Font size: +
4 minutes reading time (858 words)

የኮቪድ 19 ወረርሸኝና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ

በዓለማችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን እየተስፋፋ በመምጣቱ ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ እሲያ ከአውስትራሊያ እስከ ደቡብ አሜሪካ መንግስታት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች አነስተኞቹን ጨምሮ እንቅስቃሴያቸው እየተናጋ፤ ህልውናቸው ፈተና ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ይህ ወረርሽን ማብቂያው እና መወገጃው በግልጽ ያልታወቀ እና ሊተነበይም ያልቻለ በመሆኑ በተለይም የግል የንግድ ድርጅቶች ቀጥረው የሚያሰሯቸው ሠራተኞች ላይ ሊወስዱ ስለሚችሉት እርምጃ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም የቫይረሱ መግባት ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ መንግስት ትምህርት ቤቶችን  እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ በመቀጠልም ፍርድ ቤቶች በከፊል እንዲሁም የመንግስት ተቋማት በፈረቃ የሚሰሩበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ በሌሎች የንግድ ድርጅቶች ላይ በመንግስት ደረጃ የተሰጠ ትዕዛዝ ባይኖርም የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙ እንዲሁም ግለሰቦች በተቻላቸው አቅም ከቤት እንዳይወጡ እየተመከረ በመሆኑ ሥራ በአግባቡ እየተሰራ እና ድርጅቶች በፊት ያገኙ የነበረውን ገቢ እያስቀጠሉ ነው ለማለት አዳጋች ነው፡፡

በመሆኑም የግል የንግድ ተቋማት በተለይ በእንደዚህ አይነት አስገዳጅ የሆነ ሥራን ማሰራት፣ ገቢንም መሰብሰብ በማይቻልበት ወቅት ምን አይነት ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ? በሕጉ ላይ የተቀመጡ አማራጮች ምንድን ናቸው? አማራጮቹን ለመጠቀምስ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችስ ምን ምን ናቸው? የሚሉትን ነጥቦች ከአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 (አዋጁ) ድንጋጌዎች አንጻር በመቃኘት አሠሪዎች በሠራተኞቻቸው ላይ አላስፈላጊ እርምጃ እንዳይወስዱ፤ ሠራተኞችም የሥራ ዋስትናቸው እስከምን ድረስ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበው የራሳቸውን መብት እንዲያስከብሩ እና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማሰብ ይህን ጽሑፍ ተዘጋጅቷል፡፡

 

ከአቅም በላይ የሆኑ ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች እንዲታገዱ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎች፡-

ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች ማገድ ማለት ሠራተኛው ሥራ እንዳይሰራ የሚያደርግ፤ አሠሪውም ደመወዝ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ሊከፍል የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ሊተገበር የሚችል ሁኔታ ነው፡፡

የማገድ ምክንያቶች በሚል በአዋጁ አንቀጽ 18 ላይ የተለያዩ ምክንያቶች የተጠቀሱ ሲሆን አሁን ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ከሆነው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ሊያያዝ የሚችለው ምክንያት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ተጠቅሶ የሚገኘውና እንደሚከተለው የሚነበበው ነው፡፡

“ከ10 ተከታታይ ቀናት ላላነሰ ጊዜ የድርጅቱን ሥራ በሙሉም ሆነ በከፊል የሚያቋርጥ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት”

በዚህ አንቀጽ የተጠቀሰው ድንጋጌ በአሁን ሰዓት በዓለማችን ላይ የተከሰተውና የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ያስቆመ ከአቅም በላይ የሆነ (ቀድመው ሊተነብዩት ያልተቻለ፣ ወደፊትም ማብቂያው እና መቆጣጠሪያው ምን እና መቼ እንደሆነ ያልታወቀ) የኮሮና ወረርሽኝ ክስተትን ይመለከታል፡፡ ይህ ወረርሽን ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሥራቸውን እንዲያቆሙ አድርጓል፡፡ የተለያዩ የንግድ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው የንግድ እንቅስቃሴያቸውን እያደረጉ ነው ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ የለም፡፡ በግልጽ በሀገራችን እንደምናየውም የመንግስት ድርጅቶች እንዲሁም ወሳኝ የፍትህ አካላት ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በከፊል ተዘግተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ በረራዎችን አቁሟል፡፡ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ የወንድና የሴት የውበት ሳሎኖች፣ የቡና ጠጡ በረንዳዎች፣ ልብስ መሸጫ ቤቶች፣ ሲኒማ እና ቴአትር ቤቶች ወዘተ ሥራ አቁመው በሮቻቸውን ከዘጉ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ 

በእንደዚህ አይነት የንግድ ተቋማትን ህልውና በሚፈታተን አስቸጋሪ እና የንግድ ተቋማት ለሠራተኞቻቸው ሊከፍሉ የሚችሉት ገቢ መሰብሰብ በማይችሉበት ሁኔታ በአዋጁ አንቀጽ 17 ላይ የተጠቀሰውን ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎችን ለማገድ ቢፈልጉ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አንድ አሠሪ ከ10 ተከታታይ ቀናት በላይ ሥራውን በሙሉም ሆነ በከፊል እንዲያቋርጥ የሚያስገድድ ከአቅም በላይ የሆነ ክስተት ሲፈጠር ይህንኑ ምክንያት በደብዳቤ ጽፎ ችግሩ በተፈጠረ በ3 ቀናት ውስጥ ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም ሌላ አግባብ ላለው ባለስልጣን ማስታወቅ እንዳለበት አንቀጽ 19 ይደነግጋል፡፡

