪ የሚባለው ባአንድ ወይም በብዙ የተመደበውን የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ(ፕሪሚየም) ተቀብሎ በውሉ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ ኢንሹራንስ ለገባው ሰው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ውል ነው፡፡ ”

ከላይ በተሰጠው ትርጓሜ መሰረት ኢንሹራስ የሚከተሉት ባህሪያት አሉት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኢንሹራንስ የሚቋቋመው ቢያንስ ሁለት አካላት ማለትም ውል ሰጪው (የኢንሹራንስ ኩባንያ/insurer) እና ውል ተቀባዩ(insured) መካከል ነው፡፡ ሁለተኛ የኢንሹራንስ ውልየሚደረገው በጋራ ድርድር የሚዘጋጁ ውሎች(consultation contracts)ሳይሆን አስቀድሞ የተወሰነ ውል(Adhesive contract) ነው፡፡ በመሆኑም ውል ተቀባዩ አይቶ ከተመቸው የሚቀበለው ካልፈለገ ደግሞ የሚተወው ውል(accept or leave it) የሆነ ውል ሲሆን ውል ተቀባዩ የመደራደር አቅሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በትርጉም ወቅት መጣረስ ቢመጣ ውል ተቀባዩን በሚጠቅም መልኩ መተርጎም እንደአለበትየኢትዮጵያ ፍትሃብሄር ህግ አንቀጽ 1738 ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡

ሌላው መለያው የግራ ቀኙ ግዴታ ነው፡፡ ይህም የውሉ ዋና ጉዳይም አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የኢንሹራንስ ኩባንያው ለተጎጅው በውሉ መሰረት መካስ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞውል ተቀባዩ በየጊዜው በገባው ውለታ መሠረት አረቦን(Premium) የመክፈል ግዴታ እንዳለበት መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል Black’s Law dictionary (9እትም ገጽ 870) ላይ የሚከተለው ትርጉም አስፍሮ እናገኛለን፡-

“Insurance is a contract by which one party (the insurer) undertakes to indemnify another party (theinsured) against risk of loss, damage, or liability arisingfrom the occurrence of some specified contingency,and usuallyto defend the insured or to pay for a defenseregardless of whether the insured is ultimately foundliable. An insured party usuallypays a premium to theinsurer in exchange for the insurer's assumption of theinsured's risk.”

በዚህም መሰረት ኢንሹራንስ ማለት አንድ አካል በየጊዜው ለሌላኛው አካል በሚከፍለው አረቦን መሰረት ውል ሰጭው (insurer) ለሚደርሱ ጉዳቶች ካሳ የሚከፍልበት ውል እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የቢዝነስ ህግ መዝገበ ቃላት የሚከተለውን ትርጓሜ ሰጥቶት እናገኛለን፡-

“Insuranceis contract (i.e., insurance policy) under which the insurer (usually an insurance company) agrees for a fee (i.e., insurance premiums, normally paid at fixed intervals) to pay the insured party all or a portion of any loss suffered by accident, negligence or death. Insurance premiums vary according to the insurer’s estimate of the probability of the event insured against actually happening.”

ይህምበኢንሹራስ ፖሊሲው መሠረት አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ለውል ተቀባዩ አደጋ በደረሰ ጊዜ ሊከፈል የሚገባው ውል እንደሆነና ውል ተቀባዩም በአንጻሩ በየጊዜው አረቦን ለመክፈል የሚገባው ውል እንደሆነ መዝገበ ቃላቱ ያስረዳናል፡፡

በአጠቃላይ ከላይም ለመመልከት እንደተሞከረው የኢንሹራንስ ውል በተለያዩ ጉዳዮች ሊመሠረት ይችላል፡፡ ስለ ኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ጸሀፊው በሚቀጥለው ንኡስ ክፍል ይመለስበታል፡፡

2. የኢንሹራንስ መሰረታዊ መርሆች

ኢንሹራንስ ከተለያዩ አገራት ህግጋት ልማድ (comparative study) እንዲሁም የፍርድ ውሳኔዎች ተሞክሮ አንጻር የሚከተሉት የታወቁ መሰረታዊ መርሆች እና አስተሳሰቦች አሉት፡፡

