By Mulugeta Belay on Saturday, 21 November 2015
Category: Family Law Blog

የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ከሌሎች የቤተሰብ ሕጉ ድንጋጌዎች እና ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 ጋር ያለው ተቃርኖ

እናትነት እውነት አባትነት ግን እምነት ነው የሚለው አባባል ተደጋግሞ የሚሰማው አባትነትን ማረጋገጥ ፈታኝ የሆኑ ማህበራዊ ባይሎጂካዊና ሕጋዊ ውስብስብነት ያለው ፈታኝ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ አባት ለልጁ ግዴታዎችን  አሉበት፤ አባት ከልጁ የሚጠይቀው መብት አለው፡፡ ልጅ ለአባቱ የሚጠይቀው ግዴታዎች ያሉበትን ያህል ከአባቱም የሚጠይቀው መብት አለው፡፡ እኚህ በመሀላቸው መብትም ግዴታም ያስተሳሰራቸው ሁለት ሰዎች ታዲያ በርግጥም አባትና ልጅ ናቸው? የሚለው ጥያቄ ፈታኝ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ከባድ ስለመሆኑ አባትነትንና ልጅነትን ስለማወቅ በሕጉ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ለጥያቄው ምላሽ በሚሰጡበት አካሔድ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ጽሑፍም የሚያጠነጥነው ከጋብቻና እንደባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ግንኙነት ውጭ በአንድ አጋጣሚ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ምክንያት የተወለደን ልጅ በተመለከተ ሆኖ በእንደዚህ ዓይነት ግንኙነት የተወለደ ልጅ በርግጥ በሕግ አይን አባት አለው? ካለውስ ሕጉ በዚህ ረገድ ግልጽና ወጥ ነው? የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ በርግጥስ ፋይዳው ምንድን ነው? የሚሉ ጉዳዮችን ለውይይት መነሻ እንዲሆን ያህል ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

አባትነትን እና ልጅነትን ስለማረጋገጥ

በቤተሰብ ሕጉ አቀራረጽ መሠረት ልጆች በሦስት ይከፈላሉ፤ እነዚሁም በጋብቻ ውስጥ የተወለዱ፤ እንደ ባልና ሚስት አብረው ከሚኖሩ ሰዎች የተወለዱ ልጆች እና ከሌላ ዓይነት ማለትም ከመጀመሪያዎቹ ከሁለቱ ውጭ በሆነ  ሌላ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች ናቸው፡፡

የመጀመሪያዎቹ ሁለት ግንኙነቶች በሕግ ፊት ዕውቅና የተሰጣቸውና በሕጉም ተገቢውን ጥበቃ የሚደረግላቸው ሲሆን የመጨረሻው ዓይነት ሌላ ግንኙነት ግን በሕግ ፊት ውጤት  የማያስተካከል በዚህም ምክንያት በሕግ ጥበቃ የማይደረግለት ተራ ግንኙነት ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ሊዳሰስ የተፈለገው ተራ በሆነውና በሕግ ጥበቃ በማይደርግለት ሌላ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች የአባትነት ጥያቄ እንዴት ይመለሳል የሚለው ነጥብ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥም ሌላ ግንኙነት ማለት ከጋብቻ ወይም እንደ ባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ውጭ የሆነ ግንኙነት ሆኖ በወንድና በሴት መካከል የሚፈጠር ማናቸውም ግንኙነት ማለት ነው፡፡

አባትነትን ማረጋገጥ ፈታኝ ጉዳይ በመሆኑ ሕጉ አባትነትን ለማረጋገጥ ሦስት አማራጭ መንገዶችን አቅርቧል፡፡ የመጀመሪያው አባትነትን በሕግ ግምት ማወቅ ሲሆን ይኸውም በጋብቻ ወቅት የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ ወይም እንደ ባልና ሚስት አብረው በሚኖሩ ሰዎች ግንኙነት ውስጥ የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ አባት እናትየዋ ጋር በዚሁ ግንኙነት ውስጥ ያለው ባል ወይም ሰው ነው የሚለው የሕግ ግምት ሲሆን ሁለተኛው መንገድ  ደግሞ ልጁን ልጄ ነው ብሎ ሊቀበል የሚችል ሰው መኖር ሲሆን ሦስተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ደግሞ በሕጉ ተለይተው በተቀመጡ ውስን ምክንያቶች ብቻ ፍርድ ቤቶች በሚሰጡት ፍርድ አባትነት ሊታወቅ መቻሉ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ልጅነት የልጅነት የምስክር ወረቀት በማቅረብ፤ የልጅነት ሁኔታ መኖሩን ማለትም በማህበረሰቡ ዘንድ የሰውየው ልጅ ነው ተብሎ የሚገመት መሆኑን በማስረዳት ወይም ፍርድ ቤት በቂ ምክንያት አግኝቶ የሚፈቀድለት ከሆነ ምስክሮችን ወይም ሌላ ዓይነት ማስረጃዎችን በማቅረብ ልጅነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

