By Mulugeta Mengist Ayalew (PhD) on Friday, 19 June 2015
Category: Contract Laws Blog

ያልተመለሰ የገንዘብ ብድር ያለስምምነትና ያለማስታወቂያ/ያለማስጠንቀቂያ ወለድ ይቆጥራል?

የጉዳዩ መነሻ

ለዚህ አጭር ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 74950 የሰጠዉ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ጉዳዩ የገንዘብ ብድርን ይመለከታል፡፡ ተበዳሪ ከአበዳሪ በታሕሳስ 26 ቀን 1995 የተወሰደዉን ብር 237000.00 በጥር 30 ቀን 1995 ለመመለስ ቃል ገብቷል፡፡ ነገር ግን ገንዘቡን ሳይመልስ በመቅረቱ የአበዳሪ ወራሾች በተበዳሪ ላይ ሐምሌ 21 ቀን 2002 ባስገቡት ክስ ተበዳሪ ዋናዉን ገንዘብ እንዲመልስና ከየካቲት 01 ቀን 1995 መሰረት የሚታሰብ ወለድም እንዲከፍል ዳኝነት ይጠይቃሉ፡፡ ተበዳሪ በበኩሉ በዉላቸዉ ዉስጥ ወለድ ይከፍላል የሚል ቃል እንደሌለና ማስታወቂያ/ማስጠንቀቂያ ስላልተሰጠዉ ወለዱን መክፈል እንደማይገደድ ይከራከራል፡፡ በዚህ ሙግት የተነሳዉና ይህ ጽሁፍ የሚዳስሰዉ ጥያቄም ይኸዉ ነዉ፤ ያልተመለሰ የገንዘብ ብድር ያለስምምነትና ያለማስታወቂያ/ያለማስጠንቀቂያ ወለድ ይቆጥራል?

ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት

ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተዉ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የብድር መመለሻ ጊዜዉ ቁርጥ (ጥር 30) ባለመልኩ ስለተቀመጠ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1775(ለ) መሰረት ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ ገንዘብ ጠያቂዉ ማስጠንቀቂያ መስጠት አያስፈልገዉም፡፡ ስለሆነም ማስጠንቀቂያ ስላልተሰጠኝ ወለድ ልከፍል አይገባም የሚለዉ ክርክር ተቀባይነት ስለሌለዉ ተበዳሪ ከየካቲት 01 ቀን ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ዋናዉን የብድር ገንዘብ ይክፈሉ ሲል ወስኗል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የይግባኝ አቤቱታ የቀረበለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ በፍሬ ነገርም ሆነ በሕግ ቅሬታን የሚያስከትል አይደለም በማለት የአበዳሪዉ ወራሾችን ሳይጠራ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

ሰበር ችሎት

ይህን ጉዳይ በተመለከተ የመጨረሻ ዉሳኔ የሰጠዉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት እንዲህ በማለት ነዉ፡፡

ሆኖም ግራ ቀኙን የሚያከራክረዉ ጉዳይ የገንዘብ ብድር ጉዳይ እንደመሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳን ክርክር ስለዚሁ ጉዳይ የሚገዛዉ ልዩ የሕግ ክፍል ተፈጻሚ በማድረግ ምላሽ የሚሰጠዉ ሆኖ ከተገኘ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1676 እንደተመለከተዉ ጉዳዩ በዚህ ለጉዳዩ በቀጥታ ተፈጻሚነት ባለዉ የሕግ ክፍል መሰረት የሚታይ እንጂ ስለዉሎቸ በጠቅላላዉ በሚለዉ የሕግ ክፍል የተቀመጡት ድንጋጌዎች አግባብነት አይኖራቸዉም፡፡ ከዚህ አንጻር ይህንኑ በግራ ቀኙ መካከል የተነሳዉን አከራካሪ ነጥብ ለይቶ ለመወሰን ለጉዳዩ አግባብነት ያለዉን የፍ/ብሔር ሕጉ የሚያልቅ ነገር ብድርን አስመልክቶ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ጋር ተገናዝቦ ሊታይ ይገባል፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2478 ላይ ተበዳሪዉ ወለድ እንዲከፍል የዉል ቃል ከሌለ በቀር ለአበዳሪዉ ወለድ መክፈል የለበትም በሚል የተቀመጠዉ ድንጋጌ ተዋዋይ ወገኖች ባላቸዉ የመዋዋል ነጻነት ተጠቅመዉ በገንዘብ ብድሩ ዉል ስለወለዱ አከፋፈል የጠቀሱት ጉዳይ ባይኖር ይህ መሰል የገንዘብ ብድር ዉል ስምምነት የወለድ ክፍያ ግዴታን ያስከትላል ወይስ አያስከትልም የሚል ክርክር እንዳይነሳ ሕጉ ክፍተቱን ለመሙላት ማስቀመጡ እንጂ ተበዳሪዉ በገባዉ ግዴታ መሰረት የብድር ገንዘቡን በመመለሻዉ ጊዜ አለመክፈሌ ቢረጋገጥ ይህ የመክፈያ ጊዜዉ ላለፈበት ጊዜ ወለድ የማይፈከል መሆኑን ሁሉ የሚሸፍን አይደለም፡፡