ሀ) የጉዳት ካሳ መርሆ(Principle of Indemnity): -ይህ መርሆ የሚያስገነዝበው የኢንሹራንስ ውል ዋስትና በተሰጣቸው አደጋዎች ምክንያት የሚደርስን የገንዘብ ጉዳትን ለመተካት እና ለመካስ የሚደረግ ውል ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ንግድ ህግ በአንቀጽ 678 ላይ ኢንሹራንስ የገባ ዕቃ ማለት እቃው ካሳ ለመጠየቅ የተገባ ውል ነው በማለት ያስቀመጠው፡፡ ዳሩ ግን ካሳው ዕቃው አደጋ በደረሰበት ቀን ዋጋ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡

ለ) ኢንሹራንስ ሊገባበት የሚችል ጥቅም መኖር መርሆ/insurable interest/፡-ይህ ደግሞ ኢንሹራንስ ለመግባት አንድ ሰው መብት ወይም ጥቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ ይንን አስመልክቶም የንግድ ህጉ በአንቀጽ 675 ላይ የሚከተለውን ድንጋጌእናገኛለን፡-

በአጠቃላይ በዚህ መርሆ መሰረት ኢንሹራንስ ለመግባት የሚከተሉት ጉዳዮች እንደ ቅድመ ሁኔታነት ይነሳሉ፡፡ ለምሳሌ፡-የንብረት መብት፣ጥቅም ፣በሕይወት መኖር እና ዋስትና መሻት፤ንብረቱ ወይም ጥቅሙ የኢንሹራንሱ ዋና አካል መሆን አለበት፤ኢንሹራን በተገባለት ጉዳይ እና በውል ተቀባዩ መካከል ህጋዊ ግንኙነት መኖር እንደ የንብረት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት…ወዘተ አስፈላጊ መሆናቸውን ይህ መርሆ ይጠቁመናል፡፡

ሐ) በቅን ልቡና መግባት መርሆ/Utmost good faith/:-ንሹራንስ የሚገባ ማነኛውም ሰው ስለሚገባበት ጉዳይ ለኢንሹራንስ ኩባንያው በቅንነት እና በእውነት (latin: Uberrima fides)ላይ የተመሰረት ነገር መናገር ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ጉዳይ በንግድ ሕጋችንከአንቀጽ 667-669 ተመልክቷል፡፡

መ) የዳረጎት መርሆ/ The Principle of Subrogation/:-ይህ መርህ የሚያስገነዝበው ኢንሹራንስ ኩባንያው ለሶስተኛ ወገኖች ጉዳት አላፊነት በመውሰደ ማለትም በእነሱ ስም ከተዳረገ (subrogation) በኋላ ጉዳት አድራሹን አካል የመጠይቅ ህጋዊ መብት አለው፡፡ ይህም በንግድ ህጉ አንቀጽ 683 በግልጽ እንደተመለከተው የኢንሹራንስ ኩባንያው ለደረሰው ጉዳት ለውል ተቀባዩ ከከፈለ በኋላ ጉዳት አድራሹን ሦስተኛ ወገን ለመጠየቅ መብት አለው፡፡

3. የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ምንነት

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኢንሹራንስ አንዱ የአደጋዎች (risks) ማስተላለፊያ መንገድ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ዋና ዓላማ አደጋን በሚያጋጥምበት ጊዜአሰሪዎች፣ተቋራጮች፣ንዑስ-ተቋራጮች እንዲሁም በግንባታ ወቅት ድርሻ ያላቸው ሌሎች አካላት አደጋንወደ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚያስተላልፉበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ኢንሹራንስ የአደጋ መከላከያ መንገድ እንጂ ምትክ አይደለም፡፡ ለምን ቢባል ኢንሹራንስ በአብዛኛው ጊዜየሚሸፍነውየታወቁ እና ሊካሱ የሚችሉ አደጋወችን ነው፡፡

በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ሲባል በፕሮጀክት ግንባታ ወቅት ለሚደርሱ ጉዳቶች የሚደረጉ የመድን ውሎች ሲሆን ኢንሹራንስም የአደጋ ማስተላለፊያ መንገድ ተብሎ ሲመረጥ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሀንንም ሃሳብ ዶ/ር ናዔል፡ቡኒ ‘Risk and Insurance in Construction’ በሚለው ሁለተኛ እትም መጻሃፋቸው ገጽ 181 በአንክሮ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡

[C]onstruction insurance means all contracts of indemnity within the activities of the construction industry where insurance is chosen as the medium through which liabilities are shifted.”

