በከተማችን ሰማይ ላይ የሰፈረ መንፈስ አለ የሆነ ህጻኑን ወጣቱን አዛውንቱን የሚፈታተን መንፈስ፡፡ በራዲዮ ቢራ፣ በቴሌቭዥን ቢራ፣ በቢልቦርዶች ገፅ ላይ ቢራ ሆኗል ከተማው፡፡ ዛሬ ዛሬ ቢሮ ከሚለው ስም ይልቅ ቢራ የሚለውን ስም መስማት የተለማመደ ሆኗል፡፡ እኔም በእለት ተእለት እንቅስቃሴም ውስጥ በሁለት ነገሮች እርግጠኛ ነኝ ከእሁድ በስተቀር ቢሮ እንደምገባና አንድ የቢራ ማስታወቂያ ጆሮየ እንደሚሰማ፡፡ ከወዳጅ ዘመዶቼ ይልቅ አዲሱ ዓመት መልካም እንዲሆንልኝ አብዝተው የተመኙልኝም የቢራ ማስታወቂያዎች ናቸው፡፡ ቢራ ስትጠጣ አዲሱ ዓመት የሰላም የጤና የብልፅግና ይሆንልሀል ዓይነት ፉገራ እየፎገሩኝ፡፡ ይህን ያህል ቢራ የሕይወታችን ገፅታ ሆኗል፡፡ ስለቢራ ላለመስማት ብር ብሎ ከመጥፋት ውጭ አማራጭ የለም በመዝናናታችን መኃል፣ በመንገዶቻችን ዳርቻ፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቻች ቢራ አለ፤ ቢራ መኖሩ አይደለም ችግሩ፣ ችግሩ ቢራ አብዝቶ መኖሩና እየተነገረበት ያለው መንገድ ነው፡፡ ቢራ የማኅበራዊ የሥነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይታችን ጋሬጣ ሊሆነ በሀገሪቱ ሰማይ ላይ አንዣቧል፡፡
ህፃናት አማራጭ በሌለው የቤት ውስጥ የቲቪ መዝናኛቸው ቢራ የደስታ የመልካም ጓደኝነት መሠረት መሆኑ ዘወትር እየተነገራቸው ነው፡፡ ሕፃናት ከቻሉ ተደብቀው ካልሆነ 18 ዓመት ሲሞላቸው የደስታ ምንጭ እንደሆነ አብዝቶ የተሰበከውን ቢራ ለመጠጣት ለማለም ተገደዋል፡፡ ህጻናት ከብራና እና ከቢሮ ይልቅ ቢራ ምን እንደሆነ በተሻለ ለማወቅ ተገደዋል፡፡ ወጣቶች በቢራ እንጂ በሌላ መንገድ መዝናናት የማይቻል እንኪመስል አብዝተው በቢራ ይዝናናሉ፡፡ አሽከርካሪዎች ቢራ ጠጥተው እልፎችን ከህይወት መስመር በማስወጣት ላይ ናቸው፡፡ በየቀኑ በመልካምነት፣ በእውቀት፣ በሥራ እና በእምነት ከሚጠቀመው ይልቅ በቢራ የሚጠመቁት በዝተዋል ሀገሪቱ በቢራ ጠመቃ ላይ ነች፡፡ ቢራ የሚጠምቁት፤ የሚያስጠምቁትና የሚያሳልፉት አሳላፊዎች ደግሞ በሀገሪቱ የአርዓያነት ምልክት ተብለው የሚወሰዱ ግለሰቦች እና ተቋማት ናቸው፡፡
የሀገሪቱ ሕግ ግልጽ ነው (የማስታወቂያ አዋጅ ቁጥር 759/2004) ህፃናት ባሉበት አካባቢ፤ በትምህርት ቤት፤ በህክምና
ጣቢያዎች፤ በቲያትር ቤቶች እና በስታዲያሞች 100 ሜትር ራዲየስ ውስጥ የአልኮል መጠጥ ማስተዋወቅ ክልክል ነው፡፡ የጎልማሳ ደሰታው እንቢ ማለት ነው እንጂ መጽሐፍ ከተማይቱ በራሱ በርካታ ሕጎች ላይ እንቢ ባይ ሆናለች፡፡ የከተማይቱ ስታዲየሞች ግማሽ ክፍል የተሸፈነው በቢራ ማስታወቂያ ቢል ቦርዶች ነው፡፡ ለአንድ ዓመትም ቢሆን ለመሰባሰባችን ለአንድነታችን እና የሀገር ፍቅር መግለጫችን የነበረው እግር ኳሳችን