ይህም በመሆኑ ነዉ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2489(1) ተበዳሪ የተበደረዉን ነገር ከመመለስ ወይም ከመክፈል የዘገየ እንደሆነ ስለዉሎች በጠቅላላዉ በሚለዉና አግባብነት ባለዉ ሕግ መሰረት ጊዜ በማሳለፍ የሚፍለዉን ወለድ የመክፈል ግዴታ አለበት በሚል የተደነገገዉ፡፡ ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚነቱ የወለድ ግዴታን ላካተተም ላላካተተም ጭምር እንደሆነ ከይዘቱ መረዳት ይቻላል፡፡

ይህም በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2489(1) የተመለከተዉ ስለዉሎች በጠቅላላዉ የሕግ አፈጻጸም እንደብድሩ አይነት እየታየ ተግባራዊ የሚሆኑ እንጂ ለማናቸዉም የብድር ገንዘብ መቼም ቢሆን ተፈጻሚ ሊሆን እንደማይችል የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2482 እና 2483 ድንጋጌ ንባብ አስረጂ ነዉ፡፡

በመሆኑም በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2482 እንደተደነገገዉ ይክ ክርክር ያስነሳዉ የብድር ስምምነት የብድር ገንዘቡን መመለሻ ጊዜ አስቀድሞ መስኖ ያስቀመጠ በመሆኑ እና ወለድ የመክፈል ግዴታም ያላስቀመጠ በመሆኑም እንደዚህ ያለ የብድር መመለሻ ጊዜ ተወስኖ ከሆነ የብድር ገንዘቡን ከዚህ መመለሻ ጊዜ በፊት የመክፈል ግዴታዉን በተበዳሪዉ ላይ የሚጣል እንጂ ይህ የመክፈያ ጊዜ ካለፈ በኋላ አበዳሪዉ ለተዳሪዉ ጊዜዉ አልፏልና ክፈለኝ በማለት ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ የለበትም፡፡ አበዳሪ የማስታወቅ ግዴታ የሚኖርበት በብድር ዉሉ ላይ የብድሩን ገንዘብ መመለሻ ጊዜዉ ያልተወሰነ እንደሆነ ብቻ ስለመሆኑ ተከታይ በሆነዉ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2383 ተመልክቷል፡፡

ስለመሆኑም አለምካች የወሰዱትን የብድር ገንዘብ ብ እንጂ ወለዱንም ጨምረዉ ለመክፈል ግዴታ ያልገቡት ስምምነት በመሆኑ እና የመክፈያ ጊዜዉ በዉሉ ላይ ተወስኖ የተቀመጠ በመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ.2482(2) እና (3) መሰረት በመመለሻ ጊዜዉ የመክፈል ግዴታ ያለበት መሆኑን ተረድቶ ጊዜዉ ከማለፉ በፊት አለመክፈሉ እስከተረጋገጠ ድረስ የብድር ገንዘጉን ከሕጋዊ ወለድ ጋር የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡በዚህ ሁሉ ምክኒያት የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ዳኝነት በዉጤት ደረጃ ሲታይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አላገኘነዉም፡፡

 

ተበዳሪዉ ነገሩን ስለተጠቀመበት የሚከፈል ወለድ፤ ያለስምምነት ወለድ ይከፈላል?

የመጀመሪያዉ ጥያቄ የሚሆነዉ ተዋዋይ ወገኖች የገንዘብ ብድር ዉል በሚያደርጉበት ወቅት ወለድ ይከፈላል ብለዉ ካልተስማሙ አበዳሪዉ ወለድ ለመጠየቅ ይችላል ወይ የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህን ለመመለስ የወለድ ክፍያ ጥያቄዎች ብዙ አይነት መሆናቸዉን መገንዘብ የመጀመሪያዉ አስፈላጊ ነገር ነዉ፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ሁለቱን እዚህ ማየት ይቻላል፡፡

የመጀመሪያዉ አይነት ስምምነት ተበዳሪዉ የወሰደዉን ገንዘብ በመጠቀሙ የተነሳ የሚከፍለዉ ወለድ ነዉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰዉ አንድን ቤት በኪራይ ሲጠቀም  እንደሚከፍለዉ ክራይ ሁሉ ይህ ወለድ አንድ ሰዉ ገንዘቡን በብድር ወስዶ መጠቀም በመቻሉ የተነሳ የሚከፍለዉ ነዉ፡፡ ልክ ተከራይ ክራይ እንደሚከፍለዉ፤ ገዥ ዋጋን እንደሚከፍል፤ አሰሪዉ ለተሰራዉ ስራ ክፍያ/ደመዎዝ እንደሚከፍለዉ ሁሉ፤ ተበዳሪዉ ወለድ ይከፍላል፡፡ ከዚህ አንጻር ስንመለከተዉ ዉሎችን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ እነዚህም contracts for consideration እና gratuitous contracts ይባላሉ፡፡ contracts for consideration የሚባሉት ሁለቱም ወገኖች ግዴታዎች የሚኖሯቸዉ ናቸዉ፡፡ የስራ ዉል ሁል ጊዜ contracts for consideration ነዉ፡፡ ይህም ማለት ሁለቱም ተዋዋይ ወገኖች (አሰሪና ሰራተኛዉ) ግዴታዎች አሏቸዉ፤ ሰራተኛዉ ለስራዉ ክፍያ ያገኛል፡፡ የሽያጭ ዉልም እንዲሁ፤ ለገዛዉ እቃ/ንብረት ገዢ ዋጋ ይከፍላል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አንዳንድ ዉሎች የችሮታ ዉሎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የማይከፈለዉ እንደራሴ ሊኖር እንደሚችል ሕጋችን ያመለክታል፡፡

