ግልግል በፍትሐብሔር ሕጋችን እውቅና ከተሰጣቸው የሙግት መፍቻ ዘዴዎች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ተከራካሪዎችም ጉዳያቸውን ወደ ግልግል የሚወስዱት በመካከላቸው በሕግ ፊት የሚጸና የግልግል ስምምነት እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ በግልግል ሂደት መብታቸው የሚነካ ሦስተኛ ወገኖች ምን ዓይነት መፍትሔ ሊያገኙ ይችላሉ የሚለውን ለመመልከት ይሞክራሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ የቀረበው በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም ለገበያ ከበቃው ‹‹የግልግል ዳኝነት በኢትዮጵያ›› ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ የተቀነጨበ ነው፡፡
ዝርዝር ሐሳቦችን ለማግኘት እንዲሁም ስለ ፍሬ ሐሳቡ በጥልቀት ለመረዳት መጽሐፉን ማንበብ ጠቃሚ ነው እላለሁ፡፡ ይህ ጽሑፍ የወጣው የሕግ ባለሙያዎች በየጊዜው ከሚገጥመን ወይም ሊገጥመን ከሚችለው የሕግ ክርክር በመነሳት ሲሆን ዋናው ዓላማውም ውይይትን መፍጠር ነው፡፡
በግልግሉ ሂደት መብታችን ወይም ጥቅማችን ተነካ ብለው የሚያስቡ አካላት ወደ ግልግሉ ጣልቃ ለመግባት ፍላጎት ማሳየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ግልግል በሁለት ወገኖች ብቻ የሚደረግ ሂደት በመሆኑ ጣልቃ ለመግባት የሚፈልግ ሰው አቤቱታው በገላጋዮቹ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የግድ ይላል፡፡
በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ባለ አንድ ጉዳይ በከሳሽነት እና በተከሳሽነት በተሰየሙት ወገኖች መካከል ብቻ ክርክር ቢጀመር እነዚህ ወገኖች በሚከራከሩበት ጉዳይ መብት ወይም ጥቅም አለኝ የሚል ወገን ካለ ክርክር መጀመሩን እንደተረዳ ጣልቃ የመግባት መብት አለው፡፡ መብቱን የሚሰጠውም ሕግ ነው፡፡
ክርክር መጀመሩን ሳይረዳ እና ሳያውቅ ጉዳዩ ክርክሩ ተጠናቆ መወሰኑ እንኳን ቢታወቅ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ መብቴ ተነክቷል የሚለውና የክርክር ተካፋይ ያልነበረው ሰው ይህንኑ ውሳኔ በመንቀፍ ለመቃወም የሚችልበት ሥርዓትም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 እና ተከታዮቹ ተበጅቷል፡፡
በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ ማብራሪያ የጻፉት ሮበርት አለን ሴድለር እንዳሉት ከሆነ አንድ ሰው በክርክር ጣልቃ ይገባ ዘንድ መለኪያ ተደርጎ የሚወሰደው ጣልቃ ገቡ በክርክሩ ጥቅሙ በቀጥታ ሊነካ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
በሌላ አገላለጽ ‹‹የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብ ለመሆን ሌሎች ሰዎች በሚከራከሩበት ጉዳይ የሚሰጠው ውሳኔ በቀጥታ መብቱን እና ጥቅሙን የሚነካ መሆኑን የማስረዳት ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡… ጣልቃ ገብ ጥያቄው ተቀባይነት እንዲኖረው ውሳኔው የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነውን ሰው መብት እና ጥቅም በሚጎዳ መልኩ በቀጥታ የሚፈጸም መሆኑን እና ሌላ አዲስ ክስ በማቅረብ ለማስቀረት የማይቻል መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡››
አንድ ሰው ጣልቃ ለመግባት በሚያቀርበው ጥያቄ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን እናገኛለን፡፡ የመጀመርያው ጣልቃ ገቡ መብቱ እና ጥቅሙ የሚጎዳ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አዲስ ክስ እንዳይጀመር ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ካለ የጣልቃ ገቡ ጥያቄ በሕግ ፊት ተቀባይነት የለውም፡፡
ስለ ጣልቃ ገብ ጽንሰ ሐሳብ ይህን ያህል ካልን ጣልቃ ገብነት በግልግል ውስጥ እንዴት ይታያል የሚለውን ለመመርመር እንሞክር፡፡ ወደ ግልግሉ ጣልቃ መግባት የሚፈልግ ሦስተኛ ወገን ይህንን በሁለት መንገድ ሊፈጸመው ይችላል፡፡ የመጀመርያው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41 መሠረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 43ን በመጠቀም ነው፡፡
በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41 እና 43 መሠረት ወደ ግልግሉ ሂደት ጣልቃ መግባት ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ‹‹የግልግል ዳኝነት በኢትዮጵያ›› የሚለውን መጽሐፍ ይመልከቱ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሠረት የጣልቃ ገብነት ጥያቄ ቢቀርብ የግልግሉ ሂደት እንዴት ያስተናግደዋል የሚለውን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡
በሦስተኛ ወገኖች ጣልቃ ገብነት ላይ መመልከት የሚኖርብን ነጥብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 እና ተከታዮቹ መሠረት በግልግል ተቃውሞ ማቅረብ መቻል አለመቻሉን ነው፡፡ ክርክር መጀመሩን ሳይረዳ እና ሳያውቅ ጉዳዩ በከሳሽነት እና በተከሳሽነት በተሰየሙት ወገኖች መካከል የተደረገው ክርክር ተጠናቆ ከተወሰነ በኋላም ቢሆን ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ መብቴ ተነክቷል የሚለው ሰው ይህንኑ ውሳኔ በመንቀፍ ፍርዱ ከመፈጸሙ በፊት መቃወም እንደሚችል የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 ይደነግጋል፡፡
ወደ ክርክር መግባት ያለበት አካል በክርክሩ ተሳታፊ ሳይሆን የተወሰነው ውሳኔ መብቱን የሚነካ ሆኖ ሲገኝ ውሳኔው ከመፈጸሙ በፊት ውሳኔው እንዲነሳና ክርክሩ እርሱ ባለበት እንዲቀጥል ማመልከት እንደሚችል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 32638 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡
በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሠረት የተቃውሞ ማመልከቻ ማቅረብ የሚችሉት ሦስት ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ሮበርት አለን ሴድለር ይገልጻሉ፡፡ እነዚህም
- በአንድ ክስ ውስጥ ተደምሮ መከሰስ የሚገባው ወይም ተከራካሪ ወገን ሆኖ መጨመር ወይም መደመር የሚገባው ሰው /indispensible party/
- ትክክለኛ ጥቅማቸው የተጎዳ ወይም መብታቸው የተነካ ሰዎች /persons who are real parties in interest/
- በክርክሩ ተሸናፊ ለሆነው ወገን ድርሻ ወይም ካሳ መክፈል ያለበት ወገን /persons who will beliable for contribution or indemnity to the unsuccessful party/ እንደሆኑ በመጽሐፋቸው አስቀምጠዋል፡፡
አክለውም ‹‹የተቃውሞ ማመልከቻ በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት ሊጣመሩ ይችሉ በነበሩ ነገር ግን ለክርክሩ እጅግ አስፈላጊ ባልሆኑ ሰዎች የሚቀርብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ክስ መመሥረት ወይም የራሳቸው ሓላፊነት ያለባቸው ሊሆኑ ስለሚችሉ በውሳኔው ጥቅማቸው የሚጎዳ አሊያም መብታቸው የሚነካ አይሆንም፡፡››
የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ መብቱ የተነካው ሰው ከውሳኔ በኋላ ከአፈጻጸም በፊት የመቃወም ማመልከቻ በማቅረብ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ቢደነግግም ይህ በግልግል እንዴት ሊፈጸም ይችላል በሚለው ላይ ምንም ስለማይል እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ስላልሰጠበት ጉዳዩ ለሕግ ክርክር ክፍት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በሌላ አገላለጽ ገላጋዮች ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ውሳኔው መብቱን እንደሚነካ ማስረጃ ያለው ሰው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 እና ተከታዮቹን በመጥቀስ የመቃወም ማመልከቻ እንዳያቀርብ የሚከለክለው የሕግ ምክንያት አለ?