በጽሑፍ መግቢያ ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለምን? እንዴት? የሚሉ የውይይት መነሻዎችን መጫር ነው በመሆኑም ጸሐፊው የሚከተሉትን ጥያቄዎች እያስላስላችሁ ጽሑፉን እንድታነቡ ይጋብዛል ፡፡

አባትነትን ማወቅ ወይም ልጅነት የማረጋገጥ የመጨረሻ ውጤቱ ምንድ ነው? የአባትነትና የልጅነት ግንኙነት መኖሩን ማረጋገጥ ወይስ ሌላ? ውጤቱ የአባትነትና የልጅነት ግንኙነት መኖሩን ማረጋገጥ ከሆነ አንድን ግንኙነት ማለትም የአባትና የልጅ ግንኙነት መኖሩን ለማረጋገጥ ሁለት የተለያዩ መመዘኛዎችን ያስቀመጡ ሁለት የተለያዩ መንገዶችን ማስቀመጥ  ፋይዳው ምንድን ነው ?

በዚህ ጸሐፊ እምነት ከፍ ሲል እንደተገለጸው አባትነትን ለማረጋገጥ የተቀመጡ መመዘኛዎች ልጅነትን ለማረጋገጥ ከተቀመጡ መመዘኛዎች በእጅጉ የተለያዩ ናቸው፤ በመሆኑም አንድን ግንኙነት በሁለት የተለያዩ መንገዶች ማረጋግጥ ስለሚቻል በአባትነት ማረጋገጫ ስልቶች አባቱን ማወቅ ያልቻለ ሰው ልጅነት በማወቂያ ስልቶች አባቱን ወደ ማወቅ ይመጣል፡፡ በውጤት ደረጃ አባትነት ማወቅና ልጅነትን ማረጋገጥ የተለያዩ ናቸው ካልተባለ በስተቀር ሁለቱም ውጤታቸው በሰውየውና በልጁ መካከል የአባት እና የልጅ ግንኙነትን መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ የቤተሰብ ሕጉ በዚህ ረገድ አባትነት የማወቅ ውጤት እንዲሁም ልጅነትን የማረጋገጥ ውጤት ምን እንደሆነ በግልፅ ባለማስቀመጡ ሁለት የተለያዩ መመዘኛዎችን ያስቀመጡ ነገር ግን ተመሳሳይ የሆነ ግንኙነትን የሚያረጋግጡ ድንጋጌዎችን መያዙ አባትነትን ማወቅ እና ልጅነት የማረጋገጥ ክሶች የመጨረሻ ውጤት አንድ ነው ወደሚል ድምዳሜ ላይ እንድንደረስ ያስገድደናል፡፡ ይህም በክስ አቀራረብና በፍርድ አሠጣጥ እረገድ ልዩነት እንዲኖር በክሱ አቀራረብና አካሔድ ምክንያት ተመሳሳይ የሆኑ ፍሬ ነገሮች በተለያየ ማስረጃ እነዲረጋግጡ በዚህ ምክንያትም የተለያየ ብያኔ እንዲያገኙ የሚድረግ ውጤት ያለው ሲሆን ሰዎችም በቀላሉ ግንኙነቱን ወደሚያስረዳላቸው የግንኙነቱ ማወቂያ መንገድ እንዲያማትሩ የማድረግ ውጤት አለው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ይበልጥ ሊብራራ የተፈለገው ሁሉም ዓይነት ልጆች አባታቸውን አንዴት ያውቃሉ? የሚለው ጥያቄ ሳይሆን ከጋብቻ ውጭ ወይም አንደ ባልና ሚስት አብረው በማይኖሩ ሰዎች ግንኙነት መሀል የተወለደ ለምሳሌ በሴትና ወንድ የጓደኝነት ጊዜ ወይም በአንድ ለሊት የፍቅር ግንኙነት የተወለዱ ልጆች አባት አላቸውን? የሚለው ጥያቄ ነው ይህ ጥያቄም በሚቀጥለው አርዕስት ሥር እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡

አባትን ፍለጋ

የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ በአንድ ሴት እና ወንድ የጓደኝነት ጊዜ ወይም በተወሰኑ አጋጣሚዎች በነበረ የፍቅር ግንኙነት ምክንያት የተወለዱ ልጆች ከእናታቸው በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር ማናቸውም ዓይነት ሕጋዊ ግንኙነት አይኖራቸው ሲል በግልፅ ደንግጎ ይገኛል፡፡

ከሌላ ሰው ጋር ምንም ዓይነት ሕጋዊ ግንኙነት የላቸውም የሚለው አባባል በዚህ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች አደገውም ከሌሎች ጋር እንደ ውል መዋዋልና መወረስ ቀለብ መቁረጥ እና ቀለብ ማግኝነት የመሳሰሉ ሕጋዊ ግንኙነትን መፈጠር አይችሉም እስከሚል ድርስ እንዲተረጉም በር የሚከፍት የቃላት አጠቃቀም ቢሆንም ድንጋጌው ሊገልፀው ከፍለገው ሀሳብ ጋር የማይስማማ የቃላት አጠቃቀም በመያዙ፤ ድንጋጌው በቤተሰብ ሕግ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ እና ድንጋጌው ቤተሰብ በመመሥረት ሂደት ስላሉ ግንኙነት በሚያትተው የሕጉ ክፍል ስለሚገኝ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው ማናቸው ዓይነት ሕጋዊ ግንኙነት ተብሎ በአንቀጽ የተገለፀው ግንኙነት  ማነቸውም ዓይነት የሕግ ግንኙነት ማለት ሳይሆን ከአባትነት እና ከልጅነት ግንኙነት አኳያ ያለን ግንኙነት የሚመለከት ብቻ ነው ብለን መተርጎሙ ይበልጥ አሳማኝ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ አጥብበን ብንተረጉመውም ከሌላ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች ከሌላ ሰዎች ጋር ለምሳሌ አባታቸው ሊሆን ከሚችል ሰው ጭምር ሕጋዊ ግንኙነት የላቸውም ከተባለም እነዚህ ልጆች አባታቸውን ማወቅ፣ ልጅነታቸውን ማረጋገጥ የሚባሉ ሕጋዊ ግንኙነቶች መፍጠር በነዚህ ግንኙነቶችም የሚገኙ መብቶችን እና ግዴታዎችን ማቋቋም አይችሉም ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል፡፡

በቤተሰብ ሕጉ አባትናትንና ልጅነትን ማረጋገጫ ስልቶች በልጆች መካከል ያለምንም ልዩነት ከተቀመጡ በኋላ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ስለጉድፈቻ ወይም ልጅነትን ስለመቀበል የተወሰኑ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ከእንደዚህ ያለ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች ከእናታቸው ጋር ካልሆነ በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር ማናቸውም አይነት ግንኙነት አይኖራቸውም ተብሎ መደንገጉ በልጁ ላይ የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት ምንድን ነው?

እስኪ ከፍ ሲል የገለፅኩትን ጥያቄ በአንድ የሕግ ፈተና ውስጥ ተቀምጣችሁ እንደ ቀረበላችሁ የምርጫ ጥያቄ ቁጠሩትና ከሚከተሉት ሁለት ምርጫዎች ትክክለኛው ወይም የተሻለው ምላሽ የቱ ነው?