ወደ ገንዘብ ብድር ስንመጣ፤ 2471 ትርጓሜዉን በዚህ መልኩ ያስቀምጠዋል፤ የሚያልቅ ነገር ብድር ማለት ከተዋዋዮቹ አንዱ ወገን አበዳሪዉ ሌላዉን ተበዳሪ ሰዉ የተበደረዉን ነገር በአይነቱ ለመመለስ ተገዳጅ በማድረግ ገንዘብ ወይም በማገልገል የሚያልቅ ሌላ ነገር ለተበዳሪዉ ለመስጠትና ሀብትነቱን ለማስተላለፍ የሚገደድበት ዉል ነዉ፡፡ ከዚህ የምናየዉ የብድር ዉል እንደነገሩ ሁለት አይነት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህም እላይ እንደተጠቀሰዉ contracts for consideration እና gratuitous contracts ናቸዉ፡፡ የብድር ዉሉ gratuitous ከሆነ የተቀበለዉን ዋና ገንዘብ ከመመለስ ዉጭ ሌላ ነገር እንዲከፍል አይገደድም፤ ማለትም ወለድ የለለዉ ብድር ነዉ ማለት ነዉ፡፡ በሌላ ጎኑ ግን ዉሉ for consideration ከሆነ ዋናዉን ከመመለሱ በተጨማሪ ወለድ እንዲከፍል ይገደዳል ፡፡ በዚህ አግባብ ወለድ ማለት ገንዘቡን ወይም ንብረቱን ስለተጠቀመበት የሚከፍለዉ ዋጋ ነዉ፡፡

የብድር ዉል ሁለት አይነት ገጽታ ሊኖረዉ እንደሚችልና ከሚኖረዉ የሕግ ዉጤት አንደኛዉን የፍ/ብ/ሕ/ቁ.2474 ያስቀምጣል፤

2474፡ የአበዳሪ ግዴታ

(1)  በሽያጭ ዉል ምእራፍ የተነገሩት የሻጭን ግዴታዎች የሚመለከቱ ደንቦ በአበዳሪዉ ላይ የሚፈቀሙ ይሆናሉ፡፡

(2)  ነገር ግን ብድሩ እንዲያዉ ያለ ዋጋ ተደርጎ እንደሆነ የአበዳሪዉ ግዴታዎች በቀላሉ የሚገመቱ ይሆናሉ፡፡

(3)  በዚህ ጊዜ ባበደረዉ ነገር ላይ ለሚገኘዉ እርሱ ለሚያዉቀዉ ጉድለት ብቻ ካልሆነ ዋቢ መሆን የለበትም፡፡

 

ከላይ ማየት እንደሚቻለዉ በዋጋና በችሮታ የተደረጉ ዉሎች በአበዳሪዉ ላይ የሚጥሉት የግዴታዎች መጠን ይለያያል፡፡

ይህን ካልን በኋላ አሁን የሚነሳዉ ጥያቄ ታዲያ፤ በብድር ዉሉ ላይ ተበዳሪ ወለድ እንደሚከፍል ካልተገለጸ፤ ወለድ እንዲከፍል ይገደዳል ወይ የሚለዉ ነዉ፡፡ ወለድን አስመልክቶ ገዥዉ መርህ በቁጥር 2478 የተቀመጠዉ ነዉ፤ ተበዳሪዉ ወለድ እንዲከፍል የዉል ቃል ከሌለ በቀር ላበዳሪዉ ወለድ መክፈል የለበትም፡፡ ስለዚህ ወለድ የሚከፈለዉ በዉሉ ወለድ ይከፈላል የሚል ቃል ካለ ብቻ ነዉ፡፡ተቀራራቢ ድንጋጌ ስለዉክልና የሚመለከተዉ የፍትሐ ብሔር ክፍል ያስቀምጣል፤ በዉሉ ደመዎዝ እንደሚከፈለዉ ካልተቀመጠ፤ እንደራሴዉ ክፍያ መጠየቅ አይችልም ይላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተጨማሪ ሕጉ ምንም እንኳ ዉላቸዉ ዝም ቢልም፤ ስራዉ በተለምዶ ክፍያ የሚከፈለዉ አይነት ከሆነ እንደራሴዉ ክፍያ መጠየቅ ይችላል፡፡ ተመሳሳይ አይነት ድንጋጌ ግን ብድርን አስመልክቶ አልተቀመጠም፡፡ ነገር ግን በተለምዶ ብድር የሚከፈልበት ከሆነ ልምዱ/አሰራሩ በ1713 መሰረት የዉሉ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ዋናዉ ቁም ነገር እዚህ ላይ በዉላቸዉ ላይ (በግልጽ ወይም በ1713) መሰረት ወለድ ይከፍላል የሚል ነገር ከሌለ ተበዳሪዉ ወለድ እንዲከፍል አይገደድም፡፡ ይህ አባባል አንደኛዉን አይነት ወለድ ነዉ የሚመለከተዉ፡፡

ተበዳሪዉ ነገሩን ለመመለስ ስላዘገየ የሚከፈል ወለድ፤ ያለስምምነት ወለድ ይከፈላል?