 

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ የንግድ ህግ ስለ ኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ በግልጽ ባይደነግግም ከአንቀጽ 676 ምንባብ መረዳት እንደሚቻለው በኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱ አፈጻጸም ወቅት ለሚደርሱ ጉዳቶች ሽፋን ሊያገኙ እንደሚችሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በኢንሹራንስ ፖሊሲው በግልጽ ለእነዚህ አደጋዎች ተብሎ መገለጽ ይኖርበታል፡፡ ሌላው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በጣም ውስብስብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስን በተመለከተ ከመደበኛው የንግድ ሕግ ለየት ያሉ ሕግጋት ያስፈልጋል፡፡

አንድ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት በሚከተሉት ጉዳዮች ኢንሹራንስ ሽፋን ሊያገኝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡-ለንብረት ጉዳት፣ለሦስተኛ ወገን ጉዳት፣በጉዞ ላይ ላሉ ዕቃዎች/goods in transit/፣በሚገነባው ህንጻ ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች/damage to constructional plant/፣ታስቦ ለሚፈጸሙ አደጋዎች…ወዘተ መሰል ጉዳዮችን ያጠቃልላል፡፡

ለማጠቃለል ያህል የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ሲባል አደጋን ለመቀነስ በማሰብ ወይ በሥራ ተቋራጮች አሊያም በአሠሪወች ሥራው ከመጀመሩ በፊት የሚገባ የመድን ዓይነት ነው፡፡

4. የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ጠቀሜታ

እንደሚታወቀው ሚያዚያ 19 2008ዓ.ምበአዲስ አበባ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ስሙ ሰሚት በሚባል አካባቢባለ 5 ፎቅ ህንፃ ተደርምሶ በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ሰምተናልበተለይም አብዛኛው የከተማዋ ህንጻዎች ግንባታቸው ሳይጠናቀቁ ወደ ስራ መግባታቸው የችግሩ ምንጭ መሆኑ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡

የኢትየጵያ የሕንጻ አዋጅ ቁ.624/2001 በአንቀጽ 31 እንዲሁም አንቀጽ 32 ላይ በግንባታ ወቅት መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄወች ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሰረት ማነኛውም ግንባታ በግንባታው አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን፣የሚሰሩ ሠራተኞችን ወይም የሌሎችን ግንባታ እና ንብረቶችን ደህንነት በማያሰጋ መልኩ ዲዛይን መደረግ እና መገንባት ይኖርበታል፡፡ በተለይም ደግም የሕንጻ ደንብ ቁ.243/2003 አንቀጽ 29 ላይ የጥንቃቄ እርምጃዋችን በስፋት ይዘረዝራል፡፡ ህጉም እንዚህን የጥንቃቄ እርምጃወች አለመከተል ከፍትሃብሄር እና ከወንጀል ተጠያቂነት በተጨማሪ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚያስወስድ በደንቡ አንቀጽ 44 ላይ ይናገራል፡፡ የዚህ ጹሁፍ ዓላማ ስለጥንቃቄ እርምጃዎች ግንዛቤ መፍጠር ባይሆንም ስለ ኮንስትራክሽን ኢንሹራስ ጠቀሜታ ከተነሳ አይቀር መሰል ተያያዥ ጉዳዮችን ጠቆም ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡

በዋናነት የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ጠቀሚታው አንድም በግንባታ ወቅት የሚደርሱ አደጋወችን ለመቀነስ (proactive solution) በማሰብ ሥራ ተቋራጩ ወይም ባለቤቱ አስቀድመው ከመድን ድረጅቶች ጋር በሚገቡት ውል አማካኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-ስራ ተቋራጩ የኮንስትራክሽን መድን ውል ግዴታ ቢገባ በየ ጊዜው የሚከፍለው አረቦን በመኖሩ ምክንያት የሚገነባውን ህንጻ በጥንቃቄ ሊሰራ ይችላል፡፡ ሁለትም ጉዳት ከደረሰ በኋላ (reactive solution) ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት ለይቶ በመድን ውሉ መሰረት መካስን ይጨምራል፡፡