ሀ/ ከሌላ ግንኙነት የተወለደ ልጅ አባት የለውም አባት ስለማይኖረውም የአባትና የልጅ ግንኙነት የሚያስከትለው መብትና ግዴታ አይኖርም (ለምሳሌ. መውረስ፤ ቀለብ መስጠትና መቀበል)

ማብራሪያ ‹በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/1/ ላይ በግልፅ እንደሰፈረው ልጁ የተወለደው በሕግ ፊት ውጤት በሌለው ግንኙነት በመሆኑና ከዚህ በሕግ ፊት እውቅና ባልተሰጠው ግንኙነት የተወለደ ልጅ ደግሞ ከእናቱ በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር ማናቸውም ዓይነት ሕጋዊ ግንኙነት ሊኖረው እንደማይችል በንዑስ ቁጥር 2 ላይ በግልፅ የተደነገገ በመሆኑ ይህ አንቀፅም በቤተሰብ ሕጉ ስለጉዲፈቻ ልጅ ወይም ልጅን ስለመቀበል የተወሰኑት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በማለት ሌሎች የቤተሰብ ድንጋጌዎች ማለትም ልጁ ጉዲፈቻ አድርጎ የሚቀበለው አባት ካላገኘ ወይም አባትነትን ማወቂያ መንገድ በሆነው ልጅነትን ስለመቀበል በተቀመጡት ድንጋጌዎች መሠረት ልጄነህ ብሎ የሚቀበለው ሰው ካላገኘ በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር ማናቸውም ዓይነት ሕጋዊ ግንኙነት እንዳይኖረው ስላደረገው ልጁ ፈፅሞ አባት ሊኖረው አይችልም፡፡

በመሆኑም የዝርዝር አንቀፆች መርህ በሆነው በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ መሠረት ስለጉድፈቻና ልጅነትን ስለመቀበል የተወሰኑ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በሚለው የሕጉ አገላለፅ ምክንያት አባትነትንና ልጅነትን ስለማረጋገጥ የተደነገጉ ሌሎች ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ስለማይሆኑ የልጁ ምርጫ ጉዲፈቻ አባት ማግኘትና ልጅነህ ብሎ የሚቀበለው ሰው ማግኝት ወይም አባት አልባ ልጅ ሆኖ መኖር ነው፡፡

ለ/ ከሌላ ግንኙነት የተወለደ ልጅ አባት በአባትነት ማወቂያ ወይም በልጅነት ማረጋገጫ መንገዶች ሊታወቅ ይችላል፡፡

ማብራሪያ፡- በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 ላይ በግልፅ እንደሰፈረው ማንኛውም ህፃን ወላጆቹን የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት መብት ያለው ሲሆን ከጋብቻ ውጭ በተወለዱ ልጆች እና በጋብቻ በተወለዱ ልጆች መካከል ልዩነት ማድረግ እንደማይቻል እነዚህ ልጆችም እኩል መብት ያላቸው ስለመሆኑ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ከሌላ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች ከእናታቸው በስተቀር ከሌሎች ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ሕጋዊ ግንኙነት የላቸውም በማለት መደንገጉ ከፍ ሲል በሕገ መንግሥቱ በልጆች መካከል ልዩነት አይደረግም ህፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅ መብት አላቸው ከሚለው ድንጋጌ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ሕገ መንግሥታዊ ባለመሆኑ ተፈፃሚ ሊሆን አይችልም፡፡

በሌላ በኩል አባትነትን ስለማወቅና ልጅነትን ስለማረጋገጥ በቤተሰብ ሕጉ ከአንቀጽ 123 እስከ 162 በተደነገጉት ድንጋጌዎች መሰረት ከሌላ ግንኙነት የተወለደ ልጅ  የልጅነት ሁኔታ መኖሩን በማስረዳት በምስክር ወይም በሌላ ማስረጃ ልጅነትን በማረጋገጥ እንዲሁም ደግሞ የአባትነት ማወቂያ መንገድ ከሆኑት አንዱ በሆነው በፍርድ ቤት ውሳኔ አባትነቱ እንዲታወቅለት በማድረግ አባት ማግኝት ይችላል፡፡ በነዚህ ድንጋጌዎች ላይ በጥቅሉ አባትነትን ስለማወቅና ልጅነትን ስለማረጋገጥ  ከመቀመጡ ውጭ በልጆች መሀከል ልዩነት ባለመደረጉ የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ የልጁን አባት ማግኝት አስመልክቶ ተፈፃሚነት የለውም፡፡