ሁለተኛዉ አይነት ወለድ ምንድን ነዉ? ሁለተኛዉ ወለድ አንድ ተበዳሪ የወሰደዉን ገንዘብ ወይም እቃ በወቅቱ ባለመመለሱ የተነሳ የሚከፍለዉ ነዉ፡፡ ልብ ማለት የሚገባን ገንዘቡን ወይም እቃዉን ስለተገለገለበት የሚፈጽመዉ ክፍያ ሳይሆን ገንዘቡን ወይም እቃዉን በወቅቱ ባለመመለሱ የተነሳ የሚከፍለዉ ነዉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ተዋዋይ ወገን አንድን ስራ (በልክ የተሰፋ ልብስ ለምሳሌ) በተወሰነ ወቅት ለመጨረስ ተስማምቶ ባይሳካለትና ቢዘገይ መዘግየቱ ላደረሰዉ ኪሳራ ካሳ ይከፍላል፡፡ ይህ እንደዚህ እንደሆነዉ አንድ ተበዳሪ የወሰደዉን ገንዘብ ወይም እቃ በወቅቱ ካልመለሰ የሚከፍለዉ  ካሳ ወለድ ይባላል፡፡ ቁጥር 2489 እንዲህ ይላል፤

2489፡ ኪሳራ

(1)ተበዳሪዉ የተበደረዉን ነገር ለመመለስ ወይም የሚገባዉን ወለድ ከመክፈል የዘገየ እንደሆነ ስለ ዉሎች በጠቅላላዉ በሚል አንቀጽ በተሰጡት ዉሳኔዎች መሰረት ጊዜ በማስተላለፍ የሚከፈለዉን ወለድ እንዲከፍል ይገደዳል፡፡

(2)ይህን ግዴታ የሚያከብድ ማንኛዉም የዉል ቃል ፈራሽ ነዉ፡፡

 

2489 ተበዳሪዉ የወሰደዉን ነገር ለመመለስ ወይም ወለዱን ለመክፈል ከዘገየ በጠቅላላ የዉል ድንጋጌ መሰረት ወለድ እንደሚከፍል ይናገራል፡፡የእንግሊዘኛዉ ቅጅ ከቁጥር 1790 እስከ 1805 ያሉት የጠቅላላ የዉል ሕግ ድንጋጌዎችን መጠቀም እንዳለብን ይናገራል፡፡ በተለይ ከ1803 እስከ 1805 ያሉት ድንጋጌዎች ይህን ወለድ በተመለከተ ተፈጻሚነት አላቸዉ፡፡

1803፡ የገንዘብ እዳ፤ (1) ጊዜ በማሳለፍ ስለሚከፈል ወለድ

(1) የገንዘብ እዳ እንዲከፍል ማስጠንቀቂያ የደረሰዉ ባለእዳ አነስተኛ ወለድ እንዲከፍል በስምምነቱ ቢወሰንም አንኳ በሕግ የተወሰነዉን ወለድ መክፈል አለበት፡፡

(2) በዉለታዉ ዉስጥ የበለጠ ወለድ የታሰበ እንደ ሆነ በዚሁ በከፍተኛዉ ወለድ መታሰቡ ይቀጥላል፡፡

(3) ባለገንዘቡ ምንም ኪሳራ ባይደርስበትም ወለድ ይገባዋል፡፡

1804፡ (2) የወለድ ወለድ

(1) ከባለእዳዉ ላይ ያለዉ ገንዘብ በየጊዜዉ የሚከፈል ሆኖ ለባለገንዘቡ በየጊዜዌ የሚገኘዉ ገቢ የሆነ እንደ ሆነ ለምሳሌ ኪራይ፤ የርስት አላባ፤ የዘወትር ጡረታ ወይም ለሕይወቱ የተወሰነ ጡረታ የአንድ ካፒታል ወለድ፤ ይህን የመሰለ ከሆነ ደንበኛዉ ወለድ የሚታሰበዉ ክስ ለአንድ ፍርድ ቤት ከቀረበበት ቀን ጀምሮና ይኸዉም ባለእዳዉ የአንድ አመት ሙሉ ሒሳብ ያለበት እንደሆነ ነዉ፡፡

(2) ተመላላሽ ሒሳብን የሚመለከቱት ደንቦች የተጠበቁ ናቸዉ፡፡

1805፡ (3) የጉዳት ኪሳራ ማቻቻያ

ባለገንዘቡን ያገኘዉ ጉዳት ጊዜ በማሳለፍ ምክንያት ከሚከፈለዉ ወለድ የበለጠ የሆነ እንደሆነ ዉሉን በተዋዋሉ ጊጊ ባለእዳዉ ማስጠንቀቂያ ተደርጎለት እንደ ሆነ ወይም ዉለታዉ ያልተፈጸመበት ባለገንዘቡን ለመጉዳት በመፈለጉና በከባድ ችልታና ወይም በከባድ ጥፋት ሲሆን ኪሳራዉን ባለእዳዉ በሙሉ መክፈል አለበት፡፡

ሁለተኛዉ አይነት ወለድ አንድ ሰዉ የዉል ግዴታዉን ባለመፈጸሙ ወይም በማዘግየቱ የተነሳ የሚከፍለዉ ካሳ እኩያ ነዉ፡፡ ልዩነቱ የዘገየዉ ግዴታ ገንዘብ የመክፈል ግዴታ መሆኑ እና 1803(3) ብቻ ነዉ፡፡