ይህ የአሠሪው ግዴታ ከአንቀጹ ንባብ እንደምንረዳው ማስታወቅን እንጂ ማስፈቀድን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ሆኖም ከስር በአንቀጽ 20 የተጠቀሰውን ድንጋጌ ስንመለከት ማስታወቂያ የገባለት ሚኒስቴር ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ማስታወቂያው በገባለት በ3 ቀናት ውስጥ ለዕገዳው በቂ ምክንያት መኖሩን ይወስናል፡፡ ውሳኔውን በ3 ቀናት ውስጥ ካላሳወቀ ዕገዳውን እንደተቀበለው እንደሚቆጠር ጨምሮ አስፍሯል፡፡

 ስለዚህ አንድ አሠሪ ሥራውን በሙሉ ወይም በከፊል ሊያስቆም የሚችል ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲገጥመው ያለ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም ሌላ አግባብ ያለው ባለስልጣን ፍቃድ ሠራተኞች ለጊዜው ማገድ አይችልም የሚል አንድምታ ያለው የሕግ ትርጉም እንዳለን ከላይ ከተጠቀሱት አንቀጾች መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ዕገዳው እንዲደረግ ፍቃድ የመስጠት ወይም የመከልከል (የዕገዳው ምክንያት በቂ መሆን አለመሆኑን የመወሰን) ስልጣን ብቻ ሳይሆን የዕገዳውን ጊዜ የመገደብ መብት እንዳለው በአዋጁ አንቀጽ 21 ያስቀምጣል፡፡

ዕገዳ ለምን ያህል ጊዜ ሊቆይ ይችላል?

አሠሪ ከሥራ ውል የሚመነጩ መብት እና ግዴታዎችን አግዶ ለማቆየት የሚችልበት ሁኔታ ከ3 ወር በላይ ሊቆይ እንደማይችል በአዋጁ አንቀጽ 21 ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ይህንን የጊዜ ገደብም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወይም ሌላ ስልጣን ያለው አካል ዕገዳውን ሲፈቅድ አብሮ የሚያስቀምጥ ይሆናል፡፡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወይም ሌላ ስልጣን ያለው አካል ዕገዳውን የመፍቀድ እና ጊዜውን የመገደብ ስልጣን ብቻ አልተሰጠውም፡፡ አሠሪው የተፈቀደለት የዕገዳ ጊዜ ተጠናቆ ነገር ግን ሥራውን መልሶ ለመጀመር ባልቻለበት ሁኔታ ከላይ ከተጠቀሱት የመንግስት አካላት ፍቃድ ውጪ ሠራተኞቹን ማሰናበት አይችልም፡፡

ስለዚህ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን ካመነበት ብቻ ጊዜያዊ ዕገዳው ወደ ዘላቂ ስንብት እንዲቀየር ሆኖ አሠሪው ለሚያሰናብታቸው ሠራተኞች የስራ ስንብት እና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ሊከፍል እንደሚገባ የአዋጁ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 2 ይደነግጋል፡፡

በተቃራኒው አሠሪው የስራ ሁኔታውን መልሶ ማስቀጠል በሚችልበት ጊዜ የዕገዳው ጊዜ እንዳበቃ ሠራተኛው በቀጣዩ ቀን ወደ መደበኛ ሥራው ይመለሳል፡፡ ታግዶ የቆየው መብት እና ግዴታም መተግበር ይጀምራል፡፡

ማጠቃለያ

የኮሮና ወረርሽኝ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቀነሱ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ የንግድ ተቋማትም መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴያቸውን ወደው ሳይሆን ተገደው ከአቅማቸው በላይ በሆነ ምክንያት ካቋረጡ ሠራተኞችን ይዞ ደመወዝ፣ የቤት ኪራይ እና መሰል የአገልግሎት ክፍያዎች እየከፈሉ ሊቆዩ አይችሉም፡፡ ምናልባትም አንዳንድ ክፍያዎችን ሊያቆሙ ወይም ሊቀንሱ ቢችሉም እንደሠራተኛ ደመወዝ የመሳሰሉ ክፍያዎችን ግን ያለምንም የሕግ መነሻ ሊያቋርጡ የማይችሉ በመሆኑ ከላይ የተጠቀሰውን የዕገዳ ሥነ ሥርዓት ተከትለው እንደተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ እርምጃዎችን በጥንቃቄ ሊወስዱ እንደሚችሉ ይህ ጽሑፍ መነሻ ሀሳብ ያስቀምጣል፡፡ ሠራተኞችም ለምሳሌ የግል የትምህርት ተቋማት መምህራን የመጋቢት ወር ደመወዝ ሙሉ ለሙሉ ይገባልን ይሆን? ቀጣዮቹን ወራትስ እንዴት ያደርጉናል? የሚል ከፍተኛ ሥጋት ላይ ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አሠሪዎች ያላቸውን የገንዘብ አቅም አጢነው የተከሰተውን ችግር በመተባበር፣ በመተጋገዝ እና በመተዛዘን የብድር ሁኔታዎችን እያመቻቹ ሌሎች ሠራተኞቻቸው ኑሯቸውን ሊገፉ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጥሩ መልካም ቢሆንም ይህንን ለማድረግ የሚቸገሩ ካሉ ግን ከላይ በዝርዝር የተቀመጠውን የሕግ አማራጭ በመጠቀም ጊዜያዊ መፍትሄ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ሠራተኞችም ይህ ሊከሰት እንደሚችል በማሰብ የራሳቸውን ሌሎች አማራጮች እንዲጠቀሙ፤ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ይህ ጽሑፍ የማንቂያ ደውል ይሆናል፡፡

ሆኖም ይህ ጽሑፍ በማንኛውም መልኩ የሕግ ምክር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ-መንግሥት መተርጎም ላይ ያለው ሚና እና...
Burden of Proof in Tax Disputes: Ethiopia  

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024