የኮንስትራክሽን አደጋን ምንግዜም ማስወገድ ባይቻልም መቀነስ እና ቅድመ-መከላከል ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህም ሊሆን ከሚችልባቸውመንገዶች ውስጥ አንዱ የኢንሹራንስ ሥርዓት ነው፡፡

በዚህ ጽሁፋ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው የሰሚቱን ዓይነት የህንጻ መደርመስ በሚደርስበት ጊዜ ተቋራጩ ኢንሽራንሽ የገባ ከሆነ መልካም ነው አለበለዚያ ግን የሚደርሰው ጉዳት የከፋ ያደረገዋል፡፡

5. የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ የሕግ ማዕቀፍ

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ በተበታተነ የህግ ማዕቀፍ ይመራል፡፡ ለምን ቢባል በአንድ በኩል ከ1952ዓ.ም ጀምሮ በወጣው የንግድ ሕግ አንቀጽ 654-712 ስለ ንብረት፣አደጋወይም የሕይወት መድን ባሉ ድንጋጌዎች ይመራል፡፡

በሌላ በኩል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪን እያደገ መምጣትን ተከትሎ በተለያየ ጊዜ በሙያ ማህበራት ወይም መንግስታዊ ተቋማት  የወጡ ወጥ ውሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በውል የደነገጉበት ጊዜ መኖሩን ማየት ይችላል፡፡

እንዲሁም በ2001ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ሕንጻ አዋጅ ቁ.624/2001 አንቀጽ 26 እና 27 የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ በአስገዳጅነት በይፋ መጀመሩን ያወጀ ህግ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ የወጣው የሕንጻ ደንብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁ.243/2003 አንቀጽ 19 እና 20 ላይ ዝርዝር ጉዳዮችን በመያዝ መውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡

ታዲያ እነዚህን ህግጋተ መሰረት አድርገው የግንባታ ውል ውስጥ የሚገቡ አካላት ዝርዝር ውሎችን ሊዋዋሉ ይችላሉ፡፡ በተለይም አገር-በቀል ኩባንያዎች እንዲሁም ዓለምአቀፍ ይዘት ያላቸውን ውሉች የሚገዛው የዓለምአቀፋ አማካሪ መሀንዲሶች ማህበር ወጥ ውል (FIDIC Red book 1999) የኮንስትራክሽን አደጋዎችን ለመቀነስ ከተቀመጡ መንገዶች አንዱ የሆነውን ማለትም ኢንሹራንስን በተመለከተ በአንቀጽ 18 በዝርዝር ያሰቀመጠበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡

በተለይ በመጀመሪያው አናቅጽ መግቢያ ላይ የመድን ሽፋን ገቢ(“insuring party”) ማን ሊሆን እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት የመድን ስፍን ገቢው ሥራ-ተቋራጩ፣ ባለቤቱ(አሰሪው) ወይም በጣምራ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በፌዴክ ወጥ ውልም የተባለው መድን በተለይ በአንቀጽ 17(3) ላይ የአሰሪው አደጋዎች ተብለው ከተለዩት ለምሳሌ የጦርነት፣ሽብር ጥቃት፣ብጥብጥ፣የባለቤቱ ሰራተኞች የተባለሽ ስራ ወዘተ ዉጭ ሁሉንም ዓይነት ጥፋቶች እና አደጋዎች ሊሸፍን ይችላል፡፡

በተለይ ፌዴክ በአንቀጽ 18(2)(ረ)ላይ የመደን ሽፋን ላያገኙ የሚችሉ ሁኔታዎችን በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ለምሳሌ፡-የተበላሹ የዲዛይን ሥራዎች ወይም የፕሮጀክት ግብዓቶች ላይ ሺፋን አያገኙም፡፡

እርግጥ ነው የFIDIC ወጥ ውል ልክ እንደ ሌሎች ውሎች ወደውና ፈቅደው በታዋዋሉ ወገኖች ላይ አስገዳጅነቱ የታወቀ ነው፡፡

በ1994 ዓ.ም የወጣው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል የኮንስተራክሽን ኢንሹራንስን በተመለከተ ለሥራ ተቋራጮች ብቻ በሚመስል መልኩ የተቀረጸ ይመስላል፡፡

