ስለዓለም አቀፍ ሕግ በአጭሩ
ዓለም አቀፍ ሕግ በሉዓላዊ አገሮች መካከል ያለን ግንኙነት ወይም በአገሮችና እንደተባበሩት መንግሥታት ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ያለን ግንኙነት የሚገዛ የሁሉ አቀፍ ደንቦች እና መርሆዎች ሥርዓት ነው። በሌላ አነጋገር «International law is the universal system of rules and principles concerning the relations between sovereign States, and relations between States and international organizations such as the United Nations» የሚል ትርጉም ተሰጥቶት እናገኘዋለን። ቀደም ባሉት ጊዜያት በዓለም አቀፍ ሕግ እና በየሐገሩ በሚገኙ ዜጎች፣ ሉአላዊ ባለሆኑ አካላት (Transnational Corporations) እና መንግሥታዊ ባለሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች (International Non-Governmental Organization) ቀጥተኛ ግንኙነት ያለነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ይህ የታሰበው ቀጥተኛ ግንኙነት በስፋት እየታየ መሆኑን ዓለም አቀፍ ምሁራንን እያስማማ ነው።
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፋዊ የሆነ ማዕከላዊ ሕግ አውጭ ባለመኖሩ፣ አለፎ አልፎ ከሚታዩት በስተቀር ዓለም አቀፍ ሕግን ውጤታማና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲከበር የሚያደርጉ የእርምጃ ዘዴዎች ባለመጎልበታቸው፣ እራሱን የቻለ የተጠናከረ ማዕከላዊ አስፈጻሚ አካል ጎልቶ አለመታየቱ (የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሳይዘነጋ መሆኑ ይታወቃል) ፣ ክርክሮችን ተቀብሎ እልባት የሚሰጠው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ስራውን የሚያከናውነው እና ችሎት የሚቀመጠው አለመግባባት የታየባቸው አገሮች በራሳቸው ፍቃደኝነት ጉዳያቸውን ሲያቀርቡለት እንጂ አስገድዶ የማስቀረብ ሥልጣኑም ሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት የሌሉት መሆኑ እና ዓለም አቀፍ ሕግ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ አገሮች ጥቅምና አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ እና አፈፃፀሙም በእነሱ ተጽዕኖ ሥር በመውደቁ ፍትሃዊነቱ አጠያያቂ ነው፣ የደሃ ሐገሮችን ጥቅም አያስጠብቅም የሚሉ ትችቶችን ወ.ዘ.ተ. ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዓለም አቀፍ ሕግ የሚባል ነገር እንደ ሕግ የመቆም ብቃት የለውም የሚሉ ወገኖች እየበረከቱ መጥተዋል። በተለይ የሕግ መሠረታዊ ባህሪ ነው ተብሎ የሚታሰበውን የአስገዳጅነት ተፈጥሮ አልተላበሰም በሚል የሕግ ዋጋ የለውም እያሉ ክፉኛ ያብጠለጥሉታል። ሌሎች ደግሞ እንደ ሕግ ባለመከበሩና በመጣሱ ምክንያት ብቻ ሕግ ከመሆን የሚያግደው ነገር የለም ባይ ናቸው። እንደዚያም ከሆነ ብሄራዊ ሕጎችስ በተደጋጋሚ ሲጣሱ ይታዩ የለምን? ሲሉ በአጽእኖት ይጠይቃሉ፣ እናም የዓለማችን ግንኙነት እየሰፋ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ሕግን አሳንሶ መመልከትም ይሁን ጭራሽ እልውናውን መፈታተን እውነታን ያላገናዘበ ድምዳሜ ነው ሲሉም ትችት ያቀርባሉ።
ዓለም አቀፍ ሕጎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ልንመድባቸው እንችላለን። እነሱም ዓለም አቀፋዊ የመንግሥት ሕግ (Public International Law) እና ዓለም አቀፋዊ የግል ሕግ (Private International Law) በማለት ሲሆን ዓለም አቀፋዊ የመንግሥት ሕግ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ራሳቸውን በቻሉ ነፃ እና ሉአላዊ አገሮች መካከል የሚፈጠረውን የሁለትዩሽ ወይም ከዚያ በላይ ግንኙነቶች የሚገዛና የሚቆጣጠር ሕግ ነው። በሌላ በኩል ዓለም አቀፋዊ የግል ሕግ በፍትሐብሄር ጉዳዩች ዙሪያ የሚፈጠሩ ግንኙነቶች እና አለመግባባቶች በሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አገሮች ዜጎችን በተፎካካሪነት ያሳተፈ ሲሆን አልያም የሌሎች አገር ተወላጆች ንብረት በአንዲት አገር የሚገኝ ከሆነ እንዲሁም የውጭ አገር ዜጎች አንዳንድ የፍትሐብሄር ድርጌቶችን ለምሳሌ ውርስ፣ ውል፣ ከውል ውጭ የሚያስጠየቁ ኩነቶችን የፈፀሙ እንደሆነ አለመግባባቱ መፍትሄ የሚያገኘው በዓለም አቀፍ የግል ሕግ አማካኝነት ነው።
ዓለም አቀፍ ሕጎች የተለያዩ መሠረቶች ወይም ምንጮች እንዳሉዋቸው ዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤትን (International Court of Justices) ባቋቋመው ሰነድ አንቀጽ 38(1) ላይ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል። ዓለም አቀፍ ሕግ ውስጥ የሚካተቱት የሕግ ምንጮች፦
a. በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ራሳቸውን በቻሉ ነፃ እና ሉአላዊ አገሮች መካከል የሚፈጠረውን የሁለትዩሽ ወይም ከዚያ በላይ ግንኙነቶች (Bilateral or Multilateral) የሚያፀድቁበት ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው (Treaties)፣
b. ዓለም አቀፋዊ የባሕል ደንቦች (International Customary Law) በበርካታ አገሮች ለረጅም ጊዜ ተደጋግመው ሲሰራባቸው የነበሩ በዓለም እዝቦችና መንግሥታቶች ዘንድ እንደ ሕግ በመታየት ላይ ያሉ ደንቦች ናቸው። ዓለም አቀፋዊ ልማዶች እንድ ዓለም አቀፍ ሕግ ሊያገለግሉ የሚችሉት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ሲያሟሉ ነው። የመጀመሪያው በየሐገሮቹ ለረጅም ዘመናት ተደጋግሞየተከሰተ ልማድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ መንግሥታትና ሕዝቦች ይህን ለማድ እንደ ሕግ እውቅና ሊሰጡት፣ ሊያከብሩትና ሊገዙት ይገባል።
c. ከበለፀጉት ሐገሮች የተገኙ አጠቃላይ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆች (General Principles of International Law Derived from Civilized Nations) ናቸው።
d. የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ውሣኔዎች እና የዓለም አቀፍ ምሁራን ጽሁፎች (Judicial Decisions and Writings of Publicists) ምሁራኖች በነፃነት የሚያበረከቷቸው የተለያዩ የሕግ ጽንሰ ሐሣቦችና መርሆዎች በተለያዩ ሐገሮች የሚገኙ ሕግ አውጪዎችን በማሣመንና በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ በማሣረፍ እንደ ሕግ ምንጭነት እንዲጠቀሙባቸው ያስችሏቸዋል። እ.ኤ.አ. ከ1945 ጀምሮ ከሰባዊ መብቶች እድገት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ገለልተኛና ነፃ በሆኑ ተቋማት እልባት የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ከነዚህ ተቋማት ውስጥም የኑረንበርግ የናዚ ጀርመን ጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት፣ እ.ኤ.አ. ሃምሌ 17/1998 በ120 ሐገሮች ስምምነት ፀድቆ እሮም(Rome) ላይ የተመሠረተው ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲሁም በየክፍለ አህጉሩ የሚገኙት የፍትሕ ተቋማት ከሐገሮች የሚቀርብላቸውን አለመግባባቶች ዓለም አቀፍ ሕግጋትንና መርሆዎችን መሠረት በማድረግ ውሣኔ ያስተላልፋሉ።