ብይን

እንግዲህ ከፍ ሲል በቀረቡት ምርጫዎች ትንታኔ መሠረት እንዲሁም በሁለቱ ምርጫዎች ላይ አንባቢዎቼ ባላችሁው የግል ግንዛቤ መሠረት የተሻለው ምላሽ የትኛው ነው?  ሀ ወይስ ለ? አንዳንዶች መልስ የለም የሚል ምርጫ እንደጠበቃችሁ እገምታለሁ፡፡ ትክክለኛው ምላሽ “ሀ” ም ይሁን “ለ” ወይም ምላሽ ያልተቀመጠ ይሁንም አይሁንም ርዕስ ጉዳዩ የዳሰሳቸው የቤተሰብ ሕጉ ድንጋጌዎች ግን ግልፅ ያልሆኑ፣ እርስበርስ የተቃረነ የመምሰል እና የፋይዳ እና የአስፈላጊነት ጥያቄ  መነሳቱ ግን አይቀርም፡፡

የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ድንጋጌ ፍይዳ ምንድ ነው? ልጆቹ በርግጥም እንደ አንቀፁ አነጋገር ከናታቸው በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር ሕጋዊ ግንኙነት የላቸው? ሕጋዊ ግንኙነት የላቸውም ማለት ምን ማለት ነው? አንቀፁ አባትነትን እና ልጅነትን ስለማወቅ በሚደነግጉት የሕጉ ክፍል ላይ ያለው ውጤት ምንድን ነው ? በጉዳዩ ላይ ተፈፃሚው ድንጋጌ የትኛው ነው  ነው? ከሌላ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች ከናታቸወ በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር ማናቸው አይነት ግንኙነት የላቸውም ተብሎ በዚህ ምድር ከናታቸው ጋር ካላቸው ግንኙነት በስተቀር ልጅነታቸውን በሁኔታ ማስረዳት ከቻሉ ወይም በምስክርና በሌሎች ማስረጃዎች ማረጋገጥ ከቻሉ ወይም በፍርድ አባትነት እንዲታወቅላቸው ማድረግ ከቻሉ በአንቀጽ 107/2/ ማናቸው አይነት ሕጋዊ ግንኙነት አይኖራቸውም መባሉ ለምን አስፈላገ? ይህን መባሉ በልጅ ሕጋዊ ግንኙነት ላይ ያለው አሉታዊ ተፅእኖ ምንድ ነው? በርግጥም ሕግ አውጭው በአንቀጽ 107/2/ ሊያሳካው የፈለገው ግብ ምንድ ነው? ከጋብቻና እንደባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ውጭ ያሉ ሌሎች ግንኙነቶች እንዳይለመዱ መከላከል ወይስ ሌላ? ሌሎች ግንኙነቶች እንዳይለመዱ መከላከል ከሆነ ልጅነት በሁኔታና በምስክር እዲረጋገጥ አባትነትም በፍርድ እንዲታወቅ መልሶ መፍቀድ ለምን አስፈለገ? ነው ወይስ ከሌላ ግንኙነት የተወለዱ ልጆች በርግጥን ከናታቸው ውጭ ምንም አይነት ሕጋዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው አልተፈለገም የሕግ አውጭው ፍላጎት ይህ ከሆነ ደግሞ ሀገራችን በርካታ አባት አልባ ህፃናቶች አሏት ማለት ነው?

 

ስለዚህም በሌላ ግንኙነት የተወለደ ልጆች በግንኙነቱ ተዋናዬች ማለትም በእናታቸውና በግንኙነቱ ውስጥ በነበር ሰው ምክንያት ወንጀል እየተፈፀመባቸው ነው ማለት ይቻላል ?ለምሳሌ ህፃናቱ አባታቸውን የማወቅ፣ የቤተሰብ ስም የማግኘት፣ ባዬሎጂካል በሆኑ ወላጆች የማደግ፤ ሊወረሱት የሚችሉት አባት የማግኘት መብታቸውን የመጣስ ወንጀል? ለማንኛውም ጥያቄዎቹ የጸሐፊውን አቋም አያንፀባርቁም ይልቁንስ ጥያቀዎቹ የቤተሰብ ሕጉን አንቀፅ 107(2)ን ይሞግታሉ ነገርግን የጸሐፊውን አቋም አንድ ነው፡፡ ይህውም የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ግለፅ በሆነና ውጤቱ በታወቀው መንገድ ሊሻሻል ይገባል፡፡

Related Posts

Leave Comments