ከላይ የተደረጉ መግለጫዎችን ተከትሎ እነዚህን ሁለት ነጥቦች አንደ ማጠቃለያ አስቀምጪ ልለፍ፤

1.  አንድ ተበዳሪ ለወሰደዉ የገንዘብ ወይም የእቃ ብድር ወለድ (ለተጠቀመበት) የሚከፍለዉ በዉሉ ወለድ የመክፈል ቃል ካለ ብቻ ነዉ፡፡

2.  ነገር ግን አንድ ተበዳሪ ወለድን የመክፈል ቃል በዉሉ ወስጥ ኖረም አልኖረም መመለስ የሚገባዉንና የተበደረዉን ገንዘብ ካዘገየ፤ በ1790 ጀምሮ ባሉት ድንጋጌዎች መሰረት ወለድ (ላዘገየበት) ይከፍላል፡፡

ከላይ ከተቀመጡት ነጥቦች አንጻር የሰበር ሰሚዉ ዉሳኔ ሲፈተሸ ተገቢ ዉሳኔ ነዉ ሊባል ይችላል፡፡ አሁን ደግሞ ስለማስታወቂያ እንመለከታለን፡፡

ያለማስታወቂያ/ማስጠንቀቂያ ወለድ ይከፈላል?

1803(1) እንዳስቀመጠዉ የገንዘብ እዳ እንዲከፍል ማስጠንቀቂያ የደረሰዉ ባለእዳ አነስተኛ ወለድ እንዲከፍል በስምምነቱ ቢወሰንም አንኳ በሕግ የተወሰነዉን ወለድ መክፈል አለበት፡፡ የተሰመረበትን ቃል ልብ ይሏል፡፡ ገልብጠን ካነበብነዉ እንዲህ የሚል ነዉ፤ የገንዘብ እዳዉን እንዲከፍል ማስጠንቀቂያ ያልደረሰዉ ባለእዳ ግን ወለድ መክፈል አይገባዉም፡፡ ጉዳዩን ግን ዘርዘር አድርገን እንደሚከተለዉ እናየዋለን፡፡

በዉል ሕግ መሰረት አንድ ተዋዋይ ወገን ግዴታዉን በሕግና በዉሉ መሰረት ካልፈጸመ እንደነገሩ ሁኔታ ያኛዉ ተዋዋይ ወገን ዉሉን ሊያፈርስ፤ በዉሉ መሰረት እንዲፈጸም፤ እና/ወይም ካሳ እንዲከፈለዉ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ይህ በ1771 የተቀመጠዉ ነዉ፡፡

ነገር ግን ይህን ከመጠየቁ በፊት ባለገንዘቡ በባለእዳዉ ማስታወቂያ መስጠት እንዳለበት በ1772 ተቀምጧል፤ እንደዉሉ ሳይፈጸምልኝ ቀርቷል በማለት ክርክር ለማቅረብ የሚፈልገዉ አንደኛዉ ወገን ተዋዋይ የተዋዋለዉ ሰዉ ግዴታዉን እንዲፈጽምለት ለማድረግ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠዉ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳዉ ጥያቁ፤ ማስታወቂያ ለምን ያስፈልጋል፤ ምንስ አላማዎች አሉት የሚል ነዉ፡፡ ይህን አስመልክቶ የፍትሐ ብሔር ሕግ ረቂቅ አዘጋጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ሬኔ ዴቪድ ይህን ብለዋል፡፡

Before a person can assert the rights that arise from non-performance of a contract, he must put the other party in default, that is he must call his attention to the fact that the obligations are due and to the sanctions the debtor may incur if he does not perform them. This requirement of putting the other party in default by notice exists in all Western legal systems: French (Civil Cod, Article 1139), Swiss (Code of Obligations, Article 102); Lebanese (Civil Code, Article 257), Italian (Civil Code, Article 1219), Greek (Civil Code, Article 340) and Egyptian (Civil Code, Article 218).

No special formality is required to put a person in default. The notification can be by means of an official summons, or simply by a letter, even unregistered. The notification of default can be accomplished by any act that indicates to the debtor that the time has come for him to perform his obligation and that indicates the creditor’s intention to require performance. The only condition imposed by the law concerns the time for notification; it cannot be given before the debtor’s obligations are due and, thus, enforceable.

The notification of default has four functions. In obligations to give, it puts the risk of loss of the thing on the debtor. In obligations to pay money, it begins the accumulation of interest for delay. More generally, it reminds the debtor of his obligations and of the sanctions he will face if he does not perform. And finally, it should lessen the number of cases that come before the courts; they will only get cases in which there is a clear failure to perform.

 

ቺቺኖቪች በአንጻሩ በትንሹ የተለየ ሃሳብ ያራምዳል፤

David’s comment that the default notice “must call the debtor’s attention to the fact that his obligations are due and to the sanctions he may incur If he does not perform” is incompatible with the wording of the present article and the foreign provisions he cites (primarily art.1139 French Civ.Code and art.102 Swiss Obligations Code). A default notice not mentioning sanctions is therefore fully effective.