ከላይ የተዘረዘሩትን የዓለም አቀፍ ሕግ አይነቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው ሕጋዊ ተቀባይነትና ተፈጻሚነት በአጭሩ ማየቱ ጠቃሚ ነው። በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ-አንቀጽ (4) ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የኢትዮጵያ የሕግ አካል መሆናቸውን ይደነግጋል። ከተጠቀሱት የዓለም አቀፍ ሕግ አይነቶች ሕገ-መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሕግ አካል ያደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን (International Agreements) ብቻ ነው። ስምምነቶቹም የኢትዮጵያ ሕግ አካል የሚሆኑት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው (ratification) እንደሆነ ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ያላፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የኢትዮጵያ ሕግ አካል አይደሉም። በዚህም መሠረት ዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሕጎች፣ ከበለፀጉት ሐገሮች የተገኙ አጠቃላይ የዓለም አቀፍ የመርዕ ሕጎች፣ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ውሣኔዎች እና የዓለም አቀፍ ምሁራን ጽሁፎች በአንቀጽ 9(4) አባባል የኢትዮጵያ ሕግ አካል አይደሉም። ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ግን በሐገር ውስጥ ተረቀው እንደፀደቁ ሕጎች ተፈፃሚነት አላቸው።
እንደሚታወቀው በሐገራቸን ሕጎች ላይ የተጻፉ ማብራሪያዎችም ሆነ ትችቶች በጣም ጥቂት ናቸው። በተለይም በሃገሪቱ ቋንቋ የተፃፉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከዚህ አኳያ ፅሁፉ የራሱ የሆነ በጎ አስተዋፆ የኖረዋል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ጽሑፍ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት የሚያልፉበትን ሂደትና ሐገሮች ዓለም አቀፍ ሰምምነቶችን በነጋሪት ጋዜጣ ስለማተም ያላቸውን ልምዶችና ሕጎቻቸውን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሕጎች የበላይና የበታች አሠላለፍ ላይ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ትክክለኛ ቦታ ወይም ደረጃ የት እንደሆነ ለመመርመር ይሞከራል። ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸው የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሣኔዎች በማስረጃነት ቀርበዋል። በተጨማሪም ጉዳዩን በንጽጽር ለማየት የሌሎች ሐገሮች የሕግ መዓቀፎች እና ልምዶች ለመዳሰስ ተሞከሯል።
2. ዓለም አቀፍ ስምምነቶች (Treaties or Convention)
ዓለም አቀፍ ስምምነት ሉአላዊ ሐገሮች የተሰማሙበት አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሕጋዊ የጽሑፍ ሰነድ ሲሆን የሚመራው በዓለም አቀፍ ሕግ ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሉአላዊ አገሮች አሁን አሁን ድግሞ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ስውነት ያላቸው ድርጅቶች በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አካባቢያዊ /ክልላዊ/ ጉዳዩችን መሠረት በማድረግ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ድፕሎማሲያዊና ባሕላዊ ርዕሶች ዙሪያ አስገዳጅ የሆኑ ደንቦችን እና መርሆችን በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል የሚገቡባቸው አስገዳጅ ስምምነቶች ናቸው ማለት ይቻላል።
በዓለም አቀፍ ሕግ ውስጥ “Treaty”, “Convention”, “Pact”, “Agreement”, “Protocol”, እና “Instrument” በሚሉት ቃላት መካከል አንድና ወጥ የሆነ አጠቃቀም የለም። የሁሉም ቃላቶች ትርጉም በተመሳሳይነት የሚያመለክትው መንግሥታት ያደረጓቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ነው። የቃላቶቹ አመራረጥ የሚመራው በየሐገሮቹ ፍላጎት ስለሆነ ተመሳሳይ የሆነ አጠቃቀም የለም። በዓለም አቀፍ ሕግ ፍልስፍና ውስጥ ዓለም አቀፍ ሕግ የብሔራዊ ሕግ አካል የሚሆንበትን ግንኙነትና ትስስር የሚያሳዩ ቀደምትነት ያላቸው ሁለት ጽንስ ሀሳባዊ ሞዲሎች እንዳሉ እና በአሁኑ ወቅት ሰፊ ተቀባይነትን እና እውቅናን ያገኙ መሠረተ ሀሳቦች ናቸው። እነዚህም “Monism” (አህዳዊ) ሞዲል እና “Dualism” (መንታዊ) ሞዲል በመባል የሚታወቁት ናቸው። የመጀመሪያው (አህዳዊው) ቅድሚያ የሚሰጠው በዓለም ዓቀፍ ሕግ እና በብሔራዊ ሕግ መካከል አለ ለሚባለው ልዩነት እውቅና ስለማይሰጥ ወይም ሁለቱ የሕግ ሥርዓቶች አንድ ናቸው ከሚል መሠረተ ሃሳብ ስለሚነሳ በሁለቱ የሕግ ሥርዓቶች መካከል ግጭት ሊፈጠር የሚችልበት ክፍተት የለም የሚልውን የቀበላል። ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት ዓለም ዓቀፍ ሕግ እና ብሔራዊ ሕግ የአንድ ሥርዓት ሕግ አካል ናቸው የሚል ነው። በሁለቱ የሕግ ሥርዓቶች መካከል ያልተጠበቀ ግጭት ቢፈጠር የሕጉ አተረጓጎም እና አተገባበር ለዓለም አቀፍ ሕግ የበላይነት መስጠት አለበት የሚል ነው። የዚህ ጽንሰ ሃሳብ መከራከሪያ የብሔራዊ ሕግ መሠረታዊ ደንቦች በዓለም አቀፍ ሕግ ደንቦች ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ለብሔራዊ ሕጎች ሕጋዊነት ማረጋገጫው የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ ደንቦች ናቸው። ለብሔራዊ ሕግ አስገዳጅነት እና ተፈፃሚነት ዋነኛው መስፈርት ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር ያለው መጣጣም ነው። ብሔራዊ ሕግ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር ከተቃረነ ውድቅ ሆኖ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች ገዥ ሆነው ቀጥታ በሐገር ውስጥ ተፈጻሚ ሊደረጉ ይገባል የሚለወን መሠረተ ሃሳብ ይቀበላል።
ሁለተኛው ሞዴል ለመጀመሪያው ሞዴል ተጻራሪ ሆኖ የቆመ ሲሆን የበለጠ ክብደት የሚሰጠው የብሔራዊ የሕግ ሥርዓት እና የዓለም አቀፍ የሕግ ሥርዓት የሚመሩትና የሚቆጣጠሩት ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ጉዳዩችን በመሆኑ በመካከላቸው ግጭት ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ የለም የሚለውን ይቀበላል። ዓለም አቀፍ ሕግ በምንግሥታት መካከል ያለውን የጎንዩሽ ግንኙነት (Horizontal Relationship) የሚገዛ ሥርዓት ሲሆን ብሔራዊ ሕግ ግን በመንግሥትና በሐገሪቱ ዜጎቹ ወይም ነዋሪዎች መካከል ያለውን የቀጥታ ግንኙነት (Vertical Relationship) ለመምራትና ለመቆጣጠር ሲባል የሚውል ሥርዓት ነው። የብሔራዊ ሕግ የትኩረት አቅጣጫ የሐገሪቱ ዜጎች ወይም ነዋሪዎች ሲሆኑ የዓለም አቀፍ ሕግ የትኩረት አቅጣጫ መንግሥታት ናቸው። ብሔራዊ ሕግ በአንድ ሐገር ውስጥ ያሉ ጉዳዩችን ሁሉ የሚገዛና የአንድ ሐገር ወሰነ-ሥልጣን (Jurisdiction) ብቻ የሚመለከት የውስጥ ሕግ ነው፣ የአንድን ሐገር መንግሥትና ዜጎች የሚያስተሳስር ዋነኛ መሳሪያ ሲሆን ዓለም አቀፍ ሕግ በመንግሥታት መካከል ያለውን የውጭ ጉዳዩችና ግንኙነት የሚገዛ ሕግ ነው። በመሆኑም ብሔራዊ ሕግ እና ዓለም አቀፍ ሕግ እያንዳንዳቸው የተለያዩ እና በራሳቸው ጉዳይ ዙሪያ የበላይ ናቸው የሚለወን መሠረተ ሃሳብ ገዥ አድርጎ ይቀበላል።
3. ዓለም አቀፍ ስምምነትን የብሔራዊ ሕግ አካል የማድረግ ሥርዓት በኢትዮጵያ
«ዓለም አቀፍ ስምምነትን መዋዋል» (Treaty-Making) የሚለው አገላለጽ ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ መደራደርን፤ በረቂቁ ላይ ምልክት (ፓራፍ) ማድረግን፤ መፈራረምን፤ ዓለም አቀፍ ስምምነትን መቀበልን፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቱ የጸደቀበትን ሰነድ መለዋወጥን፤ ብሔራዊ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ስምምነቱን ያጸደቀበትን አዋጅ አሳትሞ ማውጣትን እና ከምንግስታትም ሆነ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት በሐገሩ ሕግ መሠረት የተፈጸመና በሕግ የተደገፈ መሆኑን እና ፈራሚውም ባለሥልጣን ዓለም አቀፍ ስምምነቱን ለመዋዋል ተገቢው ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ማረጋገጥንም ያጠቃልላል። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሕግ ከመሆናቸው በፊት በየሐገሮቹ የሥራ አስፈፃሚው አካል ድርድር እና ውይይት (Negotiation) ይካሄድባቸዋል። ከእነዚህ ረጅም ሂደቶች በኃላ በየሐገሮቹ ሕግ ሆነው ለመቀጠል የግድ የብሔራዊ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶችን ይሁንታ አግኝተው መፅደቅ አለባቸው።