በተለይ በአንቀጽ 21 ላይ እንደተመለከተው ሥራ ተቋራጩ በራሱ እና በአሰሪው ስም ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሲባል እንዲሁም ለሚደርሱ ጉዳቶች የመድን ሽፋን የመግባት ግዴታ አለበት፡፡ ሆኖም ግን በወጥ ውሉአንቀጽ 20 ላይ በተዘረዘሩ ልዩ አደጋዎች ማለትም እንደ ጦርነት፣ብጥብጥ ወዘተ የመድን ሽፍን መግባት አይችል፡፡

 

በጸሀፊው እምነት የሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል ከFIDIC ወጥ ውል አንጻር ሲነጻጸር በተለይ ስል ኢንሹራንስ ያስቀመጣቸው ድንጋጌወች በይዘትም ሆነ በተፈጻሚነት በጣም ጠበብ ያሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በንወስድ፡በሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ወል ኢንሹራንስ የመግባት ግዴታ የሥራ ተቋራጮች ብቻ ነው፡፡ በFIDIC ግን ሥራ ተቋራጮችም ሆነ አሰሪዎች መድን ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ሌላው በሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል ልዩ አደጋዎች( excepted risks) ከመድን ሽፋን ውጪ ሲሆኑ በአንጻሩ ደግሞ በFIDIC ወጥ ውል ግን በአሰሪው አማካኝነት ሽፋን ሊገኙ ይችላሉ፡፡

6. በኢትዮጵያ በአስገዳጅነት የወጣው የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ሕግ

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስን በተመለከተ በአስገዳጅነት የተደነገገው ህግ በ2001 ዓ.ም የወጣው የሕንጻ አዋጅ ነው፡፡ ዳሩ ግን አዋጁ የተጠቀመው ቃል “መድን”(insurance) ከማለት ይልቅ “ዋስትና” (guarantee) በሚል መልኩ አስቀምጦታል፡፡ የሆነው ሆኖ አዋጁ ዋስትና ቢልም ቅሉ በተግባር ግን የመድን ግዴታን ያስቀመጠበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡

በተለይ የአዋጁ አንቀጽ 26(3) የተመዘገቡ ባለሙያዎች (registered professionals) እንደ የዲዛይን ሥራ የሚሰሩ (designers) ወይም አማካሪዎች (consultants) ከሚሰሩት ሥራ አንጻር በዋናነት ከዲዛይን ጋር ለተያያዙ ጉዳቶች ዋስትና ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ግዴታ በ2003 ዓ.ም በወጣው ደንብ ቁ.243/2003 አንቀጽ 19(6) ላይ ምድብ “ለ” እና “ሐ” ሕንጻዎችን የህንጻ ዲዛይን ለማከናወን ውለታ የሚወስድ የተመዘገበ ባለሙያ የመድን ሽፍን ዋስትና ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ግን የምድብ “ሀ” ህንጻዎች አስገዳጁ ኢንሹራንስ አይመለከታቸውም፡፡ ይህን መሰሉ ግዴታም ለሥራ ተቋራጮች በአዋጁ አንቀጽ 27(2) እንዲሁም በደንቡ አንቀጽ 20(6) ላይ ምድብ “ለ” እና “ሐ” ሕንጻዎችን የሚከናዉኑ ሥራ ተቋራጮች የመድን ዋስትና የማቅረብ ግዴታ አለባቸው፡፡ ወደ ዝርዘር ጉዳዮች ከማምራታችን በፊት በኢትዮጵያ ሕንጻ አዋጅ የህንጻዎችን ምደባ ማየት ተገቢ ነዉ፡፡