ሳይቀር ስፖንሰር የተደረገው በአልኮል መጠጥ ነው ጭራሽ በቅርቡ በቢራ የተሰየመ አውሮፕላን ስፖርተኞችን ይዞ ሲሼልስ ገብቷል፡፡ ከሰው ልጅ ምንጭነታችን ይልቅ፤ ከነጭ አሸናፊ ጀግንነታችን ይበልጥ፤ የራሳችን ማንነት ያለን ኩሩ ሕዝብ ከመሆናችን ልቆ ቢራ ከፊታችን ቀድሟል፡፡ ጠጭነት ETHIOPIAN ከሚለው የኩራት ስም ልቆ የጥንካሬ ምንጭ የሆነውን ስፖርት ስፖንሰር አድርጎ ሲሼልስ ገብቷል፡፡ ስፖርት ባለበት ቢራ አለ ምናልባትም ቢራ መጠጣት ስፖርተኛ የሚያደርግ እስኪመስል ቢራና ስፖርት ተቆራኝተዋል፡፡ ታዋቂ የምንናላቸው አዋቂዎቻችንን ስለ ቢራ አብዝተው ይሰብኩናል፡፡ በቴሌቭዥናችን ውስጥ ከአምስቱ ማስታወቂያዎች አንዱ የቢራ ማስታወቂያ ነው፡፡ የሆነ ቴሌቭዥኑ የጠላ መጥመቂያ ጋን እስኪመስል ድረስ ቢራ ቢራ ይሸታል፡፡ የከተማው ረዣዥም ህንፃዎች ግማሽ አካል በቢራ ማስታወቂያ ፖስተሮች የተሸፈነ ነው፡፡ አይዶሉ፤ ቲያትሩ፤ ፊልሙ፤ ሙዚቃው ቢራ ቢራ ይላሉ የቢራ መንፈስ ሀገሪቱ ሞልቷታል፡፡ እንግዲህ ቢራን የአልኮል መጠጦች ወኪል አድራጌው እንጂ ቢራ ስል የአልኮል መጠጥ ማለቴ ነው፡፡
ከፍ ሲል የገለፅኩት የማስታወቂያ አዋጅ የማህበረሰቡን እሴቶች የሚሸረሽሩ ማስታወቅያዎች እንዳይሰሩ፣ እንዳይተላለፉ መጠነኛ ጥረት ቢያደርግም ሕጉ እየተከበረ አይደልም ሕጉን ለማክበር ፍላጎትም እውቀትም የለም፡፡ አዋጁን ማስፈፀም ያለባቸው ተቋማት ስራቸው ዝምታ ሆኗል፡፡ አዋጁም ቢሆን ጠንካራ እና በእርግጥም አዋጁ የወጣበትን መሠረታዊ ዓላማ ለማሳካት በቂ አቅም ያለው አይደለም፡፡ ቢራ ጠጡ ግን በኃላፊነት የሚሉ ማስታወቂዎች ራሳቸው ኃላፊነት የጎደላቸው ናቸው፡፡ እጅግ በታወቁ ሰዎች ሳቅና ፌሽታ በነገሰበት ሁኔታ መሀል ቢራ እያንደቀደቀቁ ቢራን እያደነቁ ቢራን የደስታና የሳቅ ምንጭ አድርገው የሚያሳዩ አማላይ ማስታወቂያዎች ለህፃናት እያሳዩ በሀላፊነት ይጠጡ ማለት ህፃናትን ካለመረዳት ቢረዱም ለህፃናት ግድ አለመስጠት ነው፡፡ ህፃናትን ከቴሌቭዥን ከማራቅ ቢራን ከቴሌቭዥን ማራቅ ይበልጥ ሀላፊነት የተሰማው እርምጃ ነው፡፡ ቢራን በአደባባይ በማስተዋወቅ ከሚገኝ ትርፍ ይልቅ ቢራን በአደባባይ በማስተዋወቅና የቢራን የደስታ ምንጭነት በመስበካችን የሚከስረውን ትውልድ ማዳን ይበልጥ የተከበረ እውነተኛ ትርፍ ነው፡፡ በቴሌቭዥን ማስተዋወቅ አይችልም እንደተባለው ሲጋራ ከሲጋራ ይበልጥ ማህበራዊ ክስረት የሚያደርሰው የአልኮል መጠጥ በቴሌቭዥን እንዲተላለፍ መፍቀድ የለብንም ሕጉም ቢሆን የአልኮል ማስታወቂያዎች የሚያደርሱት ችግር የመቀነስ እንጂ የማስቀረት ብቃት ስለሌለው ሊሻሻል ይገባዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ መጠጥን በቁጥብነት እና በኃላፊነት የሚጠጡ ሰዎችን በፍጹም አይመለከትም፡፡