አገራችን ኢትዮጵያ ረጅም የመንግሥትነት ታሪክ እና የነፃነት ተጋድሎ ያላት በመሆኑ ከብዙ ዘመን ጀምሮ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ስትፈርምና ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች። በንጉሱ ዘመን የነበሩት የ1931 ዓ/ም ሕገ-መንግሥት እና የ1955ቱ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት በወቅቱ ለነበሩት የሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የማፅደቅ ሥልጣን አልሰጣቸውም ነበር። ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የመዋዋል ሆነ በሐገር ውስጥ ስምምነቶቹን የማፅድቅ ሥራ ሙሉ በሙሉ የሥራ አስፈፃሚው ነበር። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገራችን ሕግ አካል የሚሆኑት ንጉሱ ካፀደቋቸው ብቻ ነበር። የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የማፅደቅ ሥልጣን የሰጠው ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ነው። የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 55 (12) እንዲህ ይነበባል፦
«የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የሕግ አስፈፃሚው አካል የሚዋዋላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያፀድቃል»
በዚህ አንቀጽ መሠረት በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዙሪያ የመደራደር፣ የመፈረምና የመዋዋል ሥልጣን የሥራ አስፈፃሚው ነው። ይህ የሥራ አስፈፃሚው ኃላፊነት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 77 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሚለው ሥር በግልጽ የተቀመጠ አይደለም። የፌዴራል ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የሥራ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወስን በወጣው አዋጅ ቁጥር 4/1987 አንቀጽ 25 (2) ውስጥ በግልጽ እንደተደነገገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስፈፃሚውን በመወከል አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ከሌሎች ሐገሮች ጋር የምታደርጋቸውን ስምምነቶች ለመደራደርና ለመፈረም ሥልጣን ተሰጥቶታል። ይሁንና ሥራ አስፈፃሚው ኢትዮጵያን ወክሎ የሚዋዋላቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በቀጥታ የሐገር ውስጥ ሕግ ሆነው ይሠራባቸዋል ማለት እንዳለሆነ ግልጽ ነው። አስፈፃሚው የፈረመውን ስምምነት የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ውይይት
ካደረገበት በኃላ ስምምነቱን ያፀደቀው ከሆነ የፀደቀው ዓለም አቀፍ ስምምነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት በተፈረመ ጊዜ ወይም ለፕሬዚዳንቱ ከደረሰ ከ15 ቀናት በኃላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣ ይደረጋል።
4. ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በነጋሪት ጋዜጣ ስለማተም /Publication of Treaties or Convention
በሕግ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ውስጥ የመጨረሻ ሂደት ነው የሚባለው የሕትመት ደረጃ (Publication Stage) ነው። ስለዚህ የሕግ አወጣጥ ሂደት ተጠናቆ ሕጉም አስገዳጅ ሆኖና የሕግነት ደረጃ አግኝቶ በሥራ ላይ ዋለ የምንለው ከሕትመት ሥነ-ሥርዓት በኃላ ነው። በቀላሉ መረዳት እንደሚቻለው የሕትመት ዋና ዓላማ ሕጎችን ለማሕበረሰቡ፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለዳኞች፣ ለዐቃቢያነ-ሕግ፣ ለጠበቆች እና ለፍትሕ አካላት እንዲሁም በሐገር ውስጥ መዋለነዋያቸውን ኢንቭስት ማድረግ ለሚፈልጉ የውጭ ሐገር ዜጎች በተሰማሩባቸው መስኮች የሚገኙ ሕጎችን እንዲያውቁ ወይም ተደራሽ ለማድረግ ነው። በሌላ አገላለጽ በአንድ ሐገር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎችና ቡድኖች የተፈቀዱ መብቶችንና ግዲታዎችን በማሳወቅ እጣ ፈንታቸውንና ምርጫቸውን እንዲወስኑ ማስቻል ነው። ደግሞም አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ያላወቀውን ሕግ እንዲያከብር መጠበቅ ፍትሕ አልባነት ነው። ሕግን ሳያሣውቁ በተፈፀሙ ድርጌቶች ሰዎችን መቅጣት አይን ያወጣ ፍትሕ አልባነት ነው።
ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከማተም ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያገኙ ሁለት መሠረተ ሃሳቦች አሉ። የመጀመሪያው መሠረተ-ሃሳብ ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ባለው የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እንዲወጡ ሕገ-መንግሥቶቻቸው የሚያስገድዷቸውን ሐገሮች የመለከታል። በእነዚህ ሐገሮች ሕጎች እና የዳበሩ አሰራሮች መሠረት በሕዝብ ተወካዩች መክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እስካልወጡ ደረስ ብሔራዊ የመንግሥት ሕግ አይሆኑም ተፈፃሚነት አይኖራቸውም። በሌላ አነጋገር በእነዚህ ሐገሮች የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ብሔራዊ የመንግሥት ሕግ እንዲሆኑ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው መውጣታቸውን እንደ ቅደም ሁኔታ የሚያዩ ሐገሮች ናቸው። ለምሳሌ በፈረንሳይ፣ በፖርቱጋል፣ በቻድ ፣በቺሊ ፣በርዋንዳ ፣ክሮሺያን ጨምሮ በብዙ የምስራቅ አውሮፓ ሐገሮች እና በእንግሊዝ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እንዲወጡ ማድረግ መሟላት ያለበት የሕግ ሁኔታ ነው። በእነዚህ ሐገሮች የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በዜጎችና በነዋሪዎች ዘንድ ገዥነትና አስገዳጅነት የሚኖራቸው በሕግ ጋዜጣ ታትመው በአዋጅ መልክ ሲገኙ ብቻ ነው።
የሁለተኛው መሠረተ-ሃሳብ ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ባለው የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አስገዳጅ እና ተፈፃሚ የሆኑ ዘንድ በነጋሪት ጋዜጣ መታወጅን ወይም መታተምን እንደ ቅደመ ሁኔታ አድረገው የማይቆጥሩ ሐገሮችን ይመለከታል። በእነዚህ ሐገሮች ሕጎች እና አሰራሮች መሠረት ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሕዝብ ተወካዩች መክር ቤት እንደ ጸደቁ ወዲያውኑ ያለሌላ ተጨማሪ ሕጋዊ መስፈርት ብሔራዊ የመንግሥት ሕግ ሆነው ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል። በሌላ አነጋገር እነዚህ ሐገሮች የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሮቻቸው የሕግ አካል እንዲሆኑ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው መውጣታቸውን አስፈላጊ ሕጋዊ ሁኔታ አድርገው አይወስዱም። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ከሴኔት አባላት መካከል የሁለት ሦስተኛውን አብላጫ ድምጽ ድጋፍ አግኝቶ በፕሬዚዳንቱ የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ እንዲወጣ ማድረግ አስፈላጊ አይደልም። በመሆኑም የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ታውጀው ባይወጡም እንኳ ተፈፃሚ እና ውጤት እንዲኖራቸው የማድረግ ግዴታ አለባቸው።