በዚህም መሰረት የምድብ “ሀ”ህንጻወች የሚባሉት በሁለት የኮንክሪት ወይም የብረት ወይም ስትራክቸራል ውቅሮች መካከል ያለው ርቀት ሰባት(7) ሜትር ወይም ከዚያ በታች የሆነ ወይም ከሁለት ፎቅ የማይበልጡ የግል መኖሪያ ቤቶች እና ባለአንድ ፎቅ ህንጻዎችን ይይዛል፡፡ በሌላ በኩል የምድብ “ለ” ህንጻወች ሚባሉት ደግሞ በሁለት የኮንክሪት ወይም የብረት ወይም ስትራክቸራል ውቅሮች መካከል ያለው ርቀት ሰባት(7) ሜትር ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ወይም ባለ ሁለት ፎቅ የሆነ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ወይም በምድብ “ሐ”የማይፈን ህንጻ ወይም በምድብ“ሀ”የተመደበ እንደ ሪል እስቴት ያለ የቤቶች ልማት ነው፡፡ በመጨረሻም በምድብ “ሐ”የሚመደቡት ደግሞ የሕዝብ መገልገያ፣ተቋም ነክ ህንጻ፣የፋብሪካ ወይም የወርክሾፕ ህንጻ ወይም ከመሬት እስከ መጨረሻው ወለል ያለው ከፋታ ከአስራ ሁለት(12) ሜትር ከፍታ በላይ ያለ ማነኛውም ህንጻ ነው፡፡ /የህንጻ አዋጅ ቁ.624/2001 አንቀጽ 2(6-8) ይመለከተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ማነኛውም የተመዘገበ ባለሙያ የሚሰራው ምድብ “ለ”ህንጻዲዛይን ጠቅላላ ወጪ እስከ 5,000,000/አምስት ሚሊየን ብር ከሆነ የፕሮጀክቱን 10/አስር በመቶ ማለትም 500,000/አምስት መቶ ሺ ብር ከታወቀ መድን ድርጀት ዋስትና ማቅረብ አለበት፡፡ ሌላው ባለሙያው ለምድብ “ሐ”ህንጻየዲዛይን ሥራዎች የፕሮጀክት ወጪያቸው እስከ 250,000/ሁለት መቶ ሃመሳ ሺ ብር ከሆነ የፕሮክቱን 20/ሃያ በመቶ ማለትም 500,000/አምስት መቶ ሺ ብር መድን መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌላው የፕሮጀክት ወጪው እስከ 20,000,000/ሃያ ሚሊየን ብር የሆነ እነደሆነ መድን መጠኑ 10/አስር በመቶ ይሆናል፡፡ በአንጻሩ የፕሮጀክት ወጪው ሲጨምር የመድን ማስያዣ መጠኑ ይቀንሳል፡፡ /ደንብ ቁ.243/2003 አንቀጽ 19(6) ይመለከቷል፡፡ /

ለሥራ ተቋራጮች በአንጻሩ በመጠንም ቢሆን መድኑ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌከሪል እስቴት ውጪ ያሉ የምድብ “ለ” ህንጻወች የፕሮጀክት ግምት ዋጋቸው 10,000,000/አሰር ሚሊየን ብር የሆኑ ግንባታዎች እስከ 20በመቶ ዋስትና ማለትም 2,000,000/ሁለት ሚሊየን ብር የዋስትና ሰነድ ከታወቀ መድን ድርጅት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ለምድብ “ሐ” ሕንጻወች የግንባታ ወጪያቸው 10,000,000/አስር ሚሊየን ለሆኑት 30በመቶ ዋስትና ማለትም 3,000,000/ሦስት ሚሊየን ብር የዋስትና ሰነድ ከታወቀ መድን ድርጅት ማቅረብ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል የፕሮጀክት ወጪያቸው 15,000,000 ገደማ ከሆነ ደግሞ 25በመቶ ዋስትና ማለትም3,750,000/ሦስት ሚሊየን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺ ብር የዋስትና ሰነድ ከታወቀ መድን ድርጅት ማቅረብ አለባቸው፡፡ በመጨረሻም የግንባታ ወጪያቸው ከ25,000,000/ሃያ አምስት ሚሊየን ብር ከሆነ 20በመቶ ዋስትና በማቅረብ ማለትም5,000,000/አምስት ሚሊየን ብር ማቅረብ አለበት፡፡ /ደንብ ቁ.243/2003 አንቀጽ 20(6) ይመለከቷል፡፡ /