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ካሳለፋቸው ውሳኔዎች የተነሳ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 ላይ ያለው አረዳድ የዳበረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህ አይተነተንም ነገር ግን ከግልግል ባሕሪይ አንጻር የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 ይፈተሻል፡፡
- ግልግል በውል ላይ የተመሠረተ ነው፤ ውሉ ደግሞ አለመግባባትን ሲፈጠር ጉዳዩን ለሦስተኛ ወገን በማቅረብ መፍትሔ የሚገኝበት መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁ 3325(1) ይደነግጋል፡፡ ውል ደግሞ ውጤት የሚኖረውና እንደ ሕግ የሚቆጠረው በተዋዋሉት ሰዎች መካከል እንደሆነ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1731(1) እና 1952(1) ይገልጻሉ፡፡
- ይህ ማለት በውሉ ለመገዛት ፈቃዳቸውን ያልሰጡ ሰዎች በዚህ አይገደዱም ማለት ነው፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 ልዩ ባሕሪይ ግን መብቱ የተነካበት ሰው ራሱ ጉዳዩ እንዲታይለት ማመልከቻውን ይዞ በፈቃደኝነት መምጣቱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰው በግልግል እንዴት ሊስተናገድ ይችላል የሚለውን ከሕጉ አግባብ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡
- በመሠረቱ አለመግባባቱ በግልግል እንዲወሰን ሕግ የሚፈቅድ ሲሆን ወይም ተከራካሪዎቹ ወገኖች የሚያከራክራቸው ነገር በግልግል እንዲወሰን ወይም ወደፊት ክርክር የተነሳ እንደሆነ በግልግል እንዲታይ የተስማሙ እንደሆነ ጉዳዩ በግልግል መታየት እንዳለበት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 315(1) ይደነግጋል፡፡ በሌላ ቋንቋ የግልግል ጉባዔ የሚቋቋመው የተፈጠረው አለመግባባት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ሲሆን ፍርድ ከተላለፈ በኋላ ግን አገልግሎቱ ያበቃል፡፡ ጉባዔው ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ትክክለኛውን ጭብጥ በመመሥረት፣ ክርክር በመስማት፣ የሰነድም ሆነ የሰው ማስረጃዎችን በአግባቡ በመመርመር ይሆናል፡፡ ጉባዔው የቀረቡለትን ተከራካሪዎች በአግባቡ መስማቱ ከተረጋገጠ ውሳኔው በድምጽ ብልጫ የሚሰጥ እንኳን ቢሆን የጸና እንደሚሆን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 318(3) በግልጽ አስፍሯል፡፡ ውሳኔው ሲዘጋጅም በፍርድ ቤት እንደሚዘጋጅ የውሳኔ ዓይነት ሆኖ የካሳንና የኪሳራን ጉዳይ ለመወሰን እንሚችል የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 318(2) መብት ይሰጣል፡፡ ውሳኔውም ቀንና ዓመተ ምሕረት ተሞልቶበት በገላጋዮቹ ከተፈረመበት በኋላ ለተከራካሪዎቹ እንዲደርሳቸው እንዲደረግ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 318(4) ያዛል፡፡
- እነዚህ ሁሉ ከተፈጸሙ በኋላ የግልግል ጉባዔው ሥራውን ያጠናቅቃል፤ ከዚህ በኋላ ተከራካሪዎቹ ጉዳያቸውን በይግባኝ ወይም በአፈጻጸም ወደ ፍርድ ቤት ይዘው ይሄዳሉ፡፡ የግልግል ጉባዔው በውሳኔው ላይ እርማት ወይም ትርጉም ለመስጠት በድጋሚ ሊሰበሰብ እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህም ማለት የገላጋይ ዳኞቹ ወደ ፍሬ ጉዳዩ ተመልሶ በመግባት አዲስ ውሳኔ ለመወሰን የሚያስችላቸውን የዳኝነት ሥልጣናቸውን (jurisdiction) ያጣሉ፡፡