ወደ ሐገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ ከላይ ካየናቸው ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች ውስጥ ኢትዮጵያ ከየትኛው ምድብ እንደምትካተት ግልጽ አይደለም። በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች አስገዳጅ የሕግ ውጤት ያገኙ ዘንድ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልግ ወይም አያስፈልግ እንደሆነ በሕግ ባለሙያዎች፣ በዳኞችና በሕግ ምሁራኖች መካከል አንድና ወጥ የሆነ አመለካከት ወይም የጋራ መግባባት አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። በዚህ ጉዳይ ላይ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ።
የመጀመሪያው አመለካከት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው በነጋሪት ጋዜጣ የመታተማቸውን አስፈላጊነት በመደገፍ ይቆማል። በዚህ አመለካከት መሠረት በነጋሪት ጋዜጣ የማተም አስፈላጊነት በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት እየወጡ እንዳሉ ሕጎች ሁሉ በጸደቁ የዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ላይ ተፈጻሚነት አለው የሚል ነው። የዚህ አመለካከት አራማጆች አዘውተረው በዋቢነት የሚጠቅሱት የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 3/1987 አንቀጽ 2(3)ትን እና የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 71(2) ነው። በዚህ አዋጅ አንቀጽ 2(3) መሠረት የፌዴራል ሕጎች በፍርድ ቤት እንዲታወቁና ተፈጻሚነትንም ያገኙ ዘንድ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ እንዲታተሙ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ እንዲያውጅ ለፐሬዚዳንቱ ሥልጣን ተሰጥቶታል። እንደ ሌሎቹ የሐገሪቱ ሕጎች ሁሉ የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት መክሮ ያጸደቃቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሕዝቡ ያውቃቸው ዘንድ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው እንዲወጡ ማድረግ ግዲታ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ስለዚህ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሐገሪቱ የሕግ አካል የሚሆነው በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ሲታወጅ ብቻ ነው የሚል አቋም አላቸው።
ሁለተኛው አመለካከት ተቃራኒ አቋምን የያዘ ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት መጽደቅ ብቻ ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ሕጋዊ ውጤት እንዲኖራቸው ያስችላል የሚል ነው። አቋማቸውንም ለማጠናከር እንዲረዳቸው በማሰብ የዚህ አመለካከት አረማጆች የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትን አንቀጽ 9 (4) በዋቢነት ይጠቅሳሉ። የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 (4) እንዲህ ይነበባል፦
«ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ሕግ አካል ናቸው» ተብሎ ተደንግጓል።
በእነዚህ ሕግ ባለሙያዎች የሚቀረበው ክርክር ዓለም አቀፍ ስምምነት የኢትዮጵያ ሕግ አካል የሚሆነው ስምምነቱ እንደጸደቀ ወዲያውኑ ነው። ሕገ-መንግሥታዊው ድንጋጌው በኢትዮጵያ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ብሔራዊ ሕግ አካል ለማድረግ በነጋሪት ጋዜጣ መታወጅን እንደቅድመ ሁኔታ አያስቀምጥም የሚል መከራከሪያ አላቸው። እነዚህ የሕግ ባለሙያዎች የዓለም አቀፍ ስምምነቱ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ መውጣት ወይም አለመውጣቱ በመጽደቅ ተግባር አስቀድሞ ሕጋዊ እንዲሆን ለተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት ሕጋዊነትን የሚጨምር ወይም የሚቀንስ አይሆንም የሚለውን የመከራከሪያ ሃሳብ የሚያራምዱ ናቸው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ታውጀው ባይወጡም የማከበርና ተፈፃሚ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነት አለባቸው የሚለውን መከራከሪያ ያቀርባሉ። የዚህ ጽሑፍ ጸሃፊ፣ በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች፣ ከሁለተኛው አመለካከት ጋር ይስማማል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አንድን ዓለም አቀፍ ስምምነት ሲያፀድቅ ስምምነቱ ውስጥ የተቀመጠውን ግዴታና ኃላፊነት ለመፈፀም ፈቅዶና በስምምነቱ ድንጋጌዎች እንደሚገደድ ተገንዝቦ ነው። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሐገሪቱ የበላይና የመጨረሻ ፍርድ ቤት ሲሆን ኢትዮጵያ ያጸደቀቸውን የዓለም አቀፍ ስምምነት ድንጋጌዎች በዋቢነት በመጥቀስ የሰጣቸውን ውሣኔውችና የሕግ ትርጉሞች በመመርመር፣ የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጻሚ የሚሆነው በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ሲታወጅ ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማገኘት እንችላለን። ለምሳሌ፦
ጉዳይ-1 (Case-1) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች ወ/ት ፀዳለ ደምሴ እና በተጠሪ አቶ ክፍሌ ደምሴ መካከል በሰበር መ/ቁ/ 23632 ለነበረው ክርክር ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንን (The Child Rights Convention) በመጥቀስ ጥቅምት 26 ቀን 2000 ዓ.ም ውሣኔ ሰጥቷል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ የበታች ፍርድ ቤቶች የሠጡትን ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት የሻረው ሲሆን ጉዳዩን «ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል የሕፃናትን መብት በሚመለከት 1984 ዓ.ም የፀደቀውን እና በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 9(4) መሠረት የሀገሪቱ የሕግ አካል የሆነው የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን አንቀጽ 3(1)» መሠረት በማድረግ ከመረመረ በኃላ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች አካላት ሕፃናትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውሣኔ ሲሰጡ የሕፃናቱን ጥቅምና ደህንነት በዋነኛነት ማስቀደም እንዳለባቸውና የሕፃኑ ጥቅምና ደህንነት (The Best Intereset of the Child) የሚጠበቀው በአመልካች በኩል መሆኑን በመተንተን የአሁኗ አመልካች ወ/ሪት ፀዳለ ደምሴ የሕፃን ቢንያም ክፍሌ ሞግዚትና አስተዳዳሪ ሆና ሕፃኑን በመልካም አስተዳደግና ደህንነነት ተንከባክባ እንድታሣድገው ተሹማለች በማለት ወስኗል፡፡