David’s Comment that, in obligations to give, the default notice puts the risk of loss of the thing on the debtor is misleading, since his reader will necessarily infer that the debtor is free from such risk before this notice. Pursuant to article 1758, the opposite is true: the debtor in any case bears risk until delivery or until the creditor’s default. “Putting” the risk of loss on a debtor already bearing it is obviously impossible. David’s affirmation that the Code does not require a default notice “where it cannot serve any of these ends” is inaccurate.    

የኢትዮጲያን የዉል ሕግ አስመልክቶ በሰፊዉ ተነባቢነትን ያተረፈዉና በፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ የተዘጋጀዉ መጽሃፍ ማስጠንቀቂያን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡

ከሁሉም በፊት የባለእዳዉ ዉል አለማክበር የሚረጋገጠዉ ከባለገንዘቡ ለሚደርሰዉ ማስጠንቀቂያ በሚሰጠዉ ምላሽ ነዉ፡፡ማስጠንቀቂያ ግዴታዉን ለመወጣት ፈቃደኝነት ለማያሳይ ዳተኛ ባለእዳ ባለገንዘቡ የሚያቀርበዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ካልሰጠ ወይም አሉታዊ የሆነ ምላሽ ከሰጠ ባለገንዘቡ የሚሰጠዉን መብት ሊሰራበት ይችላል፡፡ በሕግ ወይም በዉል የተለዩ ሁኔታ ካልተገለጸ በስተቀር የመክፈያዉ ወይም የግዴታ መወጫዉ ጊዜ ያለፈ ቢሆንም እንኳ ለባለእዳዉ ተገቢዉ ማስጠንቀቅያ ካልተሰጠ ዉሉን ለማክበር ፍላጎት የሌለዉ መሆኑ ተረጋግጧል (The debtor is in default) ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ይልቁንም የመክፈያ ጊዜዉ የደረሰዉን እዳ ለመጠየቅ የበሁሉን ጥረት ከማድረግ የተቆጠበ ባለገንዘብ በባለእዳዉ ቸልተኝነት እንደተስማማ ሕግ ግምት ይወስዳል፡፡የማስጠንቀቂያ አስፈላጊነትን የሚመለከተዉን ደንብ ታሪክ ከሮማዉያን ሕግጋት ጋር ያገናዘቡ አንድ ጸሃፊ ባቀረቡት ድርሰት ይህ ደንብ መጀመሪያ ያስፈለገዉ የዉል መፈጸሚያዉ ጊዜዉ በግልጽ ላልተቆረጠ ግዴታ አፈጻጸም የዉሉ ባለመብት የሆነዉ ወገን የግዴታ መፈጸሚያ ጊዜ እንዲሰጠዉ ለማድረግና ባለመብቱ ይህንን ካደረገና ዉሉ ካልተፈጸመለት በሕግ ክስ የመመስረት መብት እንዲፈቀድለት ነዉ ሲሉ ያብራሩና ከዚያ ወዲህ ግን አፈጻጸሙ ሌሎችንም ጉዳዮች እንዲያካትት ተደርጎ አሁን ያለዉን መልክ ማግኘቱን ይገልጻሉ፡፡

የማስጠንቀቂያ አሰጣጥ በተለይ በሲቪል ሎዉ ሕግጋት ሁለት አበይት አላማዎች እንዳሉት በመስኩ ጥናት ያደረጉ ብዙዎች ጽሐፍት ይስማማሉ፡፡ አነዚህም የባለእዳዉን ግዴታ ያለመወጣት በማረጋገጥ የጉዳት ኪሳራ የመጠየቅ መብት መግኘትና በተለይም የማስረከብ ግዴታ ባለበት ዉል ዉስጥ በእቃዎቹ ላይ የሚደርሰዉ ድንገተኛ ያልተጠበቀ አደጋ የሚያስከትለዉን የጉዳት ኪሳራ ሃላፊነት (risk) ወደ ባለእዳዉ ማሸጋገር ናቸዉ፡፡ ይህን መብት ለማግኘት የባለእዳዉ የግዴታ መፈጸሚያ ጊዜ የደረሰና የግዴታዉም አፈጻጸም የሚቻል መሆኑንም አብሮ መረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጲያ ሕግም ቢሆን ከዚህ አጠቃላይ ሂደት የተለየ አይደለም፡፡ ሕጉን ያረቀቁት ፕሮፌሰር ረኔ ዳቪድ በዚህ ረገድ ማስጠንቀቂያ አራት ተግባራት እንዳሉት ያብራራሉ….

እላይ እንደጠቀስኩት በሕጉ አርቃቂና በሕጉ ተንታኝ (ቺቺኖቪች) መካከል መለስተኛ ልዩነት አለ፡፡ ይኽም transfer of riskን ይመለከታል፡፡ ይህን አስመልክቶ በአንድ ወቅት በእንግሊዘኛ ያዘጋጀዉት መጽሀፍ ያሰፈርኩትን እዚህም ደግሜ ልለፍ፡፡

David mentioned also another function of default notice: ‘in obligations to give, it puts the risk of loss of the thing on the debtor’. This function of default notice is arguable. This is because, in such cases, the risk is already on the side of the debtor and hence there is nothing to be transferred away from the creditor.

…If the drafter, by using the term ‘debtor’, meant to refer to the party who has the obligation to take delivery, then giving default notice could transfer the risk from the one who is supposed to deliver the thing. 