- ተቋማዊም ሆነ አስተዳደር አልባ፣ የንግድም ሆነ የኢንቨስትመንት ግልግል ጉባዔው የሚቋቋመው በውል ወይም በሕግ ነው፡፡ ገላጋዮቹ ከሕግም ሆነ ከተዋዋዮቹ የሚጣልባቸው ሓላፊነት የቀረበላቸውን ክርክር ገለልተኛና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በብቃት ውሳኔ መስጠት ነው፡፡
- ገላጋዮቹ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሰጡ ማለት ደግሞ ጉባዔው የተቋቋመበትን ዓላማ ስላሳኩ ውሉ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1806 መሠረት ውለታው በተደረገው ስምምነት መሠረት ተፈጽሞ እንደሆነ ግዴታው ቀሪ እንደሚሆን ግልጽ ድንጋጌ አለ፡፡ ስለዚህ ገላጋዮቹ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ፍርድ ሰጥተው ሲያበቁ ግዴታው ቀሪ ይሆናል (the obligation will be terminated)፡፡
- የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 ግን ጉዳዩን በአዲስ መልኩ እንዲመረመር የሚያደርግ ነው፡፡ ከመቃወም ማመልከቻው በመነሳት የከሳሹም ሆነ የተከሳሹ ክስና መልስ መጀመርያ ቀርቦ ከነበረው መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡ ዳኞቹ ከቀረበላቸው ማስረጃዎች እና ክርክሮቹ በመነሳት አዲስ ጭብጥ መመሥረት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ተግባር ገላጋዮቹ የሰጡትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ የሚቀይርበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡
ከላይ የተመለከትነው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሠረት በግልግል ጣልቃ መግባት የማይቻልበትን ሁኔታ ሲሆን ለሕግ ክርክር ይሆን ዘንድ የሚቻልበትን ሁኔታም መፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሠረቱ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 ዓላማ በተመሳሳይ ፍሬ ነገር ላይ ሊመሠረቱ የሚችሉ ጉዳዮች የተለያየ መዝገብ ተከፍቶላቸው እንዳይታዩ እና በፍርድ ቤት ላይ የፋይሎች መደራረብና መብዛት (procedural economy) እንዲሁም ጥቅሙ የተካው ሰው በሚፈጸመው ውሳኔ መብቱን እንዳያጣ ወይም አላግባብ እንዳይቀማ ለማድረግ እንደሆነ ሮበርት አለን ሴድለር በመጽሐፋቸው በሚከተለው መልኩ ይገልጹታል
“The purpose of the rule permitting the filing of opposition is to enable a person who is affected by the judgment… to prevent the interference with his interests that will result if the judgment is executed.”
ከዚህ መነሳት ስንመለከተው በግልግል በተሰጠው ውሳኔ መብቱ የተነካው ሰው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሠረት ጉዳዩን ለግልግል ችሎቱ ለማቅረብ የሚችልበት አጋጣሚ አለ፡፡ የግልግል ችሎቱ የሰጠው ውሳኔ በቅን ልቦና ያለን የሦስተኛ ወገን መብት የሚያሳጣ ስለሆነ ጉዳዩን ተመልሶ ማየት የማይችልበት ምንም ምክንያት መኖር የለበትም፡፡