ጉዳይ-2 (Case-2) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች ተስፋዩ ጡምሮ እና በተጠሪ የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን-ዐቃቤ ሕግ መካከል በሰበር መ/ቁጥር 73514 በነበረው የወንጀል ክርክር የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነትን (International Covenant on Civil and Poltical Rights) በመጥቀስ ህዳር 6 ቀን 2005 ዓ.ም ውሣኔ ሰጥቷል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በፍርድ ሐተታው ላይ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕጉ ከመፅናቱ በፊት የምንግሥት ሥራውን ለቅቆ በንግድ ሥራ መሰማራቱ በተረጋገጠው አመልካች ላይ ምንጩ ያልታወቀ ሐብት ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀል ያቀረበበት ክስ ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈፀም ወይም አለመፈፀም ወንጀል መሆኑ ካልተደነገገ በስተቀር ሊቀጣ እንደማይችልና ወንጀሉ በተፈፀመ ጊዜ ተፈፃሚ ከነበረው የቅጣት ጣሪያ በላይ ሊቀጣ እንደማይችል ከደነገገው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 22 (1) እና አገራችን ባፀደቀቸው የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 15 (1) «No one shall be held guility of any criminal offince on account of any act or omission which did not constitute a criminal offince under national or international law, at the time which the criminal offince was committed» በሚል የተደነገገውን የወንጀል ሕግ መርህ የሚጥስና የአመልካችን መብት የሚያጣብብ ነው። የበታች ፍርድ ቤቶች ከላይ የተገለጸውን ዓለም አቀፋዊ መሠረታዊ መርህ በማስፈፀም የዐቃቤ ሕጉን የወንጀል ክስ ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው አመልካች ምንጩ ያልታወቀ ሐብት ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀል የፈፀመ ጥፋተኛ ነው በማለት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ አመልካች በነፃ እንዲሰናበት ሲል ወስኗል።
ጉዳይ-3 (Case-3) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች አለማየሁ ኦላና እና በተጠሪ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (United Nations Development Program) መካከል በሰበር መ/ቁጥር 98541 በነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ክርክር አመልካች የተለያዩ ክፍያዎች በተጠሪ እንዲከሏቸው በወረዳው ፍርድ ቤት በተወሰነው ውሣኔ መሠረት የአፈፃፀም መዝገብ ከፍተው ክርክሩ በመታየት ላይ እያለ ተጠሪ የመከሰስ መብት የለውም ተብሎ የአፃፀም መዝገቡ በሁሉም የበታች ፍርድ ቤቶች መዘጋቱ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ያስቀረባል ከተባለ በኃላ፣ ተጠሪ የተባበሩት መንግሥታት አካል ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ጥቅምና የተለየ ከለላን በተመለከተ በተደነገገ ስምምነትም በማንኛውም መንግሥት ፍርድ ቤቶች ተከሶ መቀረብ የሌለበት መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 105 እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ጥቅምና የተለየ ከለላን በተመለከተ በተደነገገው ስምምነት አንቀጽ 2(2) እና 3 ሥር በግልጽ ተመልክቷል። በመሆኑም ከመነሻውም ኢትዮጵያ በፈረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት፣ ተጠሪ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላለመዳኘት በሕግ የተጠበቀለት የከለላ መብትና ጥቅም እያለው፣ የወረዳው ፍርድ ቤት በሌለው ሥልጣን የሰጠው ውሣኔ እንዲፈጽም ማድረግ፣ በዲፕሎማቲክ ግንኙነቱ ላይ አሉታዊ ውጤት የሚያስከትል በመሆኑ የአመልካችን የአፈፃፀም አቤቱታ አልተቀበልነውም፣ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ሥህተት የለበትም በማለት ወስኗል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን እና የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት አጸድቃለች። ዓለም አቀፍ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን መጽደቁን ብቻ የሚያመለክት እና የስምምነቱን አንቀጾች ሙሉ ቃል ሳይዝ ወጥቷል። የጸደቀው ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አልወጣም። ሌላው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ከመሰረቱ አባል ሐገራት አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ማቋቋሚያ ቻርተሩን ፈርማ አጽድቃለች። የተባበሩት መንግሥታትና በሥሩ የሚገኙ ድርጅቶች እንደአባል መንግሥታት ሉዓላዊ አካል ለመሆናቸው በቻርተሩ አንቀጽ 2(1) ላይ የተደነገገ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታትና በሥሩ የሚገኙ ድርጅቶች እንድሁም የድርጅቶቹ አመራሮች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ጉዳይ፣ በአባል ሐገራት ፍርድ ቤቶች ያለመከሰስ የሕግ ከለላ፣ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር (Charter of the United Nations) አንቀጽ 105 (1)ና (2) ተሰጥቷቸዋል። ይሄው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (United Nations Development Program) በተከሣሽነት ቀረቦ ጉዳዩ ከታየ በኃላ፣ የያቤሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሣሽ የተለያዩ ክፍያዎችን ለከሣሽ እንዲከፍል ሲል ውሣኔ ሰጥቷል። የወረዳው ፍርድ ቤት ውሣኔ በይግባኝ ያልታረመ ቢሆንም እንኳ ሥልጣን ሳይኖረው፣ ያለመከሰስ የሕግ ከለላ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ደረጅት ላይ የሰጠው ውሣኔ ሊፈፀም የማይችል ነው ተብሎ የአፈፃፀም አቤቱታው ወድቅ ሆኗል።
ከላይ በግልጽ ባየናቸው ሦስት-ጉዳዩች፣ በኢትዮጵያ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዝርዝር ድንጋጌዎች የእንግሊዝኛው ሙሉ ቃል ከአማረኛ ትርጓሜው ጋር በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ ስላልወጣ ዜጎች፣ ዳኞችና የፍትህ አካላት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቀላሉ ሥለ ስምምነቶቹ ይዘት ማወቅ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርና የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ባልወጣበት ሁኔታ፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ሰበር ሰሚ ችሎት የእነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነት ድንጋጌዎች በፍርዱ ላይ በመጥቀስ፣ በመተርጎምና ተፈጻሚ በማድረግ የሰጠው ውሣኔ የሚያስተላለፈው መልዕክት ወይም የሚኖረው የሕግ ውጤት፤ በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታውጀው ባይወጡም በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የማከበርና በፍርዶቻቸው ውስጥ ተፈፃሚ የማድረግ ግዴታና ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ብሔራዊ ሕግ አካል ለማድረግ በነጋሪት ጋዜጣ ማወጅ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ አይደለም።
በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት መካከል ስላለው ደረጃ (Hierarchy of Treaties/Convention Verses the FDRE Constitution)