በደንቡ መሰረት የሚቀርበው ዋስትና የመልካም አፈጻጸም መያዣ/performance bond/ እና መላ የኮንትራክተሩ አደጋወች/Contractor’s All risks/ ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ይናገራል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን በቀን 2 ግንቦት 2008ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ መሰል መመሪያ መሰረት የሕንጻ ግንባታ ለማከናወን ውለታ የሚወስድ ማነኛውም የተመዘገበ ሥራ ተቋራጭ በውለታ ሰነዱ መሰረት ግንባታውን በሚያከናውንበት ወቅት በግንባታዉ የሥራ ጥራትና በጥንቃቄ ጉድለት ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳዮች የግንባታው ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ቢያንስ ለአንድ አመት የሚቆይ የጉዳት ማካካሻ ዋስትና በደንቡ መሠረት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በመመሪያው መሰረትም ሥራ ተቋራጩ ከታወቀ የመድን ድርጅት ፖሊሲ ገብቶ ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት ማቅረብ አለበት፡፡ አዲሱ መመሪያ በይዘት ከነባሩ የሕንጻ ድንብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ዝርዝሩም በሚከተለው ሰንጠረዝ ይመልከቱ፡፡

ታዲያ! ነባሩ አዋጅ እና ደንብ ለምን ተረሳ? ለምንስ አዲስ ደብዳቤ መሰል መመሪያ ማውጣት አስፈለገ? ሰሚት ላይ ሚያዚያ 19 የተደረመሰውን ህንጻ በማስመለከት እሳት የማጥፋት ሥራ ወይስ ሌላ ምክንያት? መልሱን ለአንባቢው እተዋለሁ፡፡

ሌላው መመሪያው ምንም እንኳን የፕሮጀክት ወጪ ቀመርን ለማስላት የሚረዱ የሕንጻ ደንቡን ድንጋጌዎች ቢጠቀምም የዋስትና አቀራረብ ቀመር(formula) ግን በግልጽ አልደነገገም፡፡ የመመሪያው ተፈጻሚነትም በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡

የመፍትሄ ሃሳብ

ኢንሹራንስ ማለት ውል ሰጪ(የመድን ኩባንያ) እና ውል ተቀባይ መካከል የሚደረግ አስቀድሞ የተዘጋጀ ውል ነው፡፡ ኢንሹራስ ለመግባት አንድም መድን የሚገባበት ጥቅም መኖር ወይም በቅን ልቡና ሊሆን እንደሚገባ አጠቃላይ የኢንሹራስ መርሆ ያስገነዝባል፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ሲባል አደጋን ለመቀነስ በማሰብ ወይ በሥራ ተቋራጮች አሊያም በአሠሪዎች ሥራው ከመጀመሩ በፊት የሚገባ የመድን ውል ነው፡፡ የኮንስትራክሽን መድን ጠቀሜታው በህንጻው ግንባታ ሂደት ለሚደርሱ አደጋወችንለመቀነስ በማሰብ እና በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች እንደመካሻነት የሚያገለግል ውል ነው፡፡

በመጨረሻም በጸሀፊው እምነት የዚህ ዓይነቱ መመሪያ መሰል ህግ መውጣት በሃገራችን የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ እንዲያድግ አስታዋጽዖ ቢኖረውም ከ8/ስምንት አመት በፊት የወጣ አስገዳጅ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስን ሚመለከት ሕግ እያለ ሌላ ተመሳሳይ መመሪያ ማውጣት ተገቢ አይመስልም፡፡ ሌላው የዋስትናው መጠን፣ቀመር እንዲሁም የመያዣ ጊዜን በተመለከተ ግን በደምብ ዝርዝር ጥናት ተጠንቶ ቢቀርብ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል ብየ አምናለሁ፡፡ ሌላው ይህ መመሪያ ተፈጻሚነቱ አዲስ አበባ ለሚሰሩ ህንጻወች ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደዚህ አይነቱ መመሪያ በክልሎችም ቢተገበር መልካም ነው፡፡

ሌላው በሕንጻ ድንቡም ይሁን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር መመሪያ መሰረት አስገዳጁ የኮንስትራክሽን ኢንሹራንስ ግዴታ የሚጥለው በሥራ ተቋራጮች ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ግን FIDIC ወጥ ውል እንዲሁም ከአደጉ አገራት ልማድ አንጻር የህንጻ ባለቤቶች (አሰሪዎች) እንዲገቡ ቢደረግ ዘርፉን ፍትሃዊ ያደርገዋል፡፡

Related Posts

Leave Comments