- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 3962
የኮ/መ/ቁ 179485 - ወ/ሪት እቴነሽ ፀጋዬ ወልዴ እና አቶ ሳሙኤል መንግስቴ
መ/ቁ 179485
ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- ወ/ሪት እቴነሽ ፀጋዬ ወልዴ ፡- ቀረቡ
ተከሳሽ፡- አቶ ሳሙኤል መንግስቴ ጠበቃ ራሄል ነቃጥበብ ቀረቡ
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
በዚህ መዝገብ በግራ ቀኙ መካከል የነበረዉን ክርክር ፍርድ ቤቱ ተመልክቶ የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ዉሳኔ የሰጠ ቢሆንም ተከሳሽ በሌለሁበት የተሰጠዉ ዉሳኔ ተነስቶ ክርክሩ በድጋሚ ይሰማ በማለት መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ በቃለ መሕላ የተደገፈ አቤቱታ አቅርበዉ ያቀረቡት አቤቱታ ላይም ከሳሽ አስተያዬት እንዲሰጡ ተደርጎ ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በሌለሁበት የተሰጠዉ ዉሳኔ ይነሳልኝ በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ለተከሳሽ በህጉ አግባብ ያልደረሳቸዉ መሆኑን ስለተገነዘበ ቀደም ሲል በዚህ መዝገብ የተሰጠዉ ዉሳኔ እንዲነሳ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ በወኪላቸዉ አማካኝነት ጥር 5 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የብድር ውል ብር 150,000.00(አንድ መቶ ሃመሳ ሺህ) የተበደሩ መሆኑን ተከሳሽ ለዚህ ለተበደሩት ገንዘብ አከፋፈል ዋስትና ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09/10 የብሎክ ቁጥር B6 የቤት ቁጥር B6/25 የካርታ ቁጥሩ 007/10199/00/10232 የሆነ ኮንዶሚኒዬም ቤት ያስያዙ መሆኑን ተከሳሽ ከከሳሽ በብድር የወሰዱትንም የገንዘብ መጠን በ6 ወር ዉስጥ ማለትም እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ/ም ለመከፈል ግዴታ የገቡ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ በብድር ዉሉ ላይ በተቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ዉስጥ የተበደሩትን ገንዘብ ያልከፈሉ መሆኑን ለመከፈልም ፈቃደኛ አለመሆናቸዉን ገልጸዉ ተከሳሽ በብድር የወሰዱትን ብር 150,000.00(አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ) ከሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታስብ ህጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍሏቸዉ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ተከሳሽ የቀረበባቸዉን ክስ እንዲከላከሉ እንዲፈቀድላቸዉ የመከላከያ ማስፈቀጃ አቅርበዉ ፍርድ ቤቱም በከሳሽ የቀረበባቸዉን ክስ እንዲከላከሉ ፈቅዶላቸዉ ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ/ም የተጻፈ የመከላከያ መልስ አቅርቧል፤ባቀረቡት መከላከያ መልስም ከሳሽ በማስረጃነት ባቀረቡት የብድር ውል በራሳቸዉም ሆነ በወኪላቸዉ አማካኝነት ያልተዋዋሉ መሆኑን ገንዘብ ተበዳሪም ሆነ ተዋዋይ አለመሆናቸዉን በብድር ዉሉ ላይ የተጠቀሰዉንም ገንዘብ ተበድረዉ ያልወሰዱ መሆኑን በማስረጃነት የቀረበዉ የውክልና ስልጣን ማስረጃም በእራሳቸዉ ያልተሰጠ መሆኑን በብድር ዉሉ ላይ ወ/ሮ ነጻነት መንግስቱ የወ/ሮ ላቀች ተክሉ ህጋዊ ወኪል የሚል መሆኑን ብድሩን የተበደሩት እርሳቸዉን ወክለዉ የተበደሩ ስለመሆናቸዉ የሚያመልክተዉ ነገር የሌለ መሆኑን በዉሉ ላይ ወ/ሮ ነጻነተ መንግሰቱ ብድሩን የተበደሩት ለስራ ማስኬጃ እንደሆነ የብድር ውሉ የሚያመለክት ስለሆነ በብድር ዉሉ ላይ ለተገለጸዉ የገንዘብ መጠን ወ/ሮ ነጻነት መንግስቱ በግላቸዉ ከሚጠየቁ በቀር ኃላፊ የሚሆኑበት የህግ አግባብ የሌለ መሆኑን ገልጸዉ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት የመከላከያ መልሳቸዉን አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ወ/ሮ ላቀች ተክሌ ለወ/ሪት ነጻት ውክልና የሰጡት አንድ ተከሳሽ ሆነዉ እንዲሰሩ መሆኑን ወ/ሮ ላቀች ከተከሳሽ የተሰጠ የውክልና ስልጣን ያላቸዉ መሆኑን ተከሳሽ ለወ/ሮ ላቀች በሰጡት ውክልና ወ/ሮ ላቀች ሌላ ሰዉ እንዲወክሉ ስልጣን የሰጧቸዉ መሆኑን ወ/ሮ ነጻነትም በወ/ሮ ላቀች በተሰጣቸዉ ውክልና መሰረት ተከሳሽን ወክለዉ በብድር ውሉ ላይ የተጠቀሰዉን ገንዘብ የተበደሩ መሆኑን በመግልጽ ሲከራከሩ ተከሳሽ በበኩላቸዉ ባቀረቡት ክርክር ወ/ሮ ነጻነት ብድሩን የተበደሩት ወ/ሮ ላቀችን ወክለዉ መሆኑን በብድር ውሉ ላይም ስማቸዉ ያልተጠቀሰ መሆኑን ገንዘቡን ያልተበደሩ መሆኑን በብድር ውሉ ላይ ተዋዋይ ወገን አለመሆናቸዉን ገልጸዉ ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡
የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በብድር ውሉ ላይ የተጠቀሰዉን የገንዘብ መጠን ለከሳሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተወሉ መርምሮታል፡፡
እንደመረመረዉም ውሎች ዉጤት ያላቸዉ በተዋዋሏቸዉ ወገኖች መካካል መሆኑን የፍ/ሕ/ቁ 1952(1) ስር ተደነግጓል፡፡ ይሁን እንጂ ሰዎች ህጋዊ ዉጤት ያላቸዉን ትግባራት እራሳቸዉ በቅጥታ ሊያከናዉኗቸዉ ግድ አይደለም ይልቁንም በወኪሎቻቸዉ አማካኝነት ሊያከናውኑ እንደሚችሉ ከፍ/ሕ/ቁ 2179 ጀምሮ ካሉት ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡
የሌላ ሰዉ ወኪል በመሆን ስራዎችን የመፈጸም ስልጣን ከህግ ወይም ከውል ሊመነጭ እንደሚችል የፍ/ሕ/ቁ 2179 ይደነግጋል፡፡ ውክልና ማለት ተወካይ የተባለ አንድ ሰዉ ወካይ ለተባለዉ እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ህጋዊ ስራዎች በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባባት ውል መሆኑን ውክላናም በግልጽ ወይም በዝምታ ሊሰጥ የሚችል መሆኑን ፤ተወካዩ የተሰጠዉ የውክልና ስልጣን የሚፈቀድ ከሆነ ተወካዩ በራሱ ምትክ ሌላ ሰዉ ስራዉን እንዲሰራ መተካት የሚችል መሆኑን (delegation of authority) በዚህ መልኩ በምትክ ወኪል የተሰራ ስራም ወካዩን ሊያስገድድ የሚችል መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ 2199፤2200፤2215 እና 2217 መራዳት ይቻላል፡፡
ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ሰንመለስ ተከሳሽ የሚከራከሩት በብድር ዉሉ ላይ ስሜ አልተጠቀስም በማስረጃነት የቀረበዉን ውክልና እኔ አልሰጠሁም ወ/ሮ ነጻነት መንግስቱ ብድሩን የወሰደቺዉ ለስራ ማስኬጃ ስለሆነ ኃላፊነት የለብኝም ወ/ሮ ነጻነተ መንግስቱ የወ/ሮ ላቀች ህጋዊ ወኪል ናቸዉ እንጂ የተከሳሽ ወኪል አይደሉም በማለት ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ተከሳሽ ለወ/ሮ ላቀች የሰጡት ውክልና የሌለ መሆኑን በመግለጽ ያቀረቡት ክርክር የለም ይልቁንም ወ/ሮ ላቀች ተክሌ ከተከሳሽ በቁጥር 20001/10/2000 በቀን 26/5/2000 ዓ/ም የተሰጣቸዉ የውክልና ስልጣን ያላቸዉ መሆኑን የቀረበዉ ማስረጃ ያስረዳል፤ለክርክሩ መነሻ ከሆነዉ የብድር ውል ለመመልከት እንደሚቻለዉ ወ/ሮ ነጻነት መንግስቱ በብድር ዉሉ ላይ የተጠቀሰዉን ገንዘብ የተበደሩት ከወ/ሮ ላቀች ተክሉ በቁጥር ቅ8/15969/1/08 በቀን 9/6/08 ዓ/ም የተሰጣቸዉን ውክላና መሰረት በማድረግ ነዉ በዚህ ውክልናም ወ/ሮ ነጻነት መንግስቴ እንድ አቶ ሳሙኤል መንግሰቱ ሆነዉ ከግለሰብ ብድር እንዲበደሩ የተከሳሽ ወኪል ከሆኑት ከወ/ሮ ላቀች ተክሉ የውክልና ስልጣን ተሰጥቷቸዋል ወ/ሮ ላቀች ተክሉ በተከሳሽ በተሰጣቸዉ የውክልና ስልጣን ተተኪ ወኪል እንዳይውክሉ የተከለከሉ መሆኑን በመግለጽ በተከሳሽ በኩል የቀረበ ክርክር የለም ይህ ከሆነ ደግሞ በፍ/ሕ/ቁ 2217(1) ስር በግልጽ እንደተደነገገዉ ወ/ሮ ነጻነት መንግሰቱ የተከሳሽ ወኪል በሆኑት በወ/ሮ ላቀች ትክሉ በተሰጣቸዉ የውክልና ስልጣን የብድሩን ዉሉን የፈጸሙ መሆኑን መረዳት የሚቻል በመሆኑ ተከሳሽ በብደር ዉሉ ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ በብድር ዉሉ ላይ የተገለጸዉን ብር 150,000.00( አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ) ለከሳሽ የመከፈል ሃላፊነት አለበቸዉ በማለት ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ዉሳኔ
- ተከሳሽ ብር 150,000.00(አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ) ገንዘቡ መከፈል ከነበረበት ከሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ/ም ጀምሮ ከሚታስብ 9% ወልድ ጋር ለተካሳሽ ይክፈሉ፡፡
- ወጪና ኪሳራ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 4,100፤ለቴምብር ቀረጥ ብር 15 እንዲሁም ለልዩ ልዩ ወጪዎች በቁርጥ ብር 6,000 ተከሳሽ ለከሳሽ ይክፈሉ፡፡
ትዕዛዝ
ይግባኝ ለጠየቀ ግልባጭ ይሰጥ፡፡
መዝገቡ ተዝግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