ሕጎች በባህሪያቸው፣ በተፈጥሮቸው፣ በአደረጃጀታቸው፣ ሊያስከብሩት በፈለጉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ምህበራዊ አላማዎች ክብደት፣ በሚያወጧቸው አካላት የፖለቲካ ሥልጣን ክብደት ወ.ዘ.ተ የተለያዩ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች እያሉ የሕጎች ሁሉ ደረጃ እኩል ነው ቢባል የሚያስኬድ አይደለም። ሥለዚህ በተለያዩ የሕግ አይነቶች መካከል አንዱ ከሌላው የበላይ ወይም አንዱ ከሌላው የበታች የመሆን ባህሪ በመደበኛ አጠራሩ የሕጎች ደረጃ (Hierarchy of Laws) እየተባለ የሚጠራው ነው። የሕጎች ደረጃ በሕጎች መካከል የሚኖረውን የከፍና ዝቅ፣ በሕጎች መካከል ያለውን ተዋረድና የበላይና የበታችነት (Superior-Inferior relation) ግንኙነት የሚመለከት ነው። ይህም ማለት ሕጎች በሙሉ በእኩልነት ደረጃ የሚታዩ ሳይሆኑ አንዱ ከሌላው የመብለጥ ወይም የማነስ ደረጃ አለቸው። የዳኝነት ሥርዓቱ በአንድ አከራካሪ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ሲሞክር በሕጎች መካከል አለመግባባት፣ ግጭትና ተቃርኖ ማጋጠሙ የተለመደ ነው። የዳኝነት አካሉም አንዱን ሕግ መርጦ ለጉዳዩ እልባት መስጠት አለበት። ምርጫውን ለማካሄድና አለመግባባቱን ለመፍታት በጣም የተሻለው መንገድ የሕጎችን ደረጃ ማወቅ ነው። በዚሁ መሠረት የበታች ሕጎች የበላይ ሕጎችን በምንም አይነት መቃረን አይችሉም። ተቃርነው ቢገኙ የበታች ሕጎች ውድቅ ሆነው የበላይ ሕጎች ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል። ሥለሆነም የአስተዳደር መመሪያዎችና ደንቦች በምንም መልኩ አዋጆችን፤ አዋጆች ደግሞ ሕገ-መንግሥትን ሊቃረኑ አይገባም፣ ሆኖም ከተገኘም የበላይ የሆነውን ሕግ በመምረጥ ለጉዳዩች እልባት እንሰጣለን። ስለ ሕጎች ደረጃ ለመግቢያ ያህል ይህን ካልኩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ያላቸውን ደረጃ እንመልከት።
በኢትዮጵያ የሕጎች የበላይና የበታች አሠላለፍ ላይ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ትክክለኛ ቦታ ወይም ደረጃ የት እንደሆነ ባለመታወቁ በሕግ ምሁራኖች መካከል ብዙ ክርክሮችን እየጋበዘ ያለ አጀንዳ ነው። የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከአንድ ሐገር ሕገ-መንግሥት ጋር ሊጋጭ ይችላል። በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-መንግሥቱ የበላይ የሆነ ደረጃ ሊሰጠው፣ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በእኩል ደረጃ ሊገኝ፣ ወይም ከሕገ-መንግሥቱ የበታች የሆነ ደረጃ ሊያገኝ ይችላል። በዚህ ጉዳይ ላይ በሁሉም ሐገሮች ተመሳሳይና አንድ ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍና አሰራር የለም።
በኔዘርላንድ እና በስዊስ ሕግ መሠረት የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ከተቃረነ ዓለም አቀፍ ስምምነቱ የበላይነት አለው። በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-መንግሥቱ የበላይ ነው የሚል መከራከሪያ አለ። ለዚህ አመለካከት አንደኛው ምክንያት፣ ዓለም አቀፍ ሕግ በአባል መንግሥታት ላይ አስገዳጅነት አለው፣ ሐገሮች ዓለም አቀፍ ሕግን በግዛታቸው ውስጥ እንዲከበር የማያደርጉ ከሆነ የሕግ ኃላፊነትን ያስከትልባቸዋል የሚለው ነው። በዚህ አመለካከት መሠረት አባል መንግሥታት ከዓለም አቀፍ ግዴታዎቻቸው እራሳቸውን ለማሸሽ ሲሉ በሕገ-መንግሥቶቻቸው ሊመኩ አይችሉም። ዓለም አቀፍ ሕግ ከሕገ-መንግሥቱ የበላይነት እንዳለው የቬና ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ እደተጠቀሰው የአንድ የዓለም አቀፍ ስምምነት አባል መንግሥት የሆነ ስምምነቱን ተፈፃሚ ላለማድረግ በማሰብ ሕገ-መንግሥቱን መጥቀስ አይችልም በማለት ይደነግጋል። ይህንን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁራን የዓለም አቀፍ ሕግን የበላይነት በመደገፍ ይከራከራሉ።
ሁለተኛ ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 13(2) «በምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች እና ዓለም አቀፍ ሠነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ» ከሚለው የድንጋጌው ይዘት በሚሰጠው ትርጉም የሚወሰን ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነት ከሕገ-ምንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ድንጋጌዎች የበላይ ሊያደርገው የሚችል ሁኔታ ያለ መስሎ የሚታየው በአንቀጽ 13(2) ሥር ያለውን «በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ» የሚለውን ሐረግ ስናጤነው ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ተጣጥመው ይተረጓማሉ ሣይሆን የሚለው የምዕራፍ ሦስት የሕገ-መንግሥቱ አንቀጾች ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ተጣጥመው መተርጎም አለባቸው ስለሚል ነው። በአንድ በኩል የሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ድንጋጌዎችን በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ ጥገኛ የሚያደርግ ይመስላል። በሌላ በኩል ሕገ-መንግሥቱ ከዓለም አቀፍ ስምምነት ጋር ተጣጥሞ ይተርጎም ሲባል ከፍ ያለ ደረጃ የተሰጠው ለዓለም አቀፍ ስምምነቱ ይመስላል፤ ለዚሁ ክፍል ከፍ ያለ ደረጃ ከተሰጠው ደግሞ ሁለቱ በተቃረኑ ጊዜ የዓለም አቀፍ ስምምነቱ የበላይ ሆኖ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት ነው።
በአንቀጽ 13(2) ላይ ትኩረት ያደረጉ ምሁራን ሰብዓዊ መብቶችን እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የተመለከቱት የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሲተረጎሙ እጅግ ዘመናዊ፣ ጥልቀትና ምጥቀት ባለው መንገድ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ከሚያደርጉት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችና ሥነዶች ጋር ተጣጥመው ይተርጎሙ መባሉ ቢያንስ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በተመለከተ ያሉት የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገዥና የበታች መሆናቸውን ያመለክታል ባይ ናቸው።ዛሬ ለሰው ልጆች የሰብዓዊ መብቶች የሚደረገው ጥበቃ መነሻው ከሁለተኛው የዓለም ጦረነት ማግስት አድርጎ በፍጥነት እየሠፋና እየጠለቀ በመሄድ ላይ ነው። ሥለዚህ በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ውስጥ የተካተቱት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በፍጥነት እያደገ ከሚሄደው ዓለም አቀፍ የሰብዓዎ መብት ጥበቃ ጋር ተጣጥመው ቢተረጎሙ የተሻለ ነው በማለት ክርክራቸውን ያጠናክራሉ። ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ የቆመ የፍትህ ሥርዓት ሰብዓዊ መብቶችን የበለጠ ለሚንከባከብ ዓለም አቀፋዊ ሰነዶች የበላይነት መስጠቱ ምን ላይ ነው ችግሩ ሲሉ በአፅንኦት ይጠይቃሉ። በዚህ ወገን ያሉት ምሁራኖች ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ከሕገ-መንግሥቱ በላይ ናቸው የሚል የፀና አቋም አላቸው።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር እኩል የሆነ ደረጃ የሚሰጥባቸው ሐገሮች አሉ። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ የፀደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከዩናይትድ ስቴትስ ሕገ-መንግሥት ጋር በእኩል ደረጃ ይታያሉ። በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 4 ፓራግራፍ 2 በግልጽ እንደተደነገገው ሕገ-መንግሥቱን እስካልተቃረነ ድረስ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ልክ እንደ ሕገ-መንግሥቱ የሐገሪቱ የበላይ ሕጎች ናቸው። በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር እኩል የሆነ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል ማለት ይቻላል። በተመሳሳይ በእኛም ሐገር በንጉሱ ጊዜ የነበረው የ1955ቱ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 122 በግልጽ እንደተመለከተው፣ የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር እኩል ደረጃ የተሰጣቸው መሆኑን ይገልፃል።