Transfer of riskን አስመልክቶ ከታየዉ መጠነኛ ልዩነት በስተቀር በሌሎች ነጥቦች ላይ መግባባት አለ፡፡ ሬኔ ዴቪድ፤ ቺቺኖቪች፤ እና ጥላሁን ተሾመ ማስጠንቀቂያ መስጠት ወለድ እንዲቆጥር ለማድረግ አስፈላጊ ነዉ ይላሉ፡፡ እንዲሁም በ1803(1) መጀመሪያ ላይ ይኸዉ ተመላክቷል፡፡ በመሆኑም በግልጽ በሕጉ በተለየ መልኩ ካልተቀመጠ በስተቀር የገንዘብ እዳን መክፈል ያዘገየ ሰዉ ወለድ የሚከፍለዉ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠዉ ጊዜ ጀምሮ ነዉ፤ ከዛ በፊት ማስጠንቀቂያ ካልተሰጠዉ ደግሞ የክሱ አቤቱታ ከደረሰዉ ጊዜ ጀምሮ ነዉ፡፡ እንዳልኩት እንዳንዴ ሕጉ የተለየ ድንጋጌ ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ እላይ በጠቀስኩት መጽሀፍ ላይ በእንግሊዘኛ ይህን አስቀምጨ ነበር፤

The drafter wrote that default notice has the general purpose of reminding a party of his or her obligations. In addition, it ‘should lessen the number of cases that come before the courts; they will only get cases in which there is a clear failure to perform’. On top of these two general purposes, by putting a debtor in default for an obligation to pay money, one can legitimately claim interest for delay of the payment afterward. As far as the claim of inetrest on an obligation to pay money is concerned, it should be noted that the law disregards this requirement in certain circumstances. For example, Article 2210(2) provides, ‘where the agent converted to his own use monies he owed to the principal, he shall be liable for the payment of interest as from the day of such use, without it being necessary that notice be given to him’. Likewise, Article 2221(3) provides, ‘interest on (outlays made and expenses incurred by the agent in the proper carrying out of the agency) shall be due by the principal as from the day when they were incurred without it being necessary to place the principal in default”.  

 

ይህ አባባል የሚያጠናክርልን ነገር፤ ማስጠንቀቂያ ለወለድ የማያስፈልግ ከሆነ ሕጉ ልክ 2210(2) እና 2221(3) እንዳደረገዉ ማስጠንቀቂያ አያስፈልግም ይላል፡፡

ከማስጠንቀቂያ ጋር ተያይዞ መረሳት የሌለበት ነገር አንዳንድ ጊዜ ማስጠንቀቂያ አያስፈልግም፡፡ሬኔ ዴቪድ እንዲህ ይላል፤ where the notification of default cannot serve any of these ends, the Code does not require the creditor to use it and allows him, instead, to immediately bring a court action against the debtor. ከዚህ ጋር በተያያዘ ቁጥር 1775 በሚከተሉት ሁኔታዎች ማስጠንቀቂያ መስጠት አያስፈልግም ይላል፤

(ሀ) ያለማድረግ ግዴታ በሚያጋጥምበት ጊዜ፤

(ለ) ባለእዳዉ በዉሉ ላይ በተመለከተዉ መሰረት የዉሉን ግዴታ የሚፈጽምበት ጊዜ በዉሉ ላይ ተመልክቶ እንደሆነና ይህ የተወሰነዉ የግዴታ መፈጸሚያ ዘመን ያለፈ እንደሆነ

(ሐ) ባለእዳዉ ግዴታዉን የማይፈጽም ስለመሆነ በጽሁፍ ያስታወቀ እንደሆነ

(መ) ማንኛዉም ሌላ ተግባር ሳያስፈልግ በዉሉ የተወሰነዉ ጊዜ እንዳለፈ ወዲያዉኔ ለባለእዳዉ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠዉ ይቆጠራል የሚል ቃል በስምምነቱ ላይ ተመልክቶበት እንደ ሆነ ነዉ፡፡

 

ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ የተለመከተዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ1705(ለ) መሰረት ብድሩ የሚመለስበት ቀን በዉሉ ስለተቀመጠ፤ ይህ ቀን ካለፈ በኋላ ማስጠንቀቂያ መስጠት አያስፈልግም በሚል ወስኗል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በይግባኝ ይኽን አባባል ተቀብሎታል፡፡ ጥያቄዉ በእርግጥ 1775(ለ) ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚነት አለዉ ወይ የሚል ነዉ፡፡ በዉሉ ላይ የግዴታዉ መፈጸሚያ ወቅት በመቀመጡ ብቻ ማስጠንቀቂያ አያስፈልግም ማለት አይቻልም፡፡

በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥላሁን ተሾመ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ባይሰጡም ይህን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሳኔ የሚደግፉ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የሬኔ ዴቪድ ማብራሪያ የዉል መፈጸሚያ ግዴታ መቀመጡ ማስጠንቀቂያ አያስፈልግም ወደሚል መደምደሚያ አይወስደንም፡፡ እንደዉም የእንግሊዘኛዉ ቅጂ ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል፤ the debtor assumed to perform an obligation which the contract allows to be performed only within a fixed period of time and such period has expired. አርቃቂዉ ይህን አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያ ይህን ይመስላል፡፡

A orders some fire-crackers and dance constumes from B for a feast or fair. It is obvious that A intends to sell these items at the feast and that if they are delivered late he will not be able to sell them for a very long time. B will be subject to the sanctions for non-performance if he has not delivered the items before the fair. A notification of default is not necessary in such a case.