ሌሎች ሐገሮች ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከሕገ-መንግሥቶቻቸው ያነሰ ደረጃን ይሰጣሉ። በእነዚህ ሐገሮች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሕገ-መንግሥቱን ከተቃረኑ ተፈጻሚነትን አያገኙም። ለምሳሌ በፖርቱጋል እና በግሪክ፣ ሕገ-መንግሥት ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች የበለጠ ደረጃ አለው። በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥቱ ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች የበላይነት አለው የሚሉት ወገኖች የሚከተሉትን የመከራከሪያ ድንጋጌዎች በዋቢነት ያነሳሉ። የመጀመሪያው በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት የጸደቁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ሕግ አካል ናቸው። በመቀጠል ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 55(12) መሠረት ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲያጸድቅ ሥልጣን ስለተሰጠው እነዚህ ስምምነቶች ከአዋጅ ጋር በእኩል ደረጃ እንዲገኙ ያረጋቸዋል ይላሉ። ሕገ-መንግሥቱ በኢትዮጵያ የበላይነቱን የሚደነግገው በግልጽና በማያሻማ አኳኃን ነው። የእውም በአንቀጽ 9(1) «ሕገ-መንግሥቱ የሐገሪቱ የበላይ ሕግ ነው» ብሎ ከደነገገ በኃላ የዚህ ውጤት ምን እንደሆነ ሲደነግግ «ማንኛውም ሕግ (የጸደቀ የዓለም አቀፍ ስምምነትን ይጨምራል)፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለስልጣን ውሣኔ ከዚህ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም» በማለት ይደመድማል። ሕገ-መንግሥት የሐገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ እንደመሆኑ መጠን ለዓለም አቀፍ ስምምነቶችም የበላይ የሆናል። ይህ የክርክር መስመር እንደሚያሳየው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ትክክለኛ ደረጃ ከሕገ-መንግሥቱ በታች ከአዋጅ ጋር እኩል የሚል ነው። ሆኖም የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 13(2) ከሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት ሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር ተጣጥመው ይተርጎሙ ማለቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደማገናዘቢያነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ለማሳየት ተፈልጎ ነው ባይ ናቸው። ወደነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የምናመራው በምዕራፍ ሦስት ያሉት ድንጋጌዎች ግልፅነት ሲጎላቸው፣ አሻሚና አጠርጣሪ ሲሆኑ ብቻ ነው። በዚህም ለትርጉምና ለማገናዘቢያ ብቻ ዋጋ ያላቸው መሆኑን የሚጠቁም አንቀጽ እንጂ ሕገ-መንግሥቱን የበታች ለማድረግ የተደነገገ አይደለም ይላሉ።
ሌላኛው መከራከሪያቸው የብሄራዊ ሉአላዊነት (National Sovereignty) ፅንሰ ሃሳብ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉአላዊነት የሚገለጽበትን ሕገ-መንግሥት ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገዥ ይሁን የሚባል ከሆነ መንግሥት በውሣኔ ሰጭነት ያለውን ሚና ያዳከማል፤ ሕጎችን ከብሄራዊና ሕዝባዊ ጥቅም አኳያ ለመቅረጽ ሙሉ ሥልጣኑን መጠቀም አይችልም፤ በአጠቃላይ የሐገር ሉአላዊነት የሚባለው ጉዳይ ትርጉም የለሽ ይሆናል በማለት ይከራከራሉ። በመጨረሻ የሚያነሱት መከራከሪያ የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች ያላቸውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ነው። ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ እንደተቻለው በሕገ-መንግሥቱ ረቂቅ ውይይት ወቅት በዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች መካከል ግጭት ቢፈጠር እንዲት መፈታት ይቻላል በሚል ለተነሳው ጥያቄ የተደረሰው መደምደሚያ ለሕገ-መንግሥቱ ቅድሚያና የበላይነት መሰጠት እንዳለበት ነው።
በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በአዋጅ መካከል ስላለው ደረጃ (Hierarchy of Treaties/Convention Verses National Legislation)
በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሐገሮች እንደ አዋጅ ያሉት የመጀመሪያ ደረጃ ሕጎች የሚወጡት በሕገ-መንግሥት የሕግ አውጪነት እውቅና በተሰጠውና ከሕዝብ በቀጥታ በተመረጡ አባላት በተዋቀረው የሕግ አውጪ ምክር ቤት አማካኝነት ነው። ይህ ሕግ አውጪ አካል በተለያዩ ሐገሮች የተለያየ ስም፣ ሥልጣን እና አወቃቀር አለው። ለምሳሌ ዱማ በሩሲያ፣ ኮንግረስ በአሜሪካ፣ ፓርላማ በእንግሊዝ፣ መጅሊስ በኢራን፣ ቡንዲስታግ በጀርመን እና የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በኢትዮጵያ በመባል ይታወቃሉ። አዋጅ በተወካዩች ምክር ቤት የሚወጣ ሕግ ሲሆን በደረጃው ከሕገ-መንግሥቱ በታች የሚገኝ እና አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ከሚያወጣቸው ደንቦች የበላይ ነው። ከዚህ መሠረተ ሃሳብ በመነሳት በኢትዮጵያ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት በደረጃው ከሕገ-መንግሥቱ በታች የሚገኝ ሲሆን በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከሚወጣ አዋጅ ጋር እኩል ወይም ተመሳሳይ ደረጃ አለው የሚል አተያይና አረዳድ አለ።
በፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነትና በአዋጅ መካከል ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ስምምነቱ ከአዋጅ የበላይነት ያለው ወይም የሌለው ስለመሆኑ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የሚናገረው ነገር የለም። በመሆኑም በዓለም አቀፍ ስምምነትና በአዋጅ መካከል የተፈጠረ ግጭት እኩል ደረጃ ባላቸው ሁለት ብሔራዊ ሕጎች መካከል እንደተፈጠረ ግጭት ይቆጠራል። ሁለት የእኩልነት ደረጃ (ማዕረግ) ባላቸው ሕጎች መካከል ተቃርኖ ወይም ግጭት ሲፈጠር ይህን ተቃርኖ ወይም ግጭት ለመፍታት የምንጠቀመው የአተረጓጎም ሥልት፣ በኃላ የወጡ ሕጎች ቀድመው የወጡትን ሕጎች ይሽሯቸዋል (the latter prevails over the former, i.e. repeal of a legislation by latter legislation of equal status) የሚል ነው። ቅድሚያ የምንሰጠው ለኃለኞቹ ሕጎች ነው። ከዚህ መሠረተ-ሀሳብ በመነሳት «በኃላ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ቀደም ሲል ከወጣ አዋጅ የበላይነት እንዳለው፤ በኃላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል ከፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት የበላይነት አለው» የሚለውን የመከራከሪያ ሀሳብ የሚያቀርቡ የሕግ ባለሙያዎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ነው።
በእኔ በኩል «የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከአዋጅ ጋር እኩል ወይም ተመሳሳይ ደረጃ አለው እንዲሁም በኃላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል የፀደቀን ዓለም አቀፍ ስምምነት ይሽረዋል» የሚለውን የመከራከሪያ ሀሳብ የማልስማማበትን እና እሳቤው የዓለም አቀፍ ሕግን የቃረናል የምልበትን ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ከዚህ በታች አቀርባለሁ።
አንደኛው ምክንያት፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት የቃል ኪዳን ሰነዶች፣ አባል መንግሥታት የፈረሟቸውን ስምምነቶች የማከበር፣ የማስከበር፣ የማሟላት እና የማቀላጠፍ ግዲታ ይጥልባቸዋል። አባል መንግሥታት በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት የቃል ኪዳን ስምምነት ዕውቅና እና ጥበቃ የተሰጣቸውን መብቶችና ሕግጋት ከመጣስ በመታቀብ ሰብአዊ መብቶችን የማከበር ግዴታ አለባቸው። በመሆኑም አባል ሐገራት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ጋር የሚቃረን አዋጅ በግዛታቸው ተፈፃሚ ባለማደረግ የተጣለባቸውን ሰብአዊ መብቶች የማከበር ግዴታ መውጣት አለባቸው። በሰብዓዊ መብት የቃል ኪዳን ስምምነቶች የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች አባል መንግሥታት ማከበር አለባቸው። መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን የማከበርና የማስከበር ግዴታውን የሚወጣው አስፈላጊውን የሕግ አስተዳደርና ሌሎች እርምጃዎች በመውሰድ እንደሆነ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ተደንግጓል። ነገር ግን አባል መንግሥታት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ጋር የሚቃረን አዋጅ ተፈፃሚ በማደረግ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎቹን እና ስምምነቶቹን ቀሪ ማድረጋቸው ወይም መሻራቸው የተጣለባቸውን ሰብአዊ መብቶች የማከበርና የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት እንደጣሱ የሚያስቆጥር እና ዓለም አቀፍ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ተግባር ስለሆነ ከመነሻው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትና ስምምነቶች የሚሽር ሕግ ማውጣት አይችሉም።
ሁለተኛው ምክንያት፣ ማንኛውም ዓለም ዓቀፍ ስምምነት አስገዳጅ ከመሆኑ በፊት በአባል መንግሥታት ፈቃደኝነት መሟላት ያለበት ሥርዓትና ሂደት በቬና የዓለም አቀፍ ስምምነት ሕግ (The Venna Convention on the Law of Treaties) ላይ የተመለከተ ሲሆን ይሄውም መንግሥታት በመጀመሪያ ዓለም አቀፍ አጀንዳ በሆነው ጉዳይ ላይ መደራደርን (Negotiation)፣ ሰነዱ ላይ መፈረምን (Signature)፣ በምክር ቤቶቻቸው ማፅደቅን (Ratification) እና ቀደም ሲል እውቅና ያገኘ ዓለም አቀፍ ስምምነት ሲሆን በመጨመር (Accession) ለዓለም አቀፍ ሕግ ተገዥ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ይህን ዓለም አቀፋዊ ሕግና ሥርዓት ተከትለው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቱን የሐገራቸው የሕግ አካል ያደረጉ አባል መንግሥታት ለሕጉ ተገዥ የመሆን ግዴታ አለባቸው። ስለዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነት የአባል መንግሥታት ፍቃድ የተገለፀበት ተግባር ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው ለአፈፃፀሙ ዓለም አቀፍ ሕግ ዋስትና የሚሰጠው ስምምነት ነው። አንድን ዓለም አቀፍ ስምምነት የፈረመና ያፀደቀ ሐገር ከጊዜ በኃላ በሚያወጣው አዋጅ ዓለም አቀፍ ስምምነቱን መሻር አይችልም። በኢትዮጵያ የፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከአዋጅ ጋር እኩል ደረጃ አለው፣ በኃላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል ከፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት የላቀ ደረጃ አለው በማለት የሚቀርበው መከራከሪያ፣ የቬና ዓለም አቀፍ የስምምነት ሕግን የሚቃረን አተያይና አረዳድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም የሚል እምነት አለኝ። ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ስምምነቶች በአንድ ሐገር ምክር ቤት ፀድቀው የሕግ አካል ሆኑ ማለት ዓለም አቀፍ ባህሪያቸውን ይለቃሉ ማለት አይደለም። አንድ አባል ሐገር በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማሀበራዊ ምክንያቶች የገባበትን ዓለም አቀፍ ስምምነት ቀሪ ስለሚያደረግብት፣ ስለሚያቋርጥበት እና ከስምምነቱ ስለሚወጣበት ሂደት የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በቬና ዓለም አቀፍ የስምምነት ሕግ ላይ በግልጽ ተደንግጓል። አንድ አባል ሐገር የዓለም አቀፍ ሕግና ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት ዓለም አቀፍ ስምምነቱን ቀሪ በማድረግ አባል ከሆነበት ዓለም አቀፍ ስምምነት መውጣት ይችላል። ከዚህ ውጭ ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ስምምነቶች በእዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በመፀድቃቸው ብቻ ከአዋጅ ጋር እኩል ደረጃ አላቸው፣ በኃላ የወጣ አዋጅ ቀደም ሲል ከፀደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት የበላይነት አለው በሚል የሚቀርበው መከራከሪያ ከላይ በዘረዘርኳቸወ መሰረታዊ የሕግ ምክንያቶች ስህተት አለበት እላለሁ። በመሆኑም በእኔ እምነት በኢትዮጵያ የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከአዋጅ የላቀ ወይም የበለጠ ደረጃ ያለው የመስለኛል።
ማጠቃለያና የመፍትሄ ሀሳቦች
1. ዓለም አቀፍ ስምምነት ሉአላዊ ሐገሮች የተሰማሙበት አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ሕጋዊ የጽሑፍ ሰነድ ሲሆን የሚመራው በዓለም አቀፍ ሕግ ነው። ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሉአላዊ አገሮች አሁን አሁን ድግሞ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ስውነት ያላቸው ድርጅቶች በዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አካባቢያዊ /ክልላዊ/ ጉዳዩችን መሠረት በማድረግ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ድፕሎማሲያዊና ባሕላዊ ርዕሶች ዙሪያ አስገዳጅ የሆኑ ደንቦችን እና መርሆችን በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል የሚገቡባቸው አስገዳጅ ስምምነቶች ናቸው።
2. በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(4) በግልጽ እንደተደነገገው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሕገ-መንግሥቱን መስፈርቶች አሟልተው እስከተገኙ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ አስገዳጅነት አላቸው። ነገር ግን የስምምነቶቹ ድንጋጌዎች በሐገሪቱ ተፈፃሚነትን እንዲያገኙ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ተዘጋጅተው እንዲወጡ ማድረግ አስገዳጅ አይደል።
3. በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አንድ ሐገር አንድን ዓለም አቀፍ ስምምነት አፀደቀ ማለት ራሱን ለዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ አስገዝቶ ለስምምነቱ እንደቆመ ያመለክታል። በቃል- መታሰር /Pacta Sunt Servanda/ በቬና ዓለም አቀፍ የስምምነት ሕግ አንቀጽ 26 ላይ ሰፍሯል፤ አንድ ሐገር ግዴታውን ለመወጣት ስምምነት በሚያደርግበት ወቅት በቅን ልቦና ግዴታውን እንደሚወጣ ያመለክታል። ይህ መርዕ ሀገሮች ለፀደቁ ስምምነቶች ከፍተኛ ቦታ እንዲሰጡ ይጠይቃል።