ስለዚህ የዉሉ መፈጸሚያ ጊዜ ስለተቀመጠ ብቻ ማስጠንቀቂያ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ይህ የሚሆነዉ ከዉሉ ወይም ከነገሮች ሁኔታ ዉሉ የግድ በዚያ ወቅት መፈጸም አለበት ያለበለዚያ ለባለገንዘቡ አይጠቅመዉም የሚባል ከሆነ ነዉ፡፡ ይህን አባባል 1705(መ) የበለጠ ያጠናክረዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ሲታይ የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ የሕግ ስህተት ታይቶበታል፡፡ ይህም በሰበር ችሎቱ አልታረመም፡፡ የብድሩ የመመለሻ ጊዜ ጥር 30 1995 መሆኑ በዉሉ ቢቀመጥም ይህ ቀን ሲያልፍ ያለማስጠንቀቂያ አበዳሪዉ ወለድ መጠየቅ ይችላል የሚል ነገር አልተስማሙም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ ቀን ካለፈ ዉሉ ለአበዳሪዉ ያለዉ ጠቀሜታ እጅግ በጣም ይቀንሳል ሊባልም አይችልም፡፡ በመሆኑም ማስጠንቂያ አያስፈልግም የተባለዉ ስህተት ነዉ፡፡

በሰበር ችሉት ዘንድ ጉዳዩን እላይ በተገለጸዉ መልኩ ያለማየት ስህተት ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የሕግ ድንጋጌዎችን ከተቀመጠበት context ዉጪ እንደሚከተዉ የመጠቀም ግድፈት ፈጽሟል፡፡

2482 እና 2483 ትክክለኛ አግባብ

ሰበር ችሎቱ 2482 እና 2483 ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን አላግባብ ያለቦታቸዉ በመጠቀም ትክክል ያልሆነ ዉሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ እነዚህ ሁለት ድንጋጌዎች ማስጠንቂያ ስለመስጠትና ስላለመስጠት ሳይሆን በብድር የተወሰደን ገንዘብ ወይም እቃ መቼ መመለስ ይቻላል የሚለዉን ነዉ የሚመለከቱት፡፡

በ2482(1) መሰረት ተበዳሪዉ የተበደረዉን ነገር በብዛቱና በአይነቱ ልክ በዉሉ በተወሰነዉ ጊዜ ለመመለስ ይገደዳል፡፡ በተያዘዉ ጉዳይ ላይ የተወሰነዉ ጊዜ ጥር 30 ነዉ፡፡ይህ ማለት በጥር 30 የወሰደዉን ገንዘብ እንዲመልስ ሊገደድ ይችላል፡፡

ተበዳሪዉ ከጥር 30 በፊት መመለስ ቢፈልግ ይችላል ወይ ለሚለዉ 2482(2) እንዲህ ይላል፤ ብድሩ በወለድ ያልሆነ እንደሆነ ተበዳሪዉ የተበደረዉን ለመመለስ ማሰቡን ከአንድ ወር በፊት ላበዳሪዉ አስታዉቆ ከተወነዉ ጊዜ በፊት ሊመልስለት ይችላል፡፡ በወለድ ከሆነ ግን አበዳሪዉ እስካልፈቀደ ድረስ ከዉሉ ጊዜ አስቀድሞ ሊመልስ አይችልም፡፡ 2482(3) መሰረት ከዘጠኝ በመቶ በላይ በሆነ ወለድ ተደርጎ እንደሆነ ምንም እንኳ ማናቸዉም የዉል ቃል ቢኖር የአንድ ወር በፌት አስቀድሞ በማሳወቅ መመለስ ይቻልል፡፡ 2482 የሚያገለግለዉ የመመለሻ ቀኑ በዉሉ ከተወሰነ ነዉ፡፡ የመመለሻ ጊዜዉ ካልተወሰነ ግን 2483 ስራ ላይ ይዉላል፤ አበዳሪዉ መልስልኝ ሲል ከጠየቀበት ቀን አንስቶ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ተበዳሪ የተበደረዉን ነገር መመለስ አለበት፡፡ እንዲሁም በሆነ ጊዜ ተበዳሪ የተበደረዉን ነገር ላበዳሪዉ ለመመለስ አሳቡን ከአንድ ወር ፊት ካስታወቀ በኋላ ሊመልስለት ይችላል፡፡  የ2482 እና 2483 ይዘት ይህ ሆኖ ሳለ ሰበር ችሎቱ ግን ፍጹም out of context በሆነ መልኩ ስራ ላይ አዉሎታል፡፡

በእርግጥ የጠቅላላ የዉል ሕግ ድንጋጌዎች ስራ ላይ የሚዉሉት በልዩ የዉል ሕግ አግባብነት ያለዉ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ ነዉ፡፡ እስከዚህ ድረስ ከሰበር ችሎቱ ጋር ልዩነት የለኝም፤ ልዩነቴ 2482 እና 2483 ማስጠንቀቂያን አስመልክቶ ጠቅላላ ዉል ሕግ የሚያስቀምጠዉ የተለየ ድንጋጌ አስቀምጧል ወይ በሚለዉ ነዉ፡፡ 

 

Related Posts

